የቀጥበሬ የዒልምና የዒባዳ ማዕከል መሥራች ሸኽ ዒሳ ሀምዛ ይባላሉ:: ከ1877-1940 ለ63 ዓመታት የኖሩ 0ሊምና ሙጃሂድ ናቸዉ:: ሁለንተናዊ ስብዕና እንደነበራቸዉ ይነገራል:: ጥልቅ የሸሪዐ ዕዉቀት አስደማሚ የዳዕዋ ጥበብ ግሩም ዲፕሎማሲ፣ የተዋጣላቸዉ የጦር አበጋዝ ብርቱ የልማት ሰዉ : መሳጭ የዒባዳና የዚክር አርበኛ…" በመላዉ የጉራጌ ማሕበረሰብ ጥልቀት ያለዉ ዘመን ተሻጋሪ ተጽእኖ ማሳደር ችለዋል ።ለአዲስ አበባ :ለሀረር:ለጎጃም:ቡታጅራ:ቢደራ... ሙስሊሞች የማይረሳ ዉለታ ዉለዋል።
የአዲስአበባ እንብርት በሆነዉ ፒያሳ ላይ የተሰየመዉን ኑር (በኒን) መስጂድ ዘወትር እሰግድበታለሁ። ከመላ ሀገራችን በአራቱም አቅጣጫዎች የሚመጡ ሙስሊሞችም ልክ እንደኔዉ ይገለገሉበታል። ግና ለዚህ ተቋም ምስረታና ህልዉና ሸሕ ዒሳ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ስንቶቻችን እናስበዋለን? ከአዲስ አበባ-ጎንደር መስመር በየብስ የተጓዘ የአባይን በረሀ እንደጨረሰ ከደጀን ከተማ አፋፍ ላይ አንድ ግዙፍ መስጊድ ከፊት ለፊቱ ይሰደራል። የዚያ መስጊድ መስራች ሸኽ ዒሳናቸዉ፡፡ ሸኽ ዒሳ በአካባቢዉ እንዳይቀበር ይከለከል ለነበረዉ የደጀን ከተማ ሙስሊም ማህበረሰብ የመቀበሪያ ሥፍራ አስገኝተዋል።ይህን ሁሉ ያደረጉት በግዞት በሄዱበት ነዉ።
ሸኽ ዒሳ በተቋማት ምሥረታ ላይ ብርቱ ናቸዉ። በሄዱባቸዉ አካባቢዎች ሁሉ ቀድመዉ የሚያከናዉኑት ተግባር የዒልምና የተርቢያ ማዕከላትን መመሥረት ነበር። የሸሪዐ ፍ/ቤቶች እንዲጠናከሩ ሠርተዋል። በመብት ትግሉም የተካኑ ናቸዉ።ሙስሊሞች የሀይማኖት አልባሳትን በተለይም ኩፍየታቸዉን በየትኛዉም ቦታ መልበስ ይችሉ ዘንድ በብርቱዉ ተፋልመዋል።የሀገራችንን ባንዴራ የያዘ ባለ 5 ኮከብ ኮፍያ በማሠራትም ኢትዮጵያዊነትንና እስልምናን አብሮ ማስኬድ እንደሚቻል ለሚመለከተዉ ሁሉ ትምሀርት ሰጥተዋል።
ለዘመናዊ ትምህርት የነበራቸዉ ምልከታ ዘመን ቀደም ነበር። ሙስሊሙ ለትምህርት የነበረዉን አሉታዊ አመለካከት ለማስወገድ ብርቱ ትግል አድርገዋል። የትምሀርት ተቋማት ከመመሥረት በተጓዳኝ ክርስቲያን መምህራን ከዛዉያቸዉ ድረስ በመሄድ ለደረሶቻቸዉ እንዲያስተምሩ አድርገዋል።
የቀጥበሬ የዒልም ማዕከል የተመሠረተዉ በ1900 ሲሆን ያኔ የሸኽ ዒሳ ዕድሜ 23 ነበር። በዚ ዕድሜ ያን ያህል ዘላቂ የዒልም ተቋም መመሥረት መቻል እንደተአምር የሚቆጠር ነዉ። ከልጅነት አንስቶ ለታላቅ ተልዕኮ ራሳቸዉን ያጩ ድንቅ ሰዉ።ረ.ዐ
የዲን ዕዉቀት የጀመሩት በ12 ዓመት ዕድሚያቸዉ ማለትም በ1889 ነበር። ለ11 ዓመታት ሲቀሩና በተርቢያ ሲታነጹ ቆይተዉ አሁን ማዕከላቸዉን ወደመሠረቱበት ቦታ በ1900 ተመለሱ፡፡ ሸኻቸዉ እጅግ ሲበዛ ታላቅ ነበሩ።የዳና የዒልም ማዕከል መሥራችና በኢትዮጵያ የዒልምና የተርቢያ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ ያላቸዉ ሸኽ አህመድ አደም (ጻንዩል አወል)። የኚህ ሰዉ ተማሪ መሆን መታደል ነዉ፡፡ ሸኽ ዒሳ ይህን ዕድል አግኝተዉ በአግባቡ ተጠቀሙበት። ታላቅ ሰዉም ሆኑ።ሸኽ ዒሳ አንድ ነገር በእጅጉ ያሳስባቸዉ ነበር፡፡ የሙስሊሞች አንድነት በመሆኑ ማህተማቸዉ የሚከተለዉ የቁርአን መልዕክት የሠፈረበት ነበር።
واعتصموا بحبل الله جميعا ولا تفرقوا
‹‹የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ። አትለያዩም።>> አል ኢምራን 103
ዳኖች ሸኽ ዒሳን ‹‹ያለለት›› በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸዉ ነበር ይባላል፡፡ እንደማለት ነው።በእርግጥም ለአሥሮች ዓመታት ምናልባትም ለመቶዎች ዓመታት የሚዘልቅ ተጽእኖ ማሳደር የቻሉ ዕድለኛ ናቸዉ፡፡
ሐሰን ታጁ (የሐሳብ ጠብታዎች )
https://t.me/joinchat/U4q9OHoSPqgy3teR