ስለ ውርስ ይርጋ የተሰጠ ውሳኔ አግባብነት /የሕግ ጉዳይ/
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 243973 ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአመልካች እነ ወ/ሮ ጠይባ መሐመድ እና በተጠሪ አብዱልዋሀብ መሐመድ መካከል በሰጠው ውሳኔ ወራሽነት ማስረጃ ይዞ ወይም አሳውጆ ነገር ግን ውርሱ ሳይጣራ ወይም ንብረቱን በእጁ ሳያስገባ ሦስት ዓመት ካለፈ ውርስ የመካፈል መብቱ ያልፍበታል ወይም በይርጋ ቀሪ ይሆናል ሲል ወስኗል። ይህ ውሳኔ ምን ያህል ተገቢ ነው?
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲጽፍ በትንታኔው መጨረሻ ላይ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000 /1/ መሠረት የወራሽነት ክስ በሦስት ዓመት ውስጥ ካልቀረበ ተቀባይነት እንደሌለው አስቀምጧል። ሦስት ዓመቱ የሚቆጠረው ከመቼ ጀምሮ ነው ለሚለው ጥያቄ ከሳሹ ሁለት ነገሮችን ባወቀ በሦስት ዓመት ውስጥ መክሰስ አለበት ብሏል። እነኚህም 1ኛ/. እሱ እራሱ የወራሽነት መብት ያለው መሆኑን እና 2ኛ/. ንብረቱ በሌላ ሰው ማለትም በተከሳሹ መያዙን ናቸው። እነኚህን ባወቀ በሦስት ዓመት መክሰስ አለበት ብሏል። በዚህ መሠረት ውርስ ሳይጣራ ወራሽነት መብቱን አሳውጆ ብቻ ንብረቱን በእጁ ያላስገባ ሰው ከሦስት ዓመት በኋላ አካፍሉኝ ብሎ መጠየቅ አይችልም የሚል ውሳኔ ሰጥቷል።
ይህንን በሚመለከት የፍትሐብሔር ሕጉ በቁጥር 999 የወራሽነት ጥያቄ ክስ ምን እንደሆነ ትርጉም ይሰጠዋል። የወራሽነት ጥያቄ ክስ ማለት እውነተኛው ወራሽ በሌላ ዋጋ ያለው የወራሽነት ማስረጃ ሳይኖረው ውርሱን ወይም ከውርሱ አንዱን ክፍል በእጁ ባደረገ ሰው ላይ ወራሽነቱ እንዲታወቅለትና ንብረቶቹን እንዲመልስ የሚያቀርብበት ክስ ነው። የወራሽነት ጥያቄ ክስን በሚመለከት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 998 /1/ እንዲህ ዓይነት ክስ በቀረበላቸው ጊዜ ዳኞች ያላግባብ የተሰጠውን የወራሽነት ምሥክር ወረቀት ሊሠርዙት እንደሚችሉ ይደነግጋል። ስለዚህ ሁለቱን አንቀጾች አንድ ላይ ስናገናዝብ የወራሽነት ጥያቄ ክስ ማለት ያለ አግባብ ወራሽነቱን አሳውጆ የውርስ ሀብት የያዘ ሰው የምሥክር ወረቀቱ እንዲሠረዝበትና ንብረቱን እንዲመልስ እውነተኛው ወራሽ የሚያቀርበው ክስ ብቻ ነው እንጂ ማንኛውም የውርስ ልካፈል ጥያቄ አይደለም። ሰበር ፍርድ ቤቱ ግን ማንኛውንም የውርስ አካፍሉኝ ጥያቄን የወራሽነት ጥያቄ ክስ አድርጎ መውሰዱ ትክክለኛ አይደለም። ውርስ ሳይጣራ የሚቀርብ ማናቸውም የውርስ ልካፈል ጥያቄ በሦስት ዓመት ውስጥ መቅረብ አለበት የተባለው የተሳሳተ ነው።
ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ የጀርመንን ሕግ መሠረት በማድረግ የተቀረጸ መሆኑን ካተተ በኋላ የኢትዮጵያ ሕግ የሚዛመደው ከእንግሊዝ ሕግ ጋር ነው በማለት የደረሰበት ድምዳሜም አሳማኝ አይደለም። በዓለም ላይ ሦስት ዓይነት የውርስ ማስተላለፊያ መንገዶች መኖራቸውን አትቶ እነኚህም 1ኛ/. ሞትን ተከትሎ በቀጥታ ለወራሾች የሚተላለፍበት፣ 2ኛ/. የወራሾች ፈቃደኝነት ተረጋግጦ የሚተላለፍበት እና 3ኛ/. ውርሱ እስኪጣራ ድረስ ንብረቱ በሌላ ሰው እጅ ቆይቶ የማጣራቱ ሂደት ካለቀ በኋላ ለወራሾቹ የሚዘዋወርበት መሆኑን ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ የጀርመኑ የሚከተለው ሞትን ተከትሎ ወዲያውኑ ለወራሾች የሚተላለፍበትን የመጀመሪያውን ሥርዓት ነው ሲል አስቀምጧል። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ግን የሚዛመደው ከሦስተኛው ዓይነት የእንግሊዝ ሕግ ጽንሰ ሀሳብ ጋር ነው ብሏል። ለዚህም ሰፋ ያለ ትንታኔ አቅርቧል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ የጀርመንን መሠረት በማድረግ የተቀረጸ ሆኖ ሳለ ከዚያ የተለየ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም። እንዲያውም የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 826 /1/ አንድ ሰው የሞተ እንደሆነ በሞተበት ጊዜ ዋናው መኖሪያ ስፍራው በሆነ ቦታ የሟቹ ውርስ እንደሚከፈት ይደነግጋል። ከዚህ የምንረዳው በኢትዮጵያ ውርስ የሚከፈተው በሌላ የሽግግር ሥርዓት ሳይሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሟች እንደሞተ ወዲያውኑ በሚኖርበት ቤት መሆኑን ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ የሚቀራረበው ከዛው ከተወሰዱበት ከጀርመን እንጂ ከእንግሊዝ ሕግ ጋር ሊሆን አይችልም። ከዚህ ጋር በተጣጣመ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1124 /1/ ውርስ ከተከፈተ በኋላ አንድ ወራሽ በውርስ የሚያገኘውን መብት በከፊል ወይም በሙሉ ለሌላ አሳልፎ መስጠት ይችላል ይላል። አንቀጽ 826 እና 1124 /1/ አንድ ላይ ስናናብባቸው አንድ ሰው ሲሞት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውርሱ እንደሚከፈት፣ ወራሹም ወዲያውኑ (ከማሳወጁም በፊት) በውርስ መብት እንደሚያገኝ እና ይህንንም ለሌላ ሰው ማስተላለፍ እንደሚችል ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ሕግ ውርሱ ለወራሾች የሚተላለፈው ሞትን ተከትሎ በቀጥታ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ማንኛውም ወራሽ በሦስት ዓመት ውስጥ ካልጠየቀ መብቱን ያጣል የሚለው አተረጓጎም ትክክል አይደለም። በሕግ የተገኘ መብት ለሌላ እስካልተላለፈ ድረስ እንዲሁ ሊጠፋ የሚችል ነገርም አይደለም። ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ድጋሚ በደንብ እየታየ ሊስተካከል ይገባል።
እንዲህ ዓይነት አተረጓጎም በሀገር ላይ እና በሕብረተሰቡ አኗኗርና ባህል ላይ የከፋ ውጤት ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ሊስተዋል ይገባል። ልጆች ከወላጆቻቸው መካከል አንዳቸው ሲሞቱ የቀረውን አስቀምጦ በመጦር ፈንታ ሦስት ዓመት ሳያልፍ መብቴን ልጠየቅ በሚል ወላጆቻቸውን በስተእርጅና እንዲከሱ፣ ንብረት እንዲካፈሉ፣ ለእንግልት እንዲዳርጉ ያደርጋል። በቤተሰብ መካከል መተማመንን የሚያጠፋም ነው። ንፁሀንን የሚጎዳና የውርስ ሀብት አላካፍልም ብለው ለሚክዱና በሸፍጥ ለሚከራከሩ የተሻለ ዕድል የሚሰጥም ነው። ስለዚህ አሁን ሰበሩ ፍርድ ቤት በዚህ ጥያቄ ላይ ያለውን ጉራማይሌ አተረጓጎም አንድ ወጥ ለማድረግ መሥራቱ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ይህንን አተረጓጎሙን በቶሎ ሊያስተካክለውና ሊያዳብረው ይገባል። ዩኒቨርስቲዎችና የሕግ ሙያ ማኅበራትም የተለያየ ዐውደ ጥናቶችንና ኮንፍረንሶችን ከፍርድ ቤቱ ጥናትና ምርምር ክፍል ጋር በመተባበር ሊያዘጋጁና ሊያግዙ ይገባል።
በጠበቃ ታምራት ኪዳነማርያም JOIN ስለ-ህግ ABOUT-LAW
Telegram- https://telegram.me/ethiolawblog
Facebook- https://m.facebook.com/aboutlawlegalservice
LinkedIn- https://www.linkedin.com/company/aboutethiopian-law