ክፍል ፬
ቃለ እግዚአብሔርወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ዋነኛ ትምህርታችን ነው። ቅዱስ አትናቴዎስ በሃይማኖተ አበው እንደተናገረው ሥጋ መክበሩ ቃል ስለተዋሐደው ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ ክብር ሆኖት አይደለም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔር ነው። ይህም ማለት ቃለ አብ፣ ቃለ መንፈስ ቅዱስ ነው ማለታችን ነው። በአንድ ህልውና በአንድ ባሕርይ ለሚኖሩ ሦስቱ አካላት ቃላቸው እርሱ ነው። ይህ ቃል ከሰው፣ ከእንስሳት፣ ከመላእክት ቃል (ድምፅ) የተለየ ነው። እነዚህ ቃላት (ድምፆች) ዝርዋን ናቸው እንጂ አካላውያን አይደሉም። ቃለ እግዚአብሔር አአትሪኮን፣ አተርጋዎን፣ ቦርፎሪኮን ከሚባሉት ቃላት የተለየ ቃል ነው።
ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር የሰሙት ድምፅ እንኳ ዝርው ነው። አካላዊ ቃል የሚባለው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ነው። ከንባብ (ንግግር) የተለየ አካላዊ ቃል ነው። ይህ ቃል ሥጋ ሆነ። ይህም ማለት ረቂቁ አካለ ቃል ግዙፉን አካለ ሥጋ በተዋሕዶ ገንዘቡ አደረገው ማለታችን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር እየተመላለሰ ሲያስተምር ለሕዝቡ ጆሮ ይሰማ የነበረው ድምፅ ዝርው ስለሆነ አካላዊ አይደለም። ራሱ ክርስቶስ ግን አካላዊ ቃል ነው። እርሱ የተናገረው ንግግር ግን ከእርሱ ከአካላዊ ቃል የተገኘ ንግግር (ንባብ) ነው እንጂ ራሱ ንግግሩ አካላዊ አልነበረም።
ይቀጥላል