በሰው ልጆች የጥበብ ገበታ ላይ ዘመናትን የሚሻገሩት የጥበብ ሥራዎች የሚፈሉት ከሚያባብለውና በሣቅ የተሸፈነው የሕይወት ውጫዊ ወለል በታች በሐዘን ጥላ ሥር ይመስላል።ብዙ ሰው ሐዘንና ደስታ ሁለት የተለያየ ጣዕም ያላቸው የሕይወት መንታ ገጾች እንደሆኑ አድርጎ ያስባል።ይኼንን ሚሊዮን ምንትስ ጊዜ ታዝቤያለሁ። ሆኖም ራሱን ችሎ የሚቆም ልሙጥ ሐዘንም ሆነ ደስታ የለም።
ሐዘን ቅመም ነች፤ ጥበብን ወደ ዘለዓለማዊ ማንነት የማሸጋገሪያ ቅመም...ወዳችሁ የምትሰሟቸውን ዘፈኖች አጢኑ።አብዛኞቹ የጠየመ ሐዘን ያጠላባቸው ሆነው ታገኟቸዋላችሁ። እመኑኝ የትኛውም ሰው ንጉሥ ወይም ቱጃር፣ ወይም ውበቷ የዓለምን ሥቃይ ሁሉ ልታባብል የምትጥር ልዕልት ሁሉም በየዕለቱ በራቸውን ዘግተው ለብቻቸው የሚያለቅሱበት ዐብይ ጉዳይ አላቸው። ጥበብ ይህን ክቡድ የብቻነት ዓለም እንደ ጌጥ ጥለት እየፈተለች ትዋብበታለች።
"ከባዶ ላይ መዝገን "
ከያዕቆብ ብርሃኑ መጽሐፍ የተወሰደ