ስብዕናችን #Humanity


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Психология


🔆እየጠየቁ መኖር መልስን፣
መልስን ፈልጎ ማግኘት ዕውቀትን፣
እውቀት ነፃነትን፣ ነፃነት ሙሉ ስብዕናን፣
ሙሉ ስብዕና ሠላምና እርካታን፣
እርካታ ደግሞ ደስተኛ ሆኖ መኖርን ያስገኛል፡፡
አብረን እንደግ !!
@EthioHumanity @Ethiohumanity
✍የተሰማቹን አጋሩን! ቤቱ ሁሌም ክፍት ነው፣ሃሳባቹን ፃፍፍ አርጉልን @EthioHumanitybot

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Психология
Статистика
Фильтр публикаций


🌗በአንድ ወቅት ጫካ ውስጥ መውለጃዋ የቀረበ አንዲት ሚዳቆ የመውለጃ ሰዐቷ ደርሶ ትግል ላይ ሳለች ድንገት አከባቢዋን ስትቃኝ ከፊት ለፊቷ ወንዝ ፣ ከኋላዋ ቀስት ያነጣጠረባትን አዳኝ፣ ወደ ጎን ስትዞር የተራበ አንበሳ አሰፍስፎባት ትመለከታለች።

ይህም ሳይበቃት ጭማሪ ከፍተኛ ነጎድጓድና መብረቅ ያጀበው ደመና መጥቶ ሰማዩን ያጨልመዋል። መብረቁም ሀይለኛ ስለነበር ደኑን ይመታውና ከፍተኛ ቃጠሎን ያስነሳባታል። ምን ታድርግ?

ወደ ፊት ሮጣ እንዳታመልጥ ጥልቅ ወንዝ ተደቀነባት፤ከኋላዋ አዳኙ፤ከጎኗ ደግሞ አንበሳው፤ወደ ጫካ ገብታ እንኳ እንዳትደበቅ ደኑ ከፍተኛ ቃጠሎ ላይ ነው...
በዚያ ላይ የውልደት ህመም ነፍስ ውጪ ግቢ እያስባላት ነው ...

💡ሚዳቆዋ በዚህ ውጥረት ውስጥ ሆና ትኩረቷን መፈፀም ወደ ምትችለው ነገር ላይ ብቻ በማድረግ ቀሪውን ለፈጣሪ በመተው በመወለድ ላይ ስላለው ልጇ ብቻ ማሰብ ጀመረች.....

አዳኙ ቀስቱን አነጣጥሮ ሊለቅ ባለበት ቅፅበት ድንገት የመብረቁ ብልጭታ አይኑ ላይ ብዥታ ፈጠረበትና ቀስቱ ተስፈንጥሮ ወደ ተራበው አንበሳ ይሄድና አንበሳውን ይገለዋል።

አጉበድብዶ የነበረው ደመናውም መዝነብ ይጀምርና የደኑን ቃጠሎ በቅፅበት አጠፋው። በጭንቅ ታጅባ የነበረችው ሚዳቆም በሰላም ተገላገለችና ወደ ቀደመው ህይወቷ ተመለሰች።

🔑አንዳንዴ በህይወትህ ውስጥ በብዙ ፈተናዎችና ጭንቀቶች ልትከበብ ትችላለህ፣ ያኔ አንተ ልትፈታው በምትችለው ነገር ላይ ብቻ አትኩርና ቀሪውን ለመፍትሄዎች ሁሉ ባለቤት ለሆነው ለፈጣሪህ ተወው።

መውጫ መፍትሄ አንተጋ እንጂ ፈጣሪህ ዘንድ አይጠፋም። አስታውስ ሁሌም ትላልቅ ወይም ከባባድ ፈተናዎች አሉብኝ ብለህ ለፈተናዎች እውቅና ከመስጠትህ ይልቅ የከባባድ ፈተናዎች አለቃ የሆነው ፈጣሪ አለኝ እያልክ ጭንቀቶችህን አቅልላቸው፣ሁሌም በፈጣሪህ ፈፅሞ ተስፋ አትቁረጥ!!!

📍ገጣሚ በረከት በላይነህ ''ሳይፀልዩ ማደር'' በምትለው ውብ ግጥሙ እንለያይ፣

''ሳይፀልዩ ማደር''

የተራበ ነብር ከሩቅ ተመልክታ
ሚዳቋ ፀለየች....
"አውጣኝ አውጣኝ" አለች ለፈጠራት ጌታ
...
ነብሩም ተርቦ
ወደ አምላኩ ቀርቦ
ሚዳቆዋን አይቶ - አንጀቱ ከሆዱ እንደተጣበቀ
ፈቅዶ እንዲሰጠው - አምላኩን ጠየቀ
...
የሁላችን ሰሪ
ፀሎታቸውንም ሰማቸው ፈጣሪ
አምላክም በድምፁ ሚዳቆዋን አላት
"እሩጠሽ አምልጪ ከበረታው ጠላት"
...
ነብሩንም አለው - "እሩጥ ተከተላት ምግብ አድርገህ ብላት"
ሚዳቆዋ ስትሮጥ
ከነብር ለማምለጥ
ነብሩም ሲከተላት
ሆዱን ሊሞላባት
.
ቋጥኙን ስትዘል እግሯ ተስፈንጥሮ
ሆዱን ብትረግጠው የተኛው ከርከሮ
ከእንቅልፉ ሲነቃ ልክ ሲደነብር
ጉሮሮውን ያዘው የፀለየው ነብር
...
አውጣኝ ያለው ወቶ አብላኝ ያለው በላ
ሳይፀልይ ያደረው ከርከሮ ተበላ

           ውብ አሁን ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot




💎አንተ ከነሱ የተለየህ በመሆንህ ሲስቁብህ አንተ ደግሞ አንዳይነት በመሆናቸው ሳቅባቸው!

ንስር የጨለመውን ወጀብ ሰንጥቆ ያልፋል እንጅ ጨለማው እስኪያልፍ አይጠብቅምና ጀግናም ጥዋት በወጣበት ስታይል አይመለስም ለማለት ነው ። 😉

አለም ለደፋሮች ታደላለች። ወደ ከፍ ያለ ማንነት ጉዞ ስትጀምር የነፍስክ ጥንካሬ ተአምራዊ ወደ ሆነ ቦታ ያደርሥሀል።

ሽብርቅርቅ ያለች ቅዳሜ ትሁንልን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot



💫እንኳን ለ 1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በአል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
                
❤️በመላው አለም የምትኖሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ሙስሊም ወገኖቻችን እንኳን ለ1445ኛው የዒድ  በአል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን።

✨ የዒድ በአል የእዝነት ÷ የመተሳሰብ ÷ አብሮ የመብላትና የመፈቃቀር በአል በመሆኑ በየ አካባቢያችን በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን እያሰብን እንዋል።

          ዒድ ሙባረክ !!!❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity


❤️ነፍሴ ስትመክረኝ …

የውስጥ ሰላም ከብር ፣ ከወርቅ ፣ ከአልማዝም ሆነ እንቁ ይልቃል ፤ ስኬታማነት ከውስጥ ሰላም ፣ ደስታና ፍቅር በጥብቅ የተቆራኘ ካልሆነ ትርጉሙ ጎዶሎ ነው። ወደ ሀቅ የምትጠራህ ነፍስህን በድለህ ሺህ ግዜ የምድር ሃብት ብትሰበስብ ሀብትም ሆነ ሌላ ነገርህ የውስጥ ሰላም እስካላስገኘልህ ድረስ ተሳካልህ ተብሎ አይታመንም ፤  በዚህ መልኩ የምታገኘው ነገር " ይዘህ ተገኘህ " እንጂ ተሳካልህ አያሰኝም።.

📍ሰላም የሚያሳጡ ፍጡራኖችን ያየህ እንደሆነ በሌሎች ሰዎች ዋጋና መስዋትነት ማትረፍ የለመዱ ፤ ከራሳቸው ጋር ሰላም መፍጠር ያልቻሉ ስግብግቦች እንደሆኑ  ለሰከንድ አትጠራጠር። ከእንደዚህ ዓይነት ስግብግብነት ተጠቆጠብ የሰላም እሴትህን ጠብቅ ፣ ይዘው የተገኙት እየቀደሙህ እየመሰለህ የመልካምነት ጉዞህ መሐል ላይ አትወዛገብ ከመልካምነት እና ከሀቅ በላይ አድካሚና አሸልቺ ግን ደግሞ ፍሬው ጣፋጭ የሆነ እፁብ ድንቅ መታደልና መባረክ የለም።

💡አንዳንድ ጊዜ በራስህ ዓለም ዉስጥ ብቻ ለመኖር ሞክር፡፡፡ ወደ ምድር የመጣኸው ትርጉም ላለው ዓላማ ነውና ሁሉም ቦታ ላይ ጥቀም፡፡ በደረስክበት ቦታ ሀሉ መልካም ዝራ፡፡

📍እቅድህን በመኖር ሂደት በሚገጥሙህ ፈተናዎች አታማር ከአሁን ቀደም የሆኑ ፣ እየሆኑ ያሉ ፣ ከአሁን በሁዋላ በፈለግከውም ሆነ ባልፈለግከው መንገድ የሚሆኑ ነገሮች ሁሉ በምክንያት ያጋጠሙህ እንደሆኑ እመን። የፈተና መብዛቱ ለበጎ ነው፡፡ አካሄድህን እንድታስተካክል ይረዳሃል፡፡ በችግሮች ዙሪያ ተጠበብ እንጂ አትጨነቅ ፤ ለመልካምነትና ከሀቅ ጋር ለመታረቅ የረፈደ የሚባል ግዜ የለም ፤ የቻልከዉን ያህል ስራና እረፍ ፤ ቀሪውን ለፈጠረህ ጌታ ተወው።

ሀቀኝነትን ድፈር ፤ ሀሜተኝነትንና ዋሾነትን ፍራ

💡ደፋር ይሰማል ፣ ያደምጣል ፣ ይናገራል ፣ ይመረምራል ፣ ይፅፋል ፣ ይወስናል ፤ የሰማውን ሁሉ እንደ ሰነፎችና ፈሪዎች እውነት ብሎ አያምንምም አይፈርጅምም ፤ የሰማኸውን ሁሉ እንደ እውነት አምነህ ደግመህ ደጋግመህ ሳታረጋግጥ አታውራ ፤ ማጣራትን አስቀድም ፤ ሳትጠይቅ እና ሳታመዛዝን አትፍረድ።

ስምህን ከምታውቀው በላይ እርግጠኛ ሁን

💡እንዲህ ስታደርግ ሁሉም የሚታየው ጭለማ ፣ የሚያወራው ስለጭለማ ቢሆን ላንተ የሚታይህ ብርሃን እንጂ ሌላ አይሆንም። አትጠራጠር ንስር አሞራ ፈተናዎቿን ከደመናው በላይ ከፍ በማለት እንደምትሻገረው አንተም ፈተናዎችን ከችግሮች በላይ ከፍ ብለህ በማለፍ የውስጥ ሰላምህን ቀጣይነት እያረጋገጥክ ማሳካት ወደ ምትፈልገው ግብ የማትደርስበት ቅንጣት ታክል ምክንያት አይኖርም።

📍እናም እየነዳን ወዳጆቼ

ሁሉንም ነገር በንቃት እየታዘብን እስከነዳን ድረስ  ፤ በችግር ውስጥ ሆኖ በመሳቅ ፣ በደስታ እና በውስጥ ሰላማችን እስካልተደራደርን ድረስ የማንሻገረው ፈተናና የማናሳካው  ግብ አይኖርም።

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot




🔆ከራሱ ጋር የተስማማ ከተፈጥሮው ሁሉ ጋር ይስማማል!
(Live in harmony with nature)

📍ተፈጥሮ የሰው አካል ነው፤ ሰውም የተፈጥሮ ውህድ ነው፡፡ ሰው ከተፈጥሮ ውጭ መሆን አይችልም፡፡ ከተፈጥሮው ውጪ ልሁን የሚል ሰው ካለ መጀመሪያ የሚጋጨው ከራሱ ጋር ነው፡፡ ሁለተኛም ከልዕለ የተፈጥሮ ሃይል ጋር ይላተማል፡፡ ብዙ ሰው ከሰው ጋር ተስማምቶ መኖርን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ከራሱና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖርን አይደፍርም፡፡ ተፈጥሮው በማይፈቅደው መንገድ የሚተራመሰው ይበዛል፡፡ ያልሆነውን ለመሆን የሚፍጨረጨር የትየለሌ ነው፡፡ ሰው ከተፈጥሮው ከራቀና ከሰውነቱ ካፈነገጠ አደጋ ላይ ነው፡፡ አንድም አዕምሮው ማሰብ አቁማል፤ ሁለትም ጤንነቱ አጠራጣሪ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡

📍ጥንታዊው ሮማዊው ፈላስፋ ሴኔካ ለሚወደው ጓደኛው ለሉሲሊየስ በፃፈው ደብዳቤ ላይ፡- ‹‹ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተህ ከኖርክ በጭራሽ ደሃ አትሆንም፡፡ ነገር ግን እንደሌሎች ሃሳብ መኖር ከፈቀድክ ግን መቼም ቢሆን ሀብታም አትሆንም›› ብሎት ነበር፡፡ ሴኔካ ሀብትን ከቁስ ጋር አያይዞ አይደለም ይሄን የተናገረው፡፡ እሱ ሃብት የሚለው የመንፈስ ሀብትን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከተፈጥሮ ጋር በመግባባት የሚገኝ ነው፡፡ ተፈጥሮን ማወቅ፣ መረዳትና ከተፈጥሮው ጋር ተጣጥሞና ተስማምቶ መኖር ሰውን በመንፈሳዊ ሃብት እንዲበለፅግ ያደርገዋል፡፡ ብዙዎቻችን በመንፈሳችን ያጣን የነጣን ደሃ የሆንነው አንድም ተፈጥሮውን ለመረዳት ባለመጣራችን ነው፤ ሁለትም ሰውነታችንን ከተፈጥሮው ጋር እያቃረንን ስለምንኖር ነው፡፡

💡ብዙ ሰው በራሱ ሃሳብ ሳይሆን በሌሎች ሃሳብ ነው ኑሮውን የሚገፋው፡፡ ሰው ስለእሱ በሚሰጠው ፍረጃና አስተያየት እየተመራ ህይወቱን ሲኦል የሚያደርግ እልፍ ነው፡፡ በርግጥ የሁሉም ሰው አስተያየት ሰውን ገደል ይከታል ማለት አይደለም፡፡ የዛኑ ያህል የተሰጠን አስተያየት ሁሉ የመጨረሻው እውነትም አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል ማሰብና መመርመር የሚባል ነገር አለ፡፡ የትኛውንም መጤ ሃሳብ በአዕምሮ ወንፊትነት ማጣራት ግድ ይላል፡፡ ሳያኝኩ እንደሚውጡ ሳያስቡ የሰውን ሃሳብና አስተያየት የሚተገብሩ ራሳቸውን አደጋ ውስጥ ይከታሉ ለማለት ነው፡፡

💎ታዋቂውን የግሪኩን ፈላስፋ ዲዮጋንን አንዱ እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡- ‹‹በሕይወትና በሞት መሐል ልዩነቱ ምንድነው?›› ዲዮጋንም፡- ‹‹ምንም ልዩነት የለውም›› አለው፡፡ ‹‹ታዲያ አንተ ለምን በሕይወት ትኖራለህ? ራስህን አታጠፋም ነበር?›› ሲለው፤ ዲዮጋንም፡- ‹‹እሱም ቢሆን ምንም ልዩነት የለውም!›› አለው ይባላል፡፡ ዲዮጋን ሞትንም ሕይወትንም አንድ ያደረገው ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ሞት ያለሕይወት፤ ህይወትም ያለሞት አልተፈጠረምና፡፡ ህይወትን ተቀብለህ ሞትን መተው አትችልም፡፡ ብዙዎች ከማያመልጡት ወጥመድ መሸሽ ይፈልጋሉ፡፡ ሞት የህይወትህ አካል ነው፡፡ የትም ብትሄድ አታመልጠውም፡፡ ይልቁንስ ህይወትንም ሞትንም ጠልቀህ ከተገነዘብክ አኗኗርህንና አኳኋንህን፤ መካከሉን ሕይወትህን እንድታስተካክል ይረዳሃል፡፡

📍የብዙዎቻችን አወዳደቅ ራሳችንን አለመሆናችን ነው፡፡ የእኛ የህይወት መስመር ከሌላው ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን ከራሳችን ተፈጥሮ ጋር ተራርቀን ስላለን ደረጃችንን የምንወስነው በሌሎች መለኪያ ነው፡፡ ዋናውና ስሜትን የሚጎዳው አወዳደቅ ደግሞ በትናንት ውድቀታችን ዛሬአችንን ስናወሳስበው ነው፡፡ ሁለቱም አወዳደቆች ከተፈጥሯችን ጋር በመጋጨት የሚመጡ ናቸው፡፡

💎ወዳጄ ሆይ... ከተፈጥሮው ጋር ተስማምተህ ኑር፡፡ ከራስህ አትራቅ፡፡ የአንተነትህን ተመን ራስህ አውጣ፡፡ ደስታም ይሁን ሀዘን ያለው አዕምሮህ ውስጥ ነውና በሌሎች መለኪያ ሕይወትህን አታወዳድር፡፡ ደረጃህን በራስህ ወስን፡፡ ሌሎች ምንም ብትሆን አቃቂር ከማውጣት አይቦዝኑም፡፡ ሌሎች እንዲያመሰግኑህ ብለህ ራስህን አትጣል፡፡

📍ለህሊናህ ታመን፡፡ ውስጥህን አድምጥ! ተፈጥሮህን እወቀው፤ እውነትን ተከተል፡፡ አንተነትህን አናግረው፡፡ መንፈስህን አበልጽገው፡፡ ዕለት ዕለት ከራስህ ጋር ትነጋገር ዘንድ ልመድ! ሞት የሕይወትህ ክፋይ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ መሄድህ ላይቀር ጥሩ ነገር ሰርተህ እለፍ! ከተፈጥሮውና ከተፈጥሮህ ተማር! ቀድመህ ከራስህ ጋር ተስማማ፤ ሌላው ቀሊል ነው!!

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot


#ምክር ለወዳጅ

📍ወዳጄ ሆይ !

ያወቅከው እውቀት ቢመስጥህ የመጨረሻ እውቀት አይደለም ። በገዛ ድምፁ ባብቶ የሚያለቅስ እንዳለ ሁሉ ያወቀውም እውቀት ሲያስቀውና ሌላውን ሲያስንቀው የሚውል ሞኝ አለ ። የሞትከው ትምህርት ያቆምክ ቀን ነው ። በዓይኖችህ የምታየው ወዳጅህን በጆሮህ አትመዝነው ። ስለ ወዳጅህ ሐሜትን ይዘህ አትምጣ ፣ የሰማህበት ቦታ መልስ ስጥ ። የወዳጅ ልኩ ለወዳጅ ጠበቃ መሆን ነውና ። ደጋጎች ባይኖሩ ዓለም እንደ ቆሰለች ትቀር ነበር ። አንተም በደግነትህ የዓለምን ቍስል አድርቅ ።ማፍቀርህን እንደ ውለታ አትቍጠረው ፣ እውነተኛ ሰው ሌላውን ከመውደድ ውጭ ምንም አማራጭ የለውምና ።

📍ወዳጄ ሆይ !

ዛሬ ያበሳጨህን ነገር በትዕግሥት አሳድረው ። ከቻልህ አሠልሰው ። በልኩ ማየት ትጀምራለህ ። ፈጥነህ መልስ መስጠት ጸጸትን ፣ ተስፋ መስጠትም ቁጭትን ያመጣል ። ፈጣን ፍርድ በሚሰጥባቸው አገራት የተፈረደባቸው በሞቱ በማግሥቱ ንጹሕ ነበሩ ይባላል ።

ወዳጄ ሆይ

የጥንት እውቀት በመደበቅ ፣ የዛሬ እውቀት ግን በመስጠት ይከብራል ። በዚህ ዘመን እውቀትን ብትደብቅ አላዋቂ ትሆናለህ ። የእውቀት ስስት የጠፋበት ዘመን በመሆኑ ልናደንቅ ይገባናል ። የምትወደው ሰው ጋር ለመኖር በዝግ ልብ ሁነህ አትቅረበው ። ብዙ አለመጠበቅ ፣ ይቅር ማለትና ማለፍ እንዲሁም ጠባዩንና የአስተዳደግ ተጽእኖውን መረዳት ይገባሃል ። የምትወዳቸው አንተን የማወቅ መብታቸውን ከከለከልካቸው ይጠሉሃል ። በዝግ በር እንደማይገባ ዝግ በሆነ ልብም ወዳጅ አይስተናገድም ።

💡ወዳጄ ሆይ !

ተዘቅዝቀህ ስታይ ሁሉም ሰው የተዘቀዘቀ ይመስልሃል ። ስትወድቅ ሁሉም ሰው ውዳቂ ይመስልሃል ፣ ስትረክስም የሰው ሁሉ ርኩሰት ይታይሃል ። በእግርህ ቆመህ በጭንቅላትህ አስብ ። በእግር መቆም ባመኑበት መጽናት ፣ በጭንቅላት ማሰብ ማስተዋል ነው ።

📍ወዳጄ ሆይ !

ገንዘብህን ይውሰዱብህ እንጂ አመልህን እንዲወስዱብህ አትፍቀድላቸው ። ስምህን ባገኙት ጭቃ ሊያቆሽሹት ይችላሉ ፣ አንተነትህን ግን አንተ ብቻ ትለውጠዋለህ ። ከሰረቁህ ይልቅ የምትጥለው እንዳይበዛ ተጠንቀቅ ።

💡ወዳጄ ሆይ !

በወንድምህ እጅ ያለውን ክብር ለእኔ ቢሆን ብለህ አትናፍቅ ። ምኞት ምቀኛ ፣ ምቀኝነትም ክፉ እይታ ፣ ክፉ እይታም ነፍሰ ገዳይ ያደርጉሃልና ።  ዕድሜህ እንዳያጥር ትልቅ አዋራጅ አትሁን ። መኖርህ ለሚያስደስታቸው ቅድሚያ ስጥ ። ለሚጸልዩልህ ምርኮህን አካፍላቸው ። ያልተቀበረ ሬሳ እየገደለህ ይመጣል ። ያልተሻረ ቂምም እየመረዘህ ይመጣል ።

ወዳጄ ሆይ !

ተቃውሞን ከፈራህ ሥራ አትጀምር ። ነቀፋን ከሰጋህ ከቤትህ አትውጣ ። ውግረትን ካልጠበቅህ ባለ ራእይ አትሁን ። ለማግኘት ማጣት ፣ ለመክበር መዋረድ አስፈላጊ ነው ። ጸጋ ፈጣሪ የሚበዛልህ በሁለት ነገሮች ነው ። የመጀመሪያው በትሕትና ፣ ሁለተኛው በባለጌዎች በመሰደብ ነው ።

📍እናም ወዳጄ !

ጥቅም ለማግኘት ብለህ የተዋጋኸው ውጊያ በመጨረሻ ባለጠጋ እንጂ ባለ ኒሻን አያደርግህም ። ከገንዘብ ክብር እንደሚበልጥ ተረዳ ። የረዳህን ፈጣሪ አልሰጠኝም ብሎ ማማት ነውና እያለህ ከሌላቸው ጋር አትሻማ፣ የሌለህን ስትመኝ ያለህን እንደምታጣ ተገንዘብ ። ግማሽ ደግነት የክፋት ያህል ነውና ለጉዳይህ ብለህ ቸር አትሁን ። የጎደለ እንስራና ባዶ አዳራሽ ድምፅ ያበዛሉና በእውቀትና በመንፈስ ሙሉ ሁን ።         

  ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot




🌗 ቅብጥብጡ ውሻ

✨የት እንዳነበብኳት ባላስታውስም ከረጅም ጊዜ በፊት ያነበብኳት አንዲት አጭር ታሪክ ትዝ አለችኝ፡፡ አስተምራኝ አልፋለች፣ ዛሬም ባሰብኳት ቁጥር ታስተምረኛለች፡፡ የአንድ ሰውና የውሻው አጭር ታሪክ ነው፡፡

💡በገጠራማው አካባቢ የሚኖር አንድ ሰው ከቤቱ ወጥቶ ወደ 30 ደቂቃ የሚፈጅ የእግር ጉዞ ካደረገ በኋላ መድረስ ወደሚገባው የወዳጁ ቤት ደረሰ፡፡ ከእሱ ጋር እሱ በሄደበት ሁሉ የሚከተለው በጣም የሚወደው ውሻው እንደተለመደው ተከትሎት መጥቷል፡፡ ሰውየው ወዳጁ ቤት ሲደርስ ከወዳጁ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወዳጁ፣ “ያ ሁልጊዜ በሄድክበት ሁሉ የሚከተልህ ውሻህስ የት አለ?” ብሎ ገና ከመጠየቁ ውሻው እያለከለከና በውኃ ጥም ለሃጩን እያዝረከረከ ከባለቤቱ ጀርባ ከተፍ አለ፡፡

የዚህ ሰው ወዳጅ የሰውየውን አለመድከም ከውሻው ማለክለክ ጋር አነጻጸረና፣ “ውሻህን ምን አድርገኸው ነው እንደዚህ የደከመው፡፡ አንተ ምንም የድካ ስሜት አይታይብህም፣ እሱ ግን በጣም ደክሟል” አለው፣ ልክ በውሻው ላይ እንደጨከነበትና ችላ እንዳለው አይነት ስሜት በሚሰጥ ሁኔታ፡፡

💡የውሻውም ባለቤት ይህ የለመደውና በሄደበት ሁሉ ሰዎች የሚጠይቁት ጥያቄ በመሆኑ ብዙም ሳይገረም በውስጡ አቀባብሎ ያለውን መልስ መለሰለት፣ “የሚገርምህ ነገር ሁለታችን ከቤት ተነስተን እኩል መንገድ ነው የመጣነው፡፡ በእኔና በእሱ መካከል ያለው ልዩነት እኔ ቀጥ ብዬና ተረጋግቼ ነው የመጣሁት፣ እሱ ግን እንዴ ወደ ግራ፣ አንዴ ደግሞ ወደ ቀኝ ሲባዝን፤ አንዴ አንድን ነገር ሲያባርር፣ እንዴ ደግሞ ቆም ብሎ መሬቱን እያሸተተ አንድን ነገር አገኛለሁ ብሎ ሲቆፍ፣ እኔ ስርቅበት ደግሞ ለመድረስ ሲሮጥ . . . ሁል ጊዜ እሱን የሚያደክመው ይህ ቅብጥብጥ ባህሪው ነው”፡፡

💡ለካ ያለመጠን የሚያደክመን መንገዳችን ብቻውን አይደለም፣ ለካ የሚያዝለን ስራችን ብቻውን አይደለም፣ ለካ በቀኑ መጨረሻ ላይ ዝልፍልፍ የሚያደርገን የቀኑ ዋና ዓላማችን አይደለም፣ ለካ በኑሮ ድክም ያልነው በተለመደው የኑሮ ሂደት አይደለም፡፡ እኛን የሚያደክመንና ዝለት ውስጥ የሚከተን በመንገዳችን ላይ በማያገባን ነገር እየገባን ወዲህና ወዲያ የምንለው ነገር ነው፡፡

ይህ እውነት የገባኝ ቀን . . .

💎ስለማያገባኝ ሰው ማውራት አቆምኩኝ፣ በማያገባኝ ስፍራ መገኘት ተውኩኝ፣ ምንም ለውጥ በማያመጣ ነገር ላይ መከራከርን ጣልኩት፣ ምንም ተጽእኖ ከማላመጣለት ሰው ጋር መነታረክን ተወት አደረኩኝ፣ ድምዳሜ ላይ ስደርስ ምንም ፋይዳ የማያመጣልኝን ጉዳይ ማሰላሰል እርግፍ አደረኩኝ . . . በአጭሩ የማደርገው ነገር ሁሉ ከዋናው የህይወቴ ዓላማና እሴት ጋር የመጣጣሙን ጉዳይ ማሰብ መኖር ጀመርኩኝ፡፡

ይህንን ያደረኩኝ ጊዜ ብዙ ሸክም ከላዬ ላይ የተነሳ ያህል እርምጃዬ ቀለለኝ፣ ምክንያት-የለሹ የድካም ስሜት ተወኝ፣ የጀመርኩትን ግቤን ጥጉ የማድረስ ጉልበት አገኘሁኝ! ለካ እኔንም ልክ እንደ ቅብጥብጡ ውሻ ያደከመኝ ቀጥታው ሳይሆን ግራ-ቀኙ እና መለስ-ቀለሱ ነው!
   
✍ ዶ/ር እዮብ ማሞ

ውብ ጊዜ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot




📍ወዳጄ ሆይ

አትድከም፣ አትዘን ማን ያውቃል ሸክምህና ህመምህ ሁሉ ተራግፎ ሌላ ሰው ሆነህ ትነሳ ይሆናል። ያለን ፈጣሪ እንኳን በአንድ ሙሉ ሌሊት፣ በቅጽበት ጊዜ ዉስጥም ብዙ ተዓምር ይሠራል።

በቀልባቸው ንፅህና ብቻ ሰላማቸው የበዛ ሰዎች አሉ። ቀልባችሁ ንፁህ ሲሆን ሰላማችሁ ይበዛል፣  ለሌሎች መልካም ስትመኙ በረከታችሁ ይሰፋል። ልብህ የተጠራጠረዉን ነገር ተው፤ ልብ ከዐይን በላይ ያያልና።ወደ ፊት የሚሆነውን ሳትበሳጭ ሳትሰለች በትግስት ጠብቅ።የማይረባና ጥቅም የሌለው ነገር በመከተል ጉልበትህን አታባክን።

ወዳጄ ሆይ

ከሐዘን በኋላ ደስታ እንጂ ምን አለ!
ማጣትን ማግኘት እንጂ ሌላ ምን ይከተለዋል! ምሽቱስ እየነጋ አይደል የሚሄደው?? ከጨለማ በኋላ ብርሃን እንጂ ምን ይመጣል፡፡ የጨለመው ይበራል ፣ የጠፋዉም ይገኛል ።

ሕይወትህን መስዋዕት ያደረግህለት ሥራህ በፈረሰና በተናደ ጊዜ ይህንን ክፋ ፈተና ተቀብለህ ተስፋ ሳትቆርጥ የጠፋውን ሁሉ መልሰህ ለማቋቋም በደከመ መሣሪያ ለመሥራት ሳታመነታ ተነሣ።ያለነው የፈተና ምድር ውስጥ ነው። በበሽታ መፈተን አለ። በኀጢአት መፈተን አለ። በዕዳ መፈተን አለ ፣ የምድር ፈተናዎቿ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም።

እናም ወዳጄ

ያለህን የሌለህን ገንዘብህን ሁሉ አንድነት አከማችተህ ስትሰራበት ሁሉንም ባንድ ጊዜ ስትከሥር አጣሁ ከሠርኩ ብለህ ቃል ሳትተነፍስ አሁንም ሰርተህ ለማተረፍ ከሥር ጀምረህ እንደ ገና አንድ ብለህ ድከም። ዐሳብህ ጉልበትህ ሥሮችህ ታክቶዋቸው በደከሙ ጊዜ ልብህ ብቻ ይበርታ።

ንፋስ የማይወዘዉዘው ዛፍ የለም። ሀሳብ ወስዶ የማይመልሰው ሰዉም የለም። እንዲህም ሆኖ የማይወድቅ ዛፍ አለ። በፈተና የሚፀና የሚበረታ ሰዉም አለ።

            ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot


📍በሠዎች ዘንድ ተስፋ የሌለን ብንመስልም እንኳ ዋናው ነገር በፈጣሪ ዘንድ ያለው ተስፋችን ነው። ሕይወት ጠመዝማዛ ብትሆንም ውብና ተስፋን የተሞላች ናት።

💡በዚህ አለም ሁሉ ነገር አበቃ፣ አከተመ ባልንበት ጊዜ የሚቀጥል የተሻለ እድል፣ የምናውቀውና የተለመደው በር የተከረቸመ ቢመስልም ወለል ብሎ የሚከፈት ሌላ በር፣ ዙሪያችን ጭው ያለ በረሃ ቢሆንም የለመለመ መስክ የሆነ ስፍራ ላይ እንዳለ ተምሬያለሁ።

📍ህይወት እንደ ሳንቲም ናት ሁለት ገፅታዎች አሏት ፣ ተቃራኒ ግን ማይነጣጠሉ ገፅታዎች ። በህይወት እስካለን ካአንዱ ገፅ ብቻ ስንኖር ማለፍ የለም፣ እያንዳንዷ ሁኔታ ከጀርባዋ ተቃራኒ ገፅ አላት እናም ሳንቲም ያለ ግልባጭ ገፁ ምሉዕ እንደማይሆነዉ ያለ ሀዘን ደስታ ፣ ያለ ሞት ህይወት ፣ ያለ  ለቅሶ ሳቅ ፣ያለ ድህነት ሀብት ፣ ህይወትን ከነ ህብረ ቀለሟ አምነን መቀበል አለብን ፡፡

💡እድል ፊቷን ያዞረችብን በመሰለን ጊዜ እንኳ ቢሆን አብዝቶ በትጋት መጓዝ እንጂ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ትጋት የተስፋ ልጅ ናት። ተስፋ ደግሞ በእኛና በፈጣሪ መካከል የእምነት ድልድይ ስለመኖሩ ማረጋገጫ ነውና!
"ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ፣ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው" ።

✍አለማየሁ ዋሴ

ውብ አሁን♥️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot


Видео недоступно для предпросмотра
Смотреть в Telegram
⚡️የጨረቃዋን ውበት የሚሻ ጨለማውን አይሸሽም፣ ጽጌረዳዋን ብሎ የሄደ እሾሁን ፈርቶ አይመለስም
ፍቅርን ከልቡ የሚፈልግ ሰው ከራሱ አይደበቅም ፣እራሱን ፈጽሞ አይሸሽም ።

የምንፈራው ነገር ብዙ ጊዜ የምንመኘውና የሚበጀንን ነገር ነው። ሰዎች ከእውነተኛ ፍላጎታችን የመሸሽ ባህሪ አለን። በምክንያቶች እራሳችንን እያታለንን፤ ሊነቃ የሚታገለውን ድብቅ ምኞታችንን መልሰን እናስተኛዋለን።

✨ፍርሃታችንን ብንከታተለው..ጥበባችንንም እዛው ማግኘታችን አይቀም። ለዚህም ነው ልትገባበት የምትፈራው ዋሻ ውስጥ ነው ሀብትህን የምታገኘው የሚባለው። ውብ ነገሮችን ለማግኘት ሰው ፍርሃቱን አልፎ መሄድ አለበት፤ በምንፈግልጋቸው ነገሮችና በእኛ መካከል የቆመው ትልቁ ግድግዳ ካለማውቅ የሚመነጨው ፍርሃት ነው:: ጨለማውን የደፈረ ጨረቃን፤ እሾሁን ያልፈራ ጽጌረዳዋን፤ እራሱን ያወቀ ፍቅርን ማግኘቱ አይቀርም::

🔑ፍርሃታችንን....እንከተለው ፤ የፍርሃት ዱካ እውነትኛ ምኞታችንን ያሳይን ይሆናል። ያንቀላፋውን ምኞት የሚቀሰቅሰውም ይኸው ለፍርሃት የምንሰጠው ምላሽ ብቻ ነው።

             ውብ አሁን♥️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot


🔺“ሰው - ራሱን እንኳ የሚያስደምመውን ተቃርኖ በውስጡ ተሸክሞ የማይፈራ።

“ሰው” -ጨክኖ መግደልን ከአፍቅሮ መግደል ጋር አስማምቶ ሲኖር እንቅልፍ የማያጣ።

ሰው' -ሰፍሮ ያልጨረሰው መሬት ቢጠበኝ ብሎ የሚሰፋ።

“ሰው -የስጋ ደካማነቱን ማካካሻ ከምናቡ ቆርጦ፥ በስራው፣ በሰራው እና በሚሰራው፤ ደካማነቱን የረታ፣ የሚረታ።

“ሰው -የማያቋርጥ የተቃርኖ ጅረት፣ የማይጠግ ጥበብ ምንጭ፤ የፍርሀት ልጅ፣ የድፍረት ወላጅ።

“ሰው - ምንነቱ ከማንነቱ የተምታታ፤ ምንነቱ ማለቂያ ቢስ፣ በማንነት የሚታሰር።

ሰው ፥ ይህ ሰው! እንዴትና በምን ?” ምንስ ሆኖ ?” ራሱን፣ ማንነቱን፣ ሰው-እነቱን ረሳ ?! ከዚህ በላይስ ምን ይገርማል !

📍ለማንኛውም ካላስታወሳችሁ አይፈረድባችሁም፡፡ ራሱን የረሳ ሰው፥ ሌላ ነገር አስታውስ ተብሎ ሊጠየቅ አይገባም፡፡ ግን ለምን አይገባም ?” ባይገባም፣ ባይገባም ግን ይጠየቃል፤ ይጠይቃል፣ ይመልሳል። የሆነውን ሳይሆን ያልሆነውን፣ የኖረውን ሳይሆን የተነገረውን፣ እውነቱን ሳይሆን የተባለውን ይመልሳል።

ሰው መሆን በጣም ይደንቃል። ሰው መሆኑን የረሳ ሰው፥ ወንድ መሆኑን ግን ሲያስታውስ አይደንቅም ?” ሰው መሆኑን የረሳ ሰው፥ ነጭ ወይም ጥቁር መሆኑን ሲያስታውስ አይደንቅም ?”

መሬት ላይ የተፈጠረ ሰው፥ መሬትን ረስቶ ሀገሩን ሲያስታውስ አይደንቅም ?” ከሌላው ጋር መግባቢያ ቋንቋ እንዳለውና ይህም ደግሞ ከየትኛውም ፍጡር እንደሚለየው ረስቶ፥ መናገሪያውን ማስታወሱ አይደንቅም ?”

ብትረሱም አልፈርድባችሁም። ዞሮ ዞሮ ምንም ነገር እንዳለኝ ወይም እንደነበረኝ ያወቅሁት፥ ሳይኖረኝ ሲቀር ነው። እናትም፣ ቋንቋም፣ ሀገርም፣ አያትም፣ አባትም፣ ሃይማኖትም ሁሉም፡፡

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanitybot


እነዚህ መፅሐፎች ቅፆች ያሉት ሰው የሚሸጥ ካለ እንደው ወይም የምታውቁት ሰው ካለ ብትተባበሩኝ

@Nagayta በዚህ ሊንክ ልታገኙኝ ትችላላችሁ


✨«እናንተ የዓለም ብርሃን ፣ የምድርም ጨው ናችሁ»

🔷ብርሐንና ጨው ከተባልን ዘንዳ፤ እንግዲያውስ እውነተኛው ብርሐንና እውነተኛው ጨው ምንድነው አልን ! ቃሉን ልንተነትን ሳይሆን ቃሉ ያጫረብንን መረዳት ከአኗኗራችን ዘይቤ ጋር አዛምደን፣ በዘመናችን ታይታ ወዳድነት እና የመታየት ልክፍት፥ ሳናውቅ ለገባን እኛ ነገሩን ለማስታወስ ያህል ይህን አልን!

📍ብርሐን ያሳያል እንጅ አይታይም! ብርሐን የማይታየው ጨለማ ውስጥ ስለሆነ አይደለም፣ ይልቁንም ብርሐን ብርሐኑን የሚያበራው ወደራሱ ሳይሆን ወደሌሎች በመሆኑ ነው! ሌላውን ለማሳየት እንጅ ራሱን ለማጉላትና ለማድመቅ የሚታገል ብርሐን በዙሪያው የሚረጨው ጨለማ ብቻ ነው! እዚህ ላይ ብርሐን ስል የብርሃን ምንጩን ጭምር ማለቴ ነው።ብርሃን ተፈጥሮው ማሳየት እንጅ መታየት አይደለም።

🔷ፀሐይ በምትረጨው ብርሃን ዓለም ይነጋል ፤ ፍጥረት ሁሉ ይደምቃል፣ ተክሎች ያድጋሉ፣ አበቦችም ይፈካሉ፣ ቆፈን ይገፈፋል፤ ፀሐይን ራሷን ግን ለሴከንዶች እንኳን ማየት አንችልም።ታሳያለች እንጅ አትታይም! የቤታችንን አንፖል ከነመኖሩ የምናስታውሰው ቤታችን ሲጨልም ብቻ ነው፣ ግን ሁሉን ነገር የምናየው ከአንፖሉ በሚወጣው ብርሃን ነው። አንድ ሰው ሻማ የሚለኩሰው ሻማውን ሲያይ ለማምሸት አይደለም ፣ በሻማው ብርሃን አካባቢውን ሊያደምቅ ነው! መታየትን የምትሳሳ ነብስ ብርሐን አይደለችም፤ ይልቅ ብርሐን ያስፈልጋታል፤ በሌሎች ጨለማ የምትሳለቅ ነፍስ ብርሐን በውስጧ የለም ፣ብርሐን በተገኘበት የሌሎችን ጨለማ ያነጋል እንጅ በጨለማቸው አይዘባበትም።

📍ጨው እና ብርሃን ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፤ ጨው ብቻውን ምግብ ነኝ ብሎ ማዕድ ላይ አይኮፈስም፤ ቢኮፈስም የሚነካው የለም! ጨው ምግቡ ውስጥ አይታይም ግን ምግቡን ያጣፍጣል! በአጭሩ ነፍሳችሁ መታየትን መጉላትን መደነቅን መወደስን ከፈለገች «ሰዋዊ ነው» በሚል ትሁት መታበይ ራሳችሁን አታታሉ። እንደዛ ካሰባችሁ ብርሐንም ጨውም አይደላችሁም! እንደውም ትክክለኛ ጨውነታችሁ የሚታወቀው በእናተ በጎነት ሌሎች ሲወደሱ ነው! በተረት እንዝጋው «በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ» ይሄው ነው!

✍አሌክስ አብርሃም

ውብ አሁን❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot


💡ወንድሜ! ራስ ወዳድነት የታወረ የበላይነትን የመሻት መክንያቱ ነው።የወንድምህ የበላይ የመሆን ፍላጎት ጎሳና ነገድ እንዲፈጠር ምክንያቱ ሆነ፤ጎሳና ነገድ ደግሞ እርስ በርስ መጋደልና አንዱን መጨቆን አስከተለ።

📍ፍቅር በእዉቀት ሃይል ታምናለች ፤ ፍትህ ደግሞ በጨለማው አላዋቂነት ላይ ትሰለጥናለች። ታላቋን ባቢሎን ካጠፍ ፣የኢየሩሳሌምን መሰረቶች ካናወጠ፣ሮምን ከፍርስራሿ ጋር ካስቀረዉ ከዚያ ሰልፍ ከሚያቀብል ሥልጣን፣አላዋቂነትና ጭቆናን ከሚያንሰራፋ የሥልጣን ሃይል ጋር ፍፁም ትቃረናለች። ዳሩ ታላላቅ ሰዎች ተብለው ሲጠሩ የኖሩ እንዲህ አይነቶቹ ወንጀለኞች ናቸው።

📍አኔ የምቀበለው ብቸኛ ስልጣን በተፈጥሮ ሕግ ላይ የተመሰረተዉን ፍትሕና እሱን የሚቀበለውን እዉቀት የያዘውን ብቻ ነው። የራሱን ጉዳይ ብቻ የሚያቅፍ ባለሥልጣን ላይ ፍትህ ምን የምታደርግ መስልሃል?

አንተ ወንድሜ ነህ፤ስለዚህ እወድሃለሁ! ፍቅር ደግሞ ታላቅ ፍትህ ነው! ከየትኛውም ጎሳ ወይም ነገድ ብትመጣ  ለአንተ የምሰጠው ፍትህ "ፍቅር" ብቻ ነው።

❤️ፍቅር ስለ ራስ ብቻ ማሰብ ሳይሆን ስለሌላውም ማሰብ ነው ። ፍቅር ሲታመም ሁሉም ነገር ይታመማል። ስብእናም አስተሳሰብም  ስሜትም ይታመማል ። ወዳጀ ሆይ አንተም አስተውል ያንተ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድረስላቸው ከራስህ ከፍታ ይልቅ ለሰዎችና ለሃገርህ ከበሬታ ይኑርህ ፡፡የወደቁትን አንሳ ያዘኑትን አጽናና ፍቅር ስጣቸው እርሱ ከሁሉም ይበልጣልና!!

                    ✍ ካህሊል ጂብራን

ውብ አሁን ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot


🎄በመላው ዓለም ለምትኖሩ የክርስትና እመነት ተከታይ እህት ወንድሞቻችን እንኳን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።

💛በአሉ የሰላም የፍቅርና የደስታ ይሁንልን🎄

❤️🏑 መልካም የገና  በአል 🏑


@ETHIOHUMANITY
@ETHIOHUMANITY


💡ያለፈ ጥረታችንን ሳስታውስ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ። ሃገር ስትታመም፣ ብርድ ብርድ ሲላት፣ ተስፋና ሥጋት፣ ወኔና ፍርሃት፣ ምርቃትና እርግማን - እንዳሻው ሲንጣት ከሆነብን ይልቅ እየሆነ ያለው ያሳስበኛል ፣ ከእሳቱ በላይ አያያዙ ያሰጋኛል፣ ከጥያቄው በላይ ምላሹ ይስበኛል።

📍ችግር ፈቺነት ከሚጠይቀው ጥበብ ውስጥ ዋነኛው የሚመስለኝ ለሌላ እንከን ገርበብ የማይልን በር የመተው ብልህነት ነው። አንድን ሕመም ስታክም 'ከተጠባቂው' ጎንዮሽ እንከን ውጭ ሌላ ህመም እንዳልፈጠርክ ማረጋገጥ ግዴታህ ነው። በስመ መድኃኒት የተገኘው አይደነጎርም፣ አንድ ችግር ፈትቷል ተብሎ ለሌሎች ችግሮች ሰበብ እንዲሆን አይተውም፣ በእውቀት እንጂ በደመነፍስ አይቃኝም።

💡በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ጥሞና ነው የሚያስፈልገን፣ የሰከነ ውይይት ነው የሚያሻን፣ 'ምን ብናደርግ ይበጃል?' መባባል አለብን። ጊዜው እሾህ እያወጣን ጦር የምንተክልበት አይደለም፣ እንቅፋት እየነቀልን ፈንጂ የምንቀብርበት አይደለም፣ ጀግነን አዙሪቱን እኛው ጋ የምናቆምበት እንጂ፣ የክብሪቱን እሳት እፍ በምትልበት ሰዓት ካላጠፋኸው እፍ ብሎ ያጠፋሃል።

📍'ካልደፈረሰ አይጠራም' የሚል አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ ሰዎች ዛሬም በዙሪያችን እንዳሉ ማሰብ ያደክማል፣ ሳይደፈርስ ማጥራት ከተቻለ ለምን ይደፍርስ ብሎ መጠየቅ ግን ግድ ነው። የደፈረሰ ሁሉ ይጠራል ወይ ማለትም ያስፈልጋል፣ ድፍርስ ሲጠራ ዝቃጭ እንደሚተው አለመርሳትም ደግ ነገር ነው። ምንም ብንታገል ልናስቀር የማንችለው አንድ ነገር ለውጥ ብቻ ነው፣ ለበጎ አልያም ለክፉ እንዲሆን የማድረጉ ድርሻ ግን እጃችን ላይ አለ። ችግሩ 'እንዲሆን' የምንፈልገው አለ - ሆነን ግን አንጠብቀውም.. 'እንዲመጣ' የምንሻው አለ - የምናዋጣው ግን የማይገባውን ነው።

💡በእንዲህ ያለ ቀውጢ ጊዜ ወሳኙ ሰው አንተ ነህ፣ ዘረኛ ሳይሆኑ ነው ዘረኝነትን ማረቅ የሚቻለው፣ ሳይሰርቁ ነው ዘራፊነትን ማስቆም የሚቻለው፣ አድማጭ ሆኖ ነው ጫጫታን ማስቆም የሚቻለው፣ ግማሽ መንገድ መጥቶ ነው 'እስኪ እንነጋገር' የሚባለው፣ለውጡን ተለወጠው እንጂ ከሌሎች አትጠብቀው፣ አርዓያ ሁን የሚመለከቱህ አሉ ፣ የሚከተሉህ አሉ።

ፊት መሆን በሚችል ስብዕና ከፊት ቁም፣ ጊዜህን አፍ በመካፈት አትብላው፣ ስህተት በመንቀስ አትሙላው ብሽሽቁ፣ አተካራው፣ መናቆሩ፣ ጎራ ማበጀቱ ፣ አሁን ፈጽሞ አይጠቅምም። እንዲመጣ የምትፈልገው ለውጥ አሁን አንተ ያልሆንከው ወይም የሌለህ ከሆነ ለውጡ መቼም አይመጣም መቼም!!

🔑 የትኛውም የችግር ቁልፍ የፍቅር ስሪት ከሌለው መሰበሩ አይቀርም ፣ ወደድክም ጠላህ እውነተኛውና ዘላቂው ኃይል ፍቅር ብቻ ነው ፣ የረቀቀ ሳይንስም ሆነ የጠለቀ አስተሳሰብ ፍቅርህን አያክልም፣ የገዘፈ ኃይልም ሆነ ልክ የለሽ ስልጣን ፍቅርህን አይተካም፣ የፍልስፍናህ ጥግም ሆነ የልሂቅነትህ ጠገግ አፍቃሪነትህን አይተካከልም።

የአብሮ መኖር እንከናችንን የሚደፍን ሕብር እንጂ የመለያየት ግንብ የሚገነባ መዝሙር ሰልችቶናል፣ ከነበርክበት 'የተሻለ' ብርሃን ስትፈልግ ወደ አልነበርክበት ጨለማ አለመግባትህን ማረጋገጥ ብልህነት ነው!!

  ✍ ደምስ ሰይፉ

ውብ ጊዜ ❤️

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot

Показано 20 последних публикаций.