አንደኛው ቡድን ወስጥ ያሉ ተሳታፊዎች ይህን የጽሁፍ መልመጃ ያለ ምንም እገዛ አእምሯቸውን ብቻ በመጠቀም እንዲጽፉ፤ ሁለተኛው ቡድን ወስጥ ያሉት Google የተሰኘውን የኢንተርኔት መረጃ መፈለጊያ ድረገጽ በመጠቀም እንዲጽፉ፤ ሶስተኛው ቡድን ውስጥ ያሉት ደግሞ ቻትጂፒትን በመጠቀም እንዲጸፉ ተደረገ፡፡
ቡድኖቹ መልመጃውን በሚሰሩ ጊዜ አጥኚዎቹ ጭንቅላት ላይ የሚገጠም EEG የሚባል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተፈታኞቹ አእምሮ ውስጥ የሚካሄደውን ኤሌክትሪካዊ እንቅስቃሴ ተከታተሉ፡፡
ከሶስቱ ቡድኖች መካከል ቻትጂፒትን ተጠቅመው የጽሁፍ መልመጃውን የሰሩ ተፈታኞች በአእምሯቸው ውስጥ በጣም አነስተኛ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በመልመጃው ላይም ደካማ ውጤት ነበር ያስመዘገቡት፡፡ በወራት ጊዜ ውስጥ ሲታይ የዚህ ቡድን ተሳታፊዎች በእያንዳንዱ መልመጃ ላይ እየሰነፉ ሄደው በቀጥታ እየገለበጡ መሄዳቸውን ጥናቱ ይገልጻል፡፡
ከሌሎች ቡድኖች አንፃር ቻትጂፒቲን የተጠቀሙት የጥናቱ ተሳታፊዎች ተመሳሳይና አዲስ መንገድን ያልተከተለ እንዲሁም ተመሳሳይ ሃሳቦችና አገላለፆች የሞሉት መጣጥፍ መጻፋቸው ተነግሯል፡፡
ከዚህ በተለየ አእምሯቸውን ብቻ በመጠቀም መጣጥፉን የፃፉ ተሳታፊዎች መልመጃውን በሚሰሩበት ጊዜ በአእምሯቸው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እንደታየ ተገልጿል፡፡ በተለይ ፈጠራዊ ሃሳብ እንዲመነጭ የሚያደርጉ እና ከትውስታ አቅም ጋር የሚገናኙ የአእምሮ ክፍሎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳሳዩ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ጉግልን ብቻ እንዲጠቀም የተፈቀደለት ቡድን ተሳታፊዎችም ከፍተኛ የአእምሮ ውስጥ እንቅስቃሴ አሳይተዋል ቢባልም፣ ከሁሉም የበለጠውን ያዩት ግን ያለምንም እገዛ አእምሮዋቸውን ብቻ ተጠቅመው መልመጃውን የሰሩት ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ መሳሪያዎች በተለይ በወጣቶች ላይ የመማር አቅምን እንደሚጎዱ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
AI እና የስራ ተነሳሽነት — የሃርቫርድ ጥናትከMIT ጥናት አንድ ወር ገደማ ቀደም ብሎ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተሰራ ሌላ ጥናት ጀነሬቲቭ ኤአይ ወይም ይዘት አመንጪ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ መሳሪያዎች ሰዎች በስራቸው ላይ ውጤታማ ወይም ታታሪ (ፕሮዳክቲቭ) እንዲሆኑ እንደሚያግዙ አመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መሳሪያዎች የስራ ተነሳሽነት እንደሚገድሉ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ለዚህኛው ጥናት ከ3500 በላይ ተሳታፊዎች ተመልምለው በእውነተኛው አለም የሚሰሩ ስራ ተኮር መልመጃዎችን በኤአይ እና ያለ ኤአይ እንዲሰሩ ታዘው ነበር፡፡ መልመጃዎቹም ለሶሻል ሚዲያ የሚሆን ጽሁፍ መጻፍ፣ ሃሳቦችን ማመንጨት፣ የኢሜይል መልዕክቶችን ማርቀቅን የመሳሰሉ ነበሩ፡፡ ከዚያም በስራው ላይ ያሳዩትን ብቃት እንዲሁም ስነልቦናዊ የሆኑ የመነሳሳት እና የመሰልቸት ጉዳዮችን አጥኚዎቹ ገመገሙ፡፡
በውጤቱም፦ ሁለት ተቃራኒ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በአንድ በኩል ተሳታፊዎቹ ጀነሬቲቭ ኤአይን በመጠቀማቸው የአጭር ጊዜ የስራ አፈጻጸማቸው ከፍ ብሏል፡፡ በኤአይ አማካኝነት የተሰሩት ስራዎች ረዘም ያሉ፣ ተንተን ያሉ እንዲሁም አዎንታዊ ቋንቋዎች የሞሏቸው እንደሆነ ታይቷል፡፡
በሌላ በኩል ግን ኤአይን መጠቀም ከብቃት ጋር የተገናኙት ጥቅሞቹ እንዳሉ ሆኖ ስነልቦናዊ ጉዳቶች እንዳሉት ጥናቱ ያሳያል፡፡ ኤአይን በመጠቀም ስራ የሰሩ ተሳታፊዎች ያለ ኤአይ ሌላ ስራ እንዲሰሩ ሲታዘዙ ተነሳሽነታቸው እንደቀነሰና የመሰላቸት ባህሪ እንዳሳዩ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ተነሳሽነት በ11% ሲቀንስ መሰላቸት ደግሞ በ20% ጨምሯል ይላል ጥናቱ፡፡
ከላይ ካሉት ውጤቶች በተቃራኒ ከመነሻው እስከ መጨረሻው ምንም የኤአይ እገዛ ሳይጠቀሙ መልመጃውን የሰሩ ተሳታፊዎች ያልተለዋወጠ የስነልቦና ሁኔታ እንዳሳዩ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ይህ የሃርቫርድ ጥናት የኤአይን ከስራ ብቃት ጋር የተገናኙ ጥቅሞች ለማሳደግ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶቹን ደግሞ ለመቀነስ በተለይ ቀጣሪ ድርጅቶች ቢተገብሯቸው ያላቸውን ጥቆማዎች ሰጥቷል፡፡
አንደኛ፦ የኤአይን እና የሰዎችን ድርሻ መደባለቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ኤአይን ስራ ለመጀመር እና መነሻ ሃሳብ ለማመንጨት ብቻ በመጠቀም ከዚያ በኋላ ሰዎች የራሳቸውን ፈጠራዎች እንዲያክሉ እና እንዲያስፋፉት ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛ፦ ኤአይ ላይ ያለው ጥገኝነት የሚያመጣውን ተጽእኖ ለመቀነስ ሰራተኞች በራሳቸው ያለምንም የኤአይ እገዛ የሚሰሯቸውን ስራዎች በመስጠት ተጽእኖውን ማመጣጠን እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡
ሶስተኛ፦ ኤአይን በስራ ቦታ መጠቀምን በተመለከተ ግልጽነት ማስፈን አንዱ መፍትሄ ነው ተብሏል፡፡ ሰዎች ኤአይ ሁሉን መስራት እንደሚችል ሲያስቡ ራሳቸውን ከስራው የመነጠል አዝማሚያ ያሳያሉ፤ ስለዚህ ስለ ኤአይ አጠቃቀም ግልጽ በመሆን የኤአይ ሚና የትኛው የሰዎቹ ሚና የትኛው እንደሆነ በማሳወቅ ሰዎች ባለቤትነት እንዲሰማቸው ማድረግ እንደሚጠቅም ተገልጿል፡፡
አራተኛው መፍትሄ፦ ድርጅቶች በኤአይ እና በሰዎች የሚሰሩ ስራዎችን በማቀያየር የስራ ብቃትን ጠብቀው የኤአይ ጥገኝነት የሚያመጣውን የስነ ልቦና ጫና መቀነስ ይቻላል፡፡ ተመሳሳይ ስራዎችን በአንድ ላይ ከማከማቸት ይልቅ ኤአይ የሚጠይቁትን ኤአይ ከማይጠይቁት ጋር አንዱ ሌላውን እንዲከተል ማድረግ ይቻላል፡፡
በመጨረሻ ጥናቱ የጠቆመው መፍትሄ፦ ኤአይ መሳሪያዎች ላይ ከልክ ያለፈ ጥገኝነት እንዳይኖር ድርጅቶች ለሰራተኞቻቸው ኤአይን ትርጉም ባለው መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ስልጠና መስጠት አለባቸው የሚል ነው፡፡
✍ Transit Radio
https://t.me/infoTech_et