ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ እንደጻፉት
በሰሙነ ሕማማት ይህንን አድርጉ
እንኳን አደረሳችሁ
ሰሙነ ሕማማት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ቤዛ ሆኖ ተላልፎ መሰጠቱን የምናስታውስበት ሳምንት ነው።
ይህንን ምክንያት በማድረግ የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ሲመለከቱ ግራ የሚጋቡና ሥርዓተ አምልኮውን በሚገባ ከመከታተል ይልቅ ሥርዓት የጣሱ እየመሰላቸው የሚጨነቁ ስላሉ ልናደርገው የሚገባንን እጽፍላችኋለሁ።
1. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ ፊትንና መላ ሰውነትን በትዕምርተ መስቀል {በመስቀል ምልክት} ማማተብ አይከለከልም። ከካህን እጅ ቡራኬ አንቀበልም በካህኑ እጅ ያለውን መስቀል አንሳለምምና ማማተብም የለብንም በሚል ፍልስፍና ካልሆነ ማማተብ ክልክል ነው ተብሎ የተጻፈበት ቦታ የለምና።
2. የሚከለከል ጸሎት የሌለ መሆኑን አውቃችሁ ያስለመዳችሁትን ጸሎት በትጋት ጸልዩ። መሥዋዕት ካለመሠዋታችን ቅዳሴ ካለመቀደሳችን በቀር በዚህ ሳምንት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጀምሮእስከ ሊቃውንት ድርሳናት ድረስ በቤተ ክርስቲያን የማይጸለይ ጸሎት የለምና።
3. ሰላምታ መስጠት ከጸሎተ ሐሙስ ዕለት በቀር አልተከለከለም፤ እሱም ቢሆን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ሰላምታ ተላልፎ መሰጠቱን ለማስተዎስ እንጅ ሌላ የተለየ ምክንያት ስለሌለው በመርሳት ወይም በሌላ ከድፍረት በተለየ ምክንያት ሰላምታ ያቀረበላችሁን ሰው ልታስደነግጡና ትልቅ ኃጢአት እንደሠራ አድርጋችሁ ልታስጨንቁት አይገባም።
4. “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ” ብሎ መጻሕፍትን ማንበብ ወይም ሌላ ሥራን መጀመር ይቻላል። ስመ እግዚአብሔር መጥራት የምንከለከልበት ጊዜ መቸም የለምና።
5. የጌታችንን ሕማሙንና ሞቱን የሚያስታውሱ መጻሕፍትን በማንበብና በመስማት ጊዜአችንን መወሰን ይገባናል።
6. በዚህ ሳምንት ተድላ ደስታን ሲያደርጉ መገኘት ከአይሁድ ጋር እንደ መተባበር የሚያስቆጥር ስለሆነ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ ያማረውንና ጌጠኛውን ልብስ በመልበስ፣ ባልና ሚስት በምንጣፍ በመገናኘት እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ከምናደርጋቸው ተድላ ደስታዎች መራቅ ይገባናል። ቅዱሳን በዘመናቸው ሁሉ ባሰቡት ጊዜ የሚያስጨንቃቸውን የክርስቶስን መከራ እያሰብን ለጥቂት ጊዜም እንኳን ቢሆን የክርስቶስን መከራ በሰውነታችን ማሰብ ይገባናል።
የተቻለው እንደ ጴጥሮስ የራሱን ኃጢአት እያሰበ እንደ ማርያም መግደላዊት የክርስቶስን ሞት እያዘከረ ሊያለቅስ ይገባዋል።
በወዲያኛው ዓለም ከማልቀስ የሚያድነን ዛሬ የራሳችንን ኃጢአት አስበን የክርስቶስን ሞት አዘክረን የምናለቅሰው ለቅሶ ነው እንጅ ዛሬ ከተደሰትን ደስታችንን በዚህ ዓለም ማድረጋችን አይደለምን?
7. በተቻለን መጠን በቤተ ክርስቲያን መዋል ይገባናል፤ ሕማማተ መስቀልን የሚያስታውሱ መጻሕፍት የሚነበቡበት ሳምንት ስለሆነ ነው። ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት በቤተ ክርስቲያን መዋል እንኳን ባይቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ ሁናችሁ እየዋሻችሁ በሐሰት የከሰሱትን፣ እየቀማችሁ ልብሱን የገፈፉትን፣ ሰው እየደበደባችሁ በጅራፍ የገረፉትን፣ በወንድሞቻችሁና በእኅቶቻችሁ ላይ እየፈረዳችሁ በክርስቶስ ላይ የፈረዱበትን፣ በሰዎች ላይ እየተዘባበታችሁ የተዘባበቱበትን፣ በሳቅና በሽንገላ ሰውን እየሸነገላችሁ ሽንገላ በተሞላበት ሰላምታ ጌታውንና መምህሩን አሳልፎ የሰጠ ይሁዳን ልትመስሉ አይገባም።
ይልቁንም በአይሁድ እጅ ተላልፎ ቢሰጥም ንጹሓ ባሕርይ መሆኑን በማመን እስከ ቀራንዮ የተከተሉትን ደቀመዛሙርት ልትመስሉ ይገባል። እግራችሁ በመቅደሱ ውስጥ ባይቆምም ልባችሁን ከመቅደስ ልታወጡት አይገባም። እያዘናችሁ ባላችሁበት ቦታ ዋሉ።
8. በቤታችሁም ሆነ በቤተ ክርስቲያን አብዝታችሁ ስገዱ። ስለሁላችንም ቤዛ የሚሆን ክርስቶስ በፊታችን መስቀል ተሸክሞ ሲወድቅ እያያችሁት ትቆማላችሁን? አይሁድ ገፍተውት አንድ ጊዜ ወደ ምድር በወደቀ ጊዜ ለወደቀው መውደቅ ዘመናችንን ሙሉ ብንወድቅ ብንነሣ ውለታ መክፈል እንችል ይመስላችኋል?
ቅዱሳን ሳያቋርጡ ሲሰግዱ የሚኖሩት ክርስቶስ በፊታቸው በአይሁድ እጅ እየተገፋ መስቀሉን እንደተሸከመ ሲወድቅ በዓይነ ሕሊናቸው ስለሚያዩት ነው።
በስንክሳር ተጽፎ የምናገኘው ዜና ሞታቸው እየሰገዱ ሳሉ ሞት ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለይቶ እንደሚወስዳትና ለስገደት ታጥቀው እንደተንበረከኩ እንደሚገኙ ይነግረናል። የተሰቀለውን ክርስቶስን የሚያስብ ሰው ለሰውነቱ ዕረፍትን አይሻም።
9. ከሁሉም ሰው ጋር ፍቅርን አድርጉ። ሰውን ለመውደድ ምክንያት አታብጁ። ክርስቶስ አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን “ወዳጄ” ብሎ ሲጠራው አትሰሙትም?
እግዚአብሔርን አንተን ያለ ምክንያት እንደ ወደደህ አንተም ያለ ምክንያት ሰውን መውደድ ልመድ። ክርስቶስ አንተን ጠላቱ ሆነህ ሳለ ፍቅርን ካላጎደለብህ ለጠላትህ ፍቅርን አታጉድልበት።
ክርስቶስ ይሁዳን ‘’ወዳጀ’’ ብሎ ከጠራው አንተም ይሁዳዎችህን ወዳጀ ብለህ ጥራቸው። አውቃለሁ ጠላትን መውደድ መራራ ሐሞትን ከመጠጣት በላይ መራራ ነው። ነገር ግን እኔም ለይሁዳዎቻችን ፍቅርን እንስጥ ማለቴ መራራ ሐሞት የጠጣ ክርስቶስን እንድንመስለው ነው።
10. ለሁሉም መስጠት በምትችሉት መጠን ስጡ እንጅ አትቀበሉ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነውና በመስጠታችሁ ብፁዓን ተብለው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገቡት ትቆጠራላችሁ።
ምናልባትም የምትሰጡት ገንዘብ ባይኖራችሁ ገንዘብ ለሰጧችሁ ባለጠጎች የምትሰጡት ጸሎት ሊኖራችሁ ይገባል። ከምንጊዜውም የበለጠውን ስጦታ የተቀበልንበት ሳምንት መሆኑን እያሰባችሁ አንዳች የምትሰጡት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ስጦታ የሌላችሁ ባዶዎች እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።
ከሁሉ በላይ የሆነውን ስጦታ የጌታን ሥጋና ደም እነሆ ተቀብለናል።
ክርስቶስ መድኃኒነ መጽአ ወሐመ በእንቲአነ ወበሕማማቲሁ ቤዘወነ!
©️ስምዐኮነ መልአከ