ከአዲስ አበባ እስከ ታይዋን የተዘረጋው የሕገ-ወጥ ደላሎች ሥራ አስቸጋሪ እንደሆነበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
የውጭ ጉዳይ መኒስቴር በርካታ ዜጎች በተለይም በማይናማር በስቃይ የሚገኙ ዜጎች ከአዲስ አበባ እስከ ታይዋን በተዘረጋ ሰንሰለት ሰለባ የሆኑ ናቸው ሲል አስታውቋል፡፡
በሚኒቴሩ የቆንስላ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምበሳደር ሲራጅ ረሺድ፤ "በማይናማር በከፍተኛ ሁኔታ ስቃይ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ለማስመለስ ከማይናማር መንግሥት እና ሌሎች አጋሮች ጋር ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ80 በላይ ዜጎችን የማስመለስ ሥራ መሰራቱን የሚናገሩት አምባሳደር ሲራጅ፤ በሁሉም አካባቢ ያሉትን ዜጎች የማስመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩም "ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው ዜጎች ወደ ተለያዩ ሀገራት በሕገ-ወጥ-መንንገድ የሚሄዱበት ጉዳይ ሊቆም ይገባል" ሲሉም አሳስበዋ፡፡
ማክሰኞ ዕለት 32 እንዲሁም ረቡዕ 43 ዜጎች ከማይናማር መመለሳቸውን የገለጹት ደግሞ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ሲሆኑ፤ የማሰመለሱ ሥራ ከፍተኛ የሆነ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በኃላ የተሳካ ጉዳይ መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
የማስመለሱ ሥራ ፈተኛ መሆኑን የሚያነሱት አምባሳደር ነብያት፤ "ከማይናማር ወጥተው ታይላንድ የገቡት ዜጎች በራሱ ከታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ እንኳን 600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ላይ መሆናቸው ችግሩን ከፍተኛ አድርጎታል" ብለዋል፡፡
በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት ችግሮች እንዳሉበት የገለጹም ሲሆን፤ ጃፓን በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ዜጎቹን ወደ ታይላንድ በማሻገር ወደ አገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ዜጎችን ከውጭ ሀገራት ከመመለስ በተጨማሪ በሕጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ብሎም ሕጋዊ መንገድን ተከትለው እንዲሰሩ ከማድረግ አኳያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎች በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ ቢሆንም፤ "በሕገ-ወጥ ደላሎች የተነሳ በርካታ አደጋ እየተጋለጠባቸው ይገኛል" ብለዋል፡፡
"ከአዲስ አበባ እስከ ታይዋን ከዛም አልፎ እስከ ሳኡዲ እና ሌሎች ሀገራት የተዘረጋውን የሕገ-ወጥ ደላሎች ሥራን ለማክሸፍ ከሁሉም ተባባሪ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ዓመት ውስጥ ብቻ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ ከ450 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዚህ ዓመትም ወደተለያዩ ሀገራት በሕገ-ወጥ መንገዶች ወጥተው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ፤ 27 ሺሕ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማደረጉንም ገልጿል፡፡
#አሐዱ
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news