💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 106 💙💙
▶️፩. ጦቢ.12፥18 ለመላእክት ምስጋና አይገባምን?
✔️መልስ፦ ለቅዱሳን መላእክት ምስጋና ይገባል። ለእነርሱ የሚገባው ምስጋና ግን የጸጋ ምስጋና ነው እንጂ የባሕርይ ምስጋና አይደለም። የባሕርይ ምስጋና የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። በባሕርይው ምስጉን እግዚአብሔር ብቻ ነውና።
▶️፪. ጦቢ.13፥16 መጽሐፈ ጦቢት የተጻፈው ከኢየሩሳሌም መታደስ በፊት ነው ማለት ነው?
✔️መልስ፦ አዎ። ገና እስራኤላውያን በምርኮ ሳሉ የተጻፈ መጽሐፍ ነው።
▶️፫. "ከነነዌ ውጣ ነቢዩ የተናገረው ነገር በግድ ይደረጋልና" ይላል (ጦቢ.14፥8)። ነነዌ የጠፋችው ከኢየሩሳሌም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ነው? ናቡከደነፆር የነነዌን ጥፋት ሰምቶ ደስ ያለው በምን ምክንያት ነው?
✔️መልስ፦ ነነዌ በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት እንደጠፋች ተገልጿል። ናቡከደነፆር የነነዌ ሰዎችን ይጠላ ስለነበር ነነዌ ስትጠፋ ተደስቷል።
▶️፬. መጽሐፈ ጦቢት ከ፷፮ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የለም። ለመሆኑ ይህን ሌሎች ፲፭ቱን ትተን ፷፮ ብቻ ማንበብ ተገቢ ነውን? ወይም ሁለቱንም መያዝና ማንበብ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ይፈቀዳል? ወይስ የተፈቀደልን ፹ አሐዱን ብቻ ነውን? ይህንን በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ቢያብራሩልን።
✔️መልስ፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና 81 ነው። ይኸውም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 2 በእንተ መጻሕፍት አምላካውያት ተብሎ ተገልጿል። ስለዚህ 81ዱንም መቀበልና ማንበብ ተገቢ ነው። በሁሉም የእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ እንዲሁም መግቦቱ ተገልጿልና።
▶️፭. ጦቢ.፲፬፥፬ ልጄ ወደ ሜዶን ሂድ ትጠፋ ዘንድ እንዳላት እያለ የተናገረውን ለልጁ ነገረው። ጦቢትና የዮናስ በአንድ ዘመን የነበሩ ናቸውን?
ቀጥሎ ጦቢ.፲፬፥፲፭ አባቱም እንደ ነገረው ሳይሞት የነነዌን ጥፋት ሰማ ሲል ምን ማለት ነው? የተማርነው ንስሓ እንደገቡና ከጥፋት እንደዳነች ነውና ግልፅ ቢያደርጉልን።
✔️መልስ፦ አዎ ጦቢትም ዮናስም በአንድ ዘመን በእስራኤል የምርኮ ዘመን የነበሩ ሰዎች ናቸው። የነነዌ ሰዎች ንስሓ በመግባታቸው ለጊዜው መከራው ርቆላቸው ነበር። በኋላ መልሰው ክፉ ሥራን በመሥራታቸው በሌላ ዘመን ጠፍተዋል።
▶️፮. ጦቢ.12፥19 "እኔ ግን ተገለጥሁላችሁ መልኬንም አያ ችሁ ከእናንተ ጋራ አልበላሁም አልጠጣሁም" ይላል። ጦቢ.6፥5 ላይ ደግሞ "ያም ልጅ መልአኩ እንዳዘዘው አደረገ ዓሣውንም ጠብሰው በሉ። ሁለቱ ሁሉ ገሥግሠው ሄደው ወደ በጣኔስ ደረሱ" ይላል። ሁለቱ አይጋጭም።
✔️መልስ፦ አይጋጭም። መልአኩ በላ መባሉ ምግብ ለባሕርይው የሚስማማው ሆኖ ወይም አስፈልጎት በላ ማለት አይደለም። ሥላሴ በአብርሃም ቤት በሉ እንደተባለው ያለ ነው። ይህም እሳት ቅቤ በላ እንደሚባለው ያለ ነው። በባሕርይው ምግብ ስለማይፈልግ አልበላሁም አልጠጣሁም አለ። በተገለጸበት አምሳል መብላቱን ሲያይ በላ አለ። እሳት ቅቤ በላ ሲባል መቼም ቅቤው ለእሳቱ ጥቅም ሰጠ ማለት አይደለም። ቅቤውን አቀለጠው አጠፋው ማለት ነው። ከዚህም መልአኩ በላ መባሉ የቀረበውን ምግብ የበላ መስሎ ቢታይም ለአካሉ ሳይዋሐደው አጠፋው ማለት ነው።
© በትረ ማርያም አበባው
✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ
https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።
🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw
https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።