ደርግ ዘጠነኛውን የአብዮት በዓል አስመልክቶ በጳጉሜ ወር 1975 ዓ.ም ለፖለቲካ እሥረኞች ይቅርታ ሲያደርግ ወጣቷ ልዕልት ምሕረት መኮንን ከንጉሳዊ ቤተሰብ እሥረኞች መካከል ለመለቀቅ የመጀመሪያዋ ሆነች፡፡ የደርግ “አብዮታዊ ምህረት” ሁሉንም እሥረኛ ንጉሳዊ ቤተሰብ ያካተተ ባይሆንም እሥረኞቹ እንዲፈቱ ለሚማፀኑት ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን እንደ በጐ እርምጃ ተደርጐ ተወስዷል፡፡ ተቋማቱ ምህረቱን አስመልክተው ለኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋናቸውን በማቅረብ ቀሪዎቹ እሥረኛ ንጉሳዊ ቤተሰቦች እንዲለቀቁ የተለመደውን ልመና አቅርበዋል፡፡
ደርግ ለንጉሳዊ እሥረኞቹ ያደረገው 2ኛ ምህረት የተከናወነው ከመጀመሪያው ምህረት አምስት አመት ያህል ቆይቶ ሚያዝያ 13 ቀን 1980 ዓ.ም ነበር፡፡ ከአሥራ ሁለት አመት በኋላ ከእሥር የተለቀቁት የ75 አመቷ አዛውንት ልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለሥላሴ፣ ልዕልት ሰብለ ደስታ፣ ልዕልት ሒሩት ደስታ፣ ልዕልት አይዳ ደስታ፣ ልዕልት ሶፍያ ደስታ እና ልዕልት ሳራ ግዛው ነበሩ፡፡
ደርጉ ለንጉሳዊ ቤተሰብ 2ኛውን ምህረት ከሰጠ ከአንድ አመት ከአራት ወራት በኋላ ደግሞ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ምህረት ጳጉሜ 2 ቀን 1981 ዓ.ም አደረገ፡፡ ከ13 አመታት በኋላ የተለቀቁት የንጉሳዊ ቤተሰብ እሥረኞች፣ ወርቃማውን የወጣትነት ጊዜያቸውን በወህኒ ቤት ያሳለፉት፡- ልዑል በዕደማርያም መኮንን ፣ ልዑል ሚካኤል መኮንን እና ልዑል ወሰንሰገድ መኮንን ነበሩ።