ሃሳቡን ቀድሞ ነጻ ያላወጣ ራሱን ነፃ ማውጣት አይችልም !
ምድራችን በሃሳብ የተሞላች ነች፡፡ ሰማዩ የሚያሳስብ፤ ቢያስቡት ቢያስቡት የማያልቅ ነው፡፡ ሃሳብ የሌለበት ምንም ነገር የለም፡፡ የሚታየው ዓለም በማይታይ ወይም በሰው አቅም ሊታወቅ በማይችል ስውር ሃሳብ ወይም ጥበብ ነው የተሰራው፡፡ ተፈጥሮው፣ እንስሳው፣ ነፍሳቱ፣ ቁሱ፣ ሁሉም ሃሳብ ተሸክሟል፡፡ ሰውም ከአካላዊው ተፈጥሮው ይልቅ ሃሳባዊ ተፈጥሮው ሰውነቱን ተናጋሪ ነው፡፡ ሰው በማህበራዊ ግንኙነቱ በዋናነት ሊታወቅና ከሌላው ሊለይ የሚችለው በሃሳባዊ ማንነቱ ነው፡፡ ቁመቱ፣ መልኩ፣ ቅላቱ፣ ጥቁረቱ፣ ደምግባቱ፣ ዓይኑ፣ አፍንጫው ወዘተ አካላዊ ተፈጥሮው ከመጀመሪያ ትውውቅ በኋላ የሚረሳ ነው፡፡ ዋናው መታወቂያው ሃሳቡ ሆኖ ነው የሚዘልቀው፡፡
ማሰብ ባህር ነው፤ ሃሳብ ውቅያኖስ ነው፡፡ ብልሃት የሌለው ማሰብ ከሃሳብ ውቅያኖስ ውስጥ ያሰጥማል፡፡ ዋኝቶ መውጣት የሚችል ሃሳቡን ያበሰለ የማሰብ አቅሙን ያሰፋ ብቻ ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ.... ሃሳብህ ካላሰለጠነህ ማንም አያሰለጥንህም፡፡ ከታሰርክበት የአስተሳሰብ እስራት ነጻ የምትወጣው የገዛ ሃሳብህን ነፃ ስታወጣ ነው፡፡ ሃሳቡን ነጻ ያላወጣ ራሱን ነፃ ማውጣት ይሳነዋል፡፡ የተገዢነትን መንፈስ ያላስወገደ ራሱን መግዛት አይችልም፡፡ በሌሎች ሃሳብ መገዛትን ለማቆም የራስን ሃሳብ ማጎልመስ ግድ ይላል፡፡ የራስን መንገድ መከተል መዳረሻው ነጻነት ነው፡፡ የሃሳብ ነፃነት ደግሞ በራሱ ስኬት ቢሆንም ግቡ ሕይወትን ነፃ ማውጣት ነው፡፡ የማይጨበጥ ሃሳብ ነፍስ የለውም፤ ምንም አይለውጥም፤ ሕይወትን አይቀይርም፤ አስተሳሰብን አያዘምንም፤ ሃሳብን አያሰለጥንም፡፡ መፍትሄ የሌላቸው ሃሳቦች ሊጨበጡ የማይችሉ ናቸው! ሊጨበጡ የማይችሉ ሃሳቦች ከተቆራኘን የአስተሳሰብ ባርነት አያላቅቀንም፡፡
@ እሸቱ ብሩ ይትባረክ