👉 ለሀገር ድህነትና ኋላ ቀርነት ኢስላም ተጠያቂ አይደለም ።
የአንድ ሀገር እድገትና ውድቀት የሚለካው ያ ሀገር በሚከተለው ፖሊሲ ነው ። ፖሊሲው ጤናማና ዜጎችን ስራ ወዳድና ምርታማ የሚያደርግ ከምዝበራና ባቋራጭ የመበልፀግ ፍላጎት የፀዳ ትውል መቅረፅ የቻለ ከሆነ ሀገር ማደግ ይችላል ።
የኢስላምን አስተምሮን ብንመለከት የሰው ልጅ በእጁ ማደር እንዳለበት ፣ በሚሰራ ጊዜ ስራውን ማጥራትና በአግባቡ ሀላፈነቱን መወጣት እንዳለበት አበክሮ ያወሳል ። ጉበኝነትን ፣ አስመሳይነትን ፣ ሌብነትን ፣ አለባብሶ ማለፍን ፣ የዛሬን ስራ ለነገ ማሳደርን ያወግዛል ። ከዚህ በላይ በጣም ትኩረት ሰጥቶ የሚያስተምረው ባለ መብቃቃትንና የሌሎችን አለመመኘትን ነው ።
ግብይትን አስመልክቶ በሰው ልጅ የህይወት ታሪክ አምሳያ የሌላቸው ረቂቅ የሆኑ ህግጋቶችን ያስቀምጣል ። ከእነዚህ ውስጥ እንደማሳያ የሚከተሉትን እንይ : –
– ስፍርና ሚዛንን መጠበቅ
– በእጅ ያልገባን ነገር መሸጥ መከልከል
– አየር ባየር የሚባልን ሽያጭ መከልከል
– ማታለልን መከልከል
– ገበሬ ምርቱን ወደ ገበያ በሚያመጣ ጊዜ
መንገድ ጠብቆ መግዛትን መከልከል
– ማንኛውንም ህዝብ የሚጠቀምበትን እቃ
( መጋዘን ) አከማችቶ ዋጋ ለመጨመር የለም ማለትን መከልከል የሚሉት ይገኙበታል ።
እነዚህ የኢስላም አስተምሮዎች ተግባራዊ የሆኑባት ሳውዲ አረቢያ የደረሰችበት ደረጃ የኢስላም አስተምሮ ለሀገር እድገት ያለው ሚና ትልቅ ማሳያ ነው ።
ሙስሊሞች ትክክለኛ እስልምናቸው እንዳያውቁና ልማዳዊ አምልኮን አጎልብተው ለስሜታቸውና ዝንባሌያቸው ያደሩ ኋላ ቀር እንዲሆኑ በሚደረግባት ዐለም ለሀገር ውድቀት እስልምናን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይደለም ።
ወደ ኋላ መለስ ብለን የታሪክ መዛግብትን ብናይ ሙስሊሞች በትክክለኛው የኢስላም አስተምሮ ሀገር በመሩበት ዘመን የት ደርሰው እንደነበር ማወቅ እንችላለን ። ከነብዩ ዘመን አንስቶ የአቡ በከር ፣ የዑመር ፣ የዑስማንና ዐልይ እንዲሁም የመጀመሪያዎቹ የአመዊዮች ስርወ መንግስት ዘመናትን ታሪክ ማወቅ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው ።
የምእራቡ አለም ከኢስላም ሊቃውንቶች የወሰዷቸው ቀመሮች ለብልፅግናቸው መሰረት መሆኑን የፃፈው ጀርመናዊው ዘይጝሪድ ሆንካ
" ሸምሱል ዐረብ ( ኢስላም) ተስጠዕ ዓላ አልጘርብ " በሚል ወደ ዐረብኛ በተተረጎመው መፅሐፉ ላይ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ አስፍሮታል ። ይህ ግለሰብ ምእራባዊያኖች እስልምናን ለመምታት የእስልምናን አስተምሮ እንዲያጠኑ የቤት ስራ ከሰጡዋቸው ግለሰቦች አንዱ ነበር ። የኢስላምን አስተምሮ ሲያጠና ከቆየ በኋላ ምእራቦቹ የሚጠቀሙባቸው ብዙ ቀመሮች የኢስላም ሊቃውንቶች ውጤት መሆናቸውና አብዛኛው የኢስላም አስተምሮ ለእድገታቸው ምክንያት መሆኑን ሲያይ በወቅቱ ትኩረቱ በዓረቡ ዐለም ስለነበርና ኢስላምን የሚያውቀው በእነርሱ በመሆኑ መፅሐፉን ከላይ በጠቀስነው ርእስ ፃፈው ። የርእሱ ትርጉም ( የዐረቡ ( የእስልምና) ብርሃን በአውሮፓ ሲፈነጥቅ ) የሚል ነው ።
ምእራባዊያን ከእስልምና አስተምሮ ወስደው መበልፀጋቸው ባልተጠላ ነበር ። ነገር ግን እነዚህ አካላት ከእነርሱ መበልፀግ ጎን ለጎን የኢስላሙ ዐለም ኋላ ቀር መሆን አለበት ብለው ከአስተምሮ ርቆ ቀብር አምላኪ እንዲሆንና የኢስላምን አስተምሮ ሳይሆን ስሜቱንና ዝንባሌውን እንዲከተል ባጀት መድበው የሰው ሀይል አሰማርተው መስራታቸው ነው ። እነዚህ አካላት ለዚህ እኩይ ተግባራቸው የሚያሰማሩዋቸው አካላት ዋነኛ ስራቸው ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ የእነሱን በመርዝ የተለወሰ አመለካከት የሚያራምድ መመልመል ነው ። በአሁኑ ሰአት አብዛኛው ሙስሊም ማህበረሰብ በእነዚህ የምእራባዊያን ሴራ መረብ የተተበተበ ነው ።
ታዲያ በምን ሚዛን ነው በዚህ አይነት መረብ የተተበተበ ሙስሊም ማህበረሰብ ባለበትና በምእራቡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የአለም መዘወሪያ ፖሊሲ በሚመራ ሀገር ላይ ለሚደርስ ኋላ ቀርነትና ድህነት ኢስላም ተጠያቂ የሚሆነው ? በምንም መመዘኛ ሊሆን አይችልም ። ነገር ግን ሙስሊሞች በየትኛውም ተፅኖ ስር ቢሆኑም የኢስላምን አስተምሮ መርህ በማድረግ ምርታማ በመሆን የተፅኖውን ካባ አውልቀው በመጣል ማንነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ።
ለዚህ የመጀመሪያው እርምጃ ኢስላም ማለት እመን ትድናለህ በሚል መርህ ሙስሊሞችን ያልከረቸመ መሆኑን በመረዳትና ኢስላም ማለት ማመን ፣ መመስከርና መተግበር ነው የሚል የህይወት መመሪያ መሆኑን አውቆ ለተግባራዊነቱ መዘጋጀት ነው ።
የኢስላም አስተምሮ መለኮታዊ የህይወት መመሪያ እንጂ spiritual cocept ( መንፈሳዊ ሀሳብ ) ላይ ብቻ የተገደበ ቁንፅል መርህ አይደለም ። በመሆኑም ኢስላምን አለመግደል ፣ አለመስረቅ በሚል መንፈሳዊ እምነት ብቻ ገድቦ ለመግለፅ መሞከር ተቀባይነት የሌለው ሙከራ ነው ። በኢስላም አስተምሮና በሙስሊሞች ዐቂዳ ላይ የሚደረገው ዘመቻ እየረቀቀና መልኩን እየቀየረ ሁሌም የሚቀጥል መሆኑን ሙስሊሞች አውቀው ዲናቸውን ሊገነዘቡና ሊጠብቁ ግድ ይላቸዋል ።
https://t.me/bahruteka