''...ነፍሰ-ጡሯ የፊንሐስ ሚስት...''
ሰሞኑን አንዳች ሥራ ጀምሬ ወትሮ እንደማደርገው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ የጥናት ጊዜዬን ለመከወን እጅግ ተቸግሬ ነበር። ያው ሙሉ በሙሉ ጥናቴን ባላቆምም እንደበፊቱ ሰፊ ሰዓት የማንበቡ እና የማሰላሰሉ ዝንባሌዬ ርቆኛል። ሆኖም ጌታ እረድቶኝ በማገኛት ጥቂት ጊዜ ከአባቴ የተካፈልኩትን ወዳጆቼን ላጋራችሁ ሻትሁ።
ዛሬስ ምን ሊለኝ ይሁን በሚል አይነት የገጉት መንፈስ የናፈቀኝን አምላክ ቁም-ነገር ልካፈል የማጥኛ ጠረጴዛዬ ዘንድ ሰፈርሁ። በአንዲት ቅፅበትም የመከራ ዶፍ የዘነበባትን አንዲት ሴት ተጨባበጥኩኝ። ይህች ሴት ነፍሰ-ጡሯ የፊንሐስ ሚስት ነች። የነፍሰ-ጡር'ነቷ ወር ይነጉዳል። የምትወልድበትም ዘጠነኛው ወር እደጇን እያንኳኳ ነው።
ይህ አይነት ጊዜ ለሴት ልጅ ምን ያክል የጭንቅ ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ ለሴቲቱ የቤተሰቦቿ አጠገብ መሆን ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ሆኖም በዚህ ጊዜ ከሚያበረታ ድምጽ ይልቅ አጥንት የሚሰብር መርዶ ይደርሳታል።(1ሳሙ:-4v19) የእግዚአብሔር ታቦት መማረኩ፣ የዐማቷ እና የባሏ የመሞት ዜና ጆሮዋ ዘንድ ደርሷል። ይህንም ስትሰማ እጅግ ተብረከረከች። ምጡ ጠናባት! ለመሞት ማጣጠር ጀመረች። ካለችበት ብርቱ የወሊድ ምጥ ላይ ሌላ ነፍስን አፍኖ የሚገድል ምጥ ተደመረባት። አይደለም ወልዶ መሳም ለመኖር እንኳን ተስፋን አጣች።
ታዲያ ለሞት በምታጣጥርበት ጊዜ ማንም ሌላ ተስፋ አይታየውም። አዋላጆቿም በታላቅ ስጋት ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመቱ አይከብድም። ሆኖም በዚህ ጠንከር ባለ የሀዘን ጊዜ አንዳች ተስፋን የሰነቀ ድምፅ ይደርሳታል። ''አይዞሽ ወንድ ልጅ ወልደሻል።''(1ሳሙ:-4v20) የሚል ድምፅ!! ይህንን ቁጥር ሳነበው በአንዲት ቅፅበት የመርዶ መዓት የጎረፈባትን ሴት በርህራሄ ልብ አሰብኳት። አጠገቤ እንዳለች ያክል እያሰብኩኝ ''እንኳን ጌታ ካሰሽ አልኳት።'' ምንም እንኳን የህይወት አጋሯን፣ አማቷን ብታጣም፤ በአዲሱ በእግዚአብሔር ስጦታ ልትፅናና እንደምትችል በማሰብ እጅግ ደስ አለኝ። በማስታወሻ ደብተሬ ላይ'ም 'እግዚአብሔር ይክሳል' በሚል ርዕስ ትምህርት መስራት እንዳለብኝ በማሰብ ቀጣዩን ቁጥር ማጥናቴን ቀጠልኩኝ።
ቀጣዩ ቁጥር ግን ይልቁን አወዛገበኝ። ነፍሱ-ጡሯ ይልቁን ስትከፋ አገኘኋት። ለሰማቺው የምሥራች የሚመጥን የደስታ ምላሽ ሲጠበቅ ቅንጣት ታክል እንኳን ፈገግ ስትል አትታይም። ( ''እርሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብ ብላም አላደመጠችም።''(1ሳሙ:-4v20) እርግጥ ነው በአንዲት ቅፅበት የደረሳት መርዶ አደናብሯታል። ቢሆንም በዚህ ሁሉ መሃል አምላክ ልጅ እያስታቀፋት፣ እየካሳትም ነው። እርሷ ግን ወይ ፍንክሽ ስትስቅ አትታይም። ታዲያ እኔም ዝብርቅርቅ ባለ ስሜት ወደ ቀጣዩ ቁጥር አቀናሁ።
ቀጣዩንም ቁጥር ደጋግሜ አየሁት። አንዳችም ቁም-ነገር ነፍሴን ይኮረኩራት ጀመር። ለካ ነፍሰ-ጡሯ እንዲያ የሆነቺው በዚህ ምክንያት ነው የሚል መገለጥ ነፍሴን ጠፍንጎ ያዛት።
1ሳሙ:-4v21 :- "የእግዚአብሔር ታቦት ስለተማረከ፣ ዐማቷና ባሏም ስለሞቱ፣ "ክብር ከእስራኤል ተለይቷል " ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድ አለችው።
የዚህን ቁጥር ሀሳብ ሳገኝ ስክን አልኩኝ፤ እጅግ ተረጋጋሁ። የቅድሙን ደስታ ሁሉ ጣልኩኝ። የሠራሁትን ትምህርት አፈረስኩኝ።
ጉዳዩ ወዲህ ነው፦ ለካ ነፍሰ-ጡሯ በልጅ የማይካስ ሀዘን ነፍሷን በጦር ወግቷታል። ይህ ሀዘን የእግዚአብሔር ታቦት በመማረኩ የመጣ ነው። የቁ'21'ን የሀሳቡን ቅደም ተከተል እና 'flow' ስናይ የሚነግረን ይህንኑ ነው። የእግዚአብሔር ታቦት ማለት የእግዚአብሔር አብርሆት ማለት ነው።
ነፍሰ-ጡሯ አንድ እውነት ገብቷታል:- ልጅ በልጅ ይተካ ይሆናል። እግዚአብሔር ግን በምን ይተካል? በምንም አይተካም!!!
ነፍሰ-ጡሯ ሴት:- ሕፃኑን ልጇን ካለችበት ትልቅ ሀዘን እንደመፋቺያ መፍትሔ ስትቀበለው አናያትም፤ እንዲያውም ይልቁን ሀዘኗን የምታስታውስበት ማስታወሻ አድርጋ ስሙን ኢ-ካቦድ አለቺው። ኢካቦድ ማለት ክብር ከእስራኤል ተለይቷል ማለት ነው።
የእግዚአብሔር ክብር ተለይቶ የምን surprise አለ? የለም!!!
ተወዳጆች ሆይ:- ገንዘብ ቢጠፋ በገንዘብ ይካሳል፤ ሰው ቢሄድ ሰው በሰው ይካሳል፤ በዚህ ምድር ላይ ያለ የትኛውም ነገር መተኪያ ሊኖረው ይችል ይሆናል።
የእግዚአብሔር አብርሆት ግን በምን ይተካል?
ነፍሰ-ጡሯ የፊንሐስ ሚስት የገባት እውነት ይግባን!!!
✍️ Tesfatsion Feleke
💐💐 @wengelbeArt 💐💐