ቀን ታህሳስ 14/2017 ዓ.ም
በወቅታዊ ጉዳይ ከጣና ገላውዴዎስ ክ/ጦር የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል በርካታ የፈተና ስንክሳሮችን እያለፈ፣ የሴራ ድሮችን እየበጣጠሰ፣ በጽኑ አለት ላይ ራሱን እየተከለ በመጓዝ ላይ ይገኛል።
ትግላችን የሕዝባችን የኅልውናዉ ማረጋገጫ ተምኔቱ ነው፤ ትግላችን በጀግንነትና በአርበኝነት የቆሰሉና የተሰው ጓዶቻችንን አደራ የተሸከምንበት የደም መላሽነት መንገድ ነው፤ ትግላችን እውነትን፣ ፍትሕን፣ ነጻነትንና እኩልነትን መርኁ አድርጎ የሚጓዝ የዐይን ብሌናችን ነው።
በመሆኑም የሕዝባችን ቀጣይነት ማረጋገጫ፣ የታሪካችን፣ የባሕል የእምነታችን ማስቀጠያ ሐዲዳችን የሆነውን የኅልውና ትግል እንደ ነፍሳችን መጠበቅ ሕዝባዊ ብሎም ታሪካዊ ኃላፊነታችንም ግዴታችንም ነው።
ይህ ትግል ቅንጣት ታክል ስህተትን የማይፈቅድ፣ ወቅቱን፣ የፖለቲካ አሰላለፎችንና ስሁት እሳቤ ሸቃጮችንም ጭምር በትግሉ ሜዳ በሚገኙ ሐቀኛ ዐይነ-ንሥር ልሂቃን አማካይነት እየመረመርን መጓዝ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።
ትግሉ በተለያዩ ቀጠናዎች በጠላት ላይ ሁሉንአቀፍ ድልን እየተቀዳጀ በመጓዝ ላይ ቢሆንም በትግሉ ሜዳ በማወቅም ባለማወቅም የኅልውና፣ የፍትሕ፣ የነጻነትና የእኩልነት ትግላችንን የሚጎትቱ ጥቂት የማይባሉ አካላት መኖራቸውን በውል እንገነዘባለን።
የጣና ገላውዴዎስ ክፍለ ጦር እስካሁን ድረስ የትኛውም አደረጃጀት ውስጥ ሳይካተት ከውጭ ሆኖ የአደረጃጀቶችን አካሄድ እንዲሁም በመርኅ እና በሐቅ አታጋይነታቸው የቆሙትን ሲመረምር ቆይቷል።
ክፍለ ጦራችን ነገሮችን በውል ከመረመረ በኋላ ታህሳስ 12/2017 ዓ.ም የክ/ጦሩ እና የብርጌድ አመራሮች በተገኙበት ወቅታዊዉን የትግል ሂደት፣ ነባራዊዉን የፖለቲካ አሰላለፍ፣ የቀጠናውን የአደረጃጀቶች ቁመና በወጉ መርምሮ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዚህ መሠረት ክ/ጦራችን እስካሁን ከአደረጃጀቶች ውጭ መቆየቱ ዙሪያ ገባውን ለመመልከት እድል በፈጠረልን መሠረት በመርኅና በሐቅ ታግሎ አታጋይነቱ በአርበኛ ባዬ ቀናው የሚመራው "የአማራ ፋኖ በጎንደርን" ምርጫችን አድርገን ወደተቋሙ ለመግባት በሙሉ ድምጽ አጽድቀን መግባታችንን ለመግለጽ እንወዳለን።
ከዚህ በተጨማሪ የአማራ ፋኖ በጎንደር መሪ አርበኛ ባዬ ቀናው እና የአማራ ፋኖ ጎንደር እዝ መሪ አርበኛ ሐብቴ ወልዴ እንዲሁም የበላይ ጠባቂ አባት አርበኞች የጎንደር ሁለቱን ግዙፍ አደረጃጀቶች ወደአንድ የትግል መስመር ለማምጣት የሄዱበትን መንገድ በሙሉ ልባችን እንደምንደግፍ እየገለጽን ለተግባራዊነቱም ከትግል ጓዶቻችን ጋር ሆነን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያለንን ጽኑ አቋም ማስገንዘብ እንፈልጋለን።
ስለሆነም የኅልውና ትግላችን የፖለቲካ ደላሎችንና ቁማርተኞችን አጥብቆ ይጠየፋል፤ ይታገላቸዋልም። የኅልውና ትግላችን ፉክክርና ውድድርን ሳይሆን ትብብርን ተደጋግፎትን፣ መለያየትን ሳይሆን በአንድ ተቋም ውስጥ ሆኖ መታገልን የሚሻ በመሆኑ የጎንደር አርበኞች የጀመሩትን የአንድነት መንገድ ለማደናቀፍ መጓዝ ታሪክ ይቅር የማይለው ድርጊት ስለሆነ ሁሉም ታጋይ ለአንድነት ቦታ እንዲሠጥ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም የሚዲያ አካላት ከዛሬ ጀምሮ ሁለቱ ግዙፍ እዞች አንድ የተቋም ስያሜ እስከሚይዙ ድረስ የአማራ ፋኖ በጎንደር ጣና ገላውዴዎስ ክ/ጦር ብላችሁ እንድትዘግቡ እንጠይቃለን።
ትግላችን በክንዳችን
ትግላችን በአንድነታችን
ትግላችን በሐቀኝነታችን
የጣና ገላውዴዎስ ክፍለ ጦር
ጎንደር፣ አማራ፣ ኢትዮጵያ
https://t.me/fanozgonder