በድሀ ደንብ ክስ መመስረት
መሠረቱ
📌 በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 ላይ እንደተመለከተው በገንዘብ ሊተመኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡት ክሶች ሁሉ ዳኝነት ካልተከፈለባቸው በቀር ተቀባይነትን አያገኙም።
ግለሰቡ ለዳኝነት የሚከፍለው ገንዘብ የሌለው ከሆነ?
📌 የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 467 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ “ማናቸውም ሰው ለሚያቀርበው ክስ የሚያስፈልገውን የዳኝነት ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለመክፈል የማይችል መሆኑን ገልጾ ከዚህ በላይ ባለው ንዑስ ቁጥር በተነገረው ድንጋጌ መሠረት የነፃ ፋይል ከፍቶ ክስ ለማቅረብ እንዲፈቀድለት ለማመልከት ይችላል።” በማለት ይደነግጋል።
📌 በመሆኑም ለፍርድ ቤት ለዳኝነት የሚከፈል ገንዘብ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የሌለው ሰው ጉዳዩን በቅድሚያ በድሀ ደንብ እንዲታይለት በመጠየቅ ክሱን በማቅረብ መብን ማስከበር ይቻላል።
📌 ይህ ማለት ግን ግለሰቡ በክርክር ሂደት መሐል ሀብት ንብረት ያገኘ ከሆነ ወይም ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በሰጠው ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ወይም ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ንብረት ሦስተኛ ወገን ጥቅም ጥቅም እንዲያገኝበት ያደረገ መሆኑ ሲረጋገጥ ለዳኝነት እንዲከፍል የተተመነውን ከመክፈል የሚያስቀረው አይደለም።
ሂደቱ ምን ይመስላል?
📌 በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 468 ላይ እንደሰፈረው ከሳሽ ከሚያቀርበው መደበኛ ክስ ጋር በማድረግ በመሐላ ቃል በተደገፈ አቤቱታ ክሱ በድሀ ደንብ እንዲታይለት ከሚጠይቅ ማመልከቻ እና የሰነድ ወይም የሰው ማስረጃዎች ጋር በመሆን እንዲቀርብ ይደረጋል። በተጠየቀው አቤቱታ ላይም በቅድሚያ ተከሳሽ መልስ እንዲሰጥበት ይደረጋል።
ፍርድ ቤቱ ከሳሽ ያቀረበውን በድሀ ደንብ ክስ እንድመሰርት ይፈቀድልኝ አቤቱታን ውድቅ ያደረገው እንደሆነ ጉዳዬ ዳኝነት ሳይከፈልበት በነፃ ሊታይልኝ ይገባል በማለት ይግባኝ መጠየቅ የሚቻል ስለመሆኑ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 6 በመዝገብ ቁጥር 23744 በሆነው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።
በድሀ ደንብ ክስ ለመክፈት መሟላት ያለበት
📌 በድሀ ደንብ ክስ እንዲታይልዎት ከሚያቀርቡት ማመልከቻ ጋር
1️⃣ ከሚኖሩበት ወረዳ ለዳኝነት ሊከፈል የሚችለውን የገንዘብ መጠን ለመክፈል የማይችሉ ድሀ ስለመሆንዎት የሚያስረዳ ማስረጃ፤
2️⃣ ዳኝነት ለመክፈል የማይችሉ ስለመሆንዎት ሊያስረዱ የሚችሉ ቢያንስ 03 /ሦስት/ የሰው ምስክሮች ስም ዝርዝር።
ሆነ ብሎ ድሀ ሳይሆኑ ድሀ ነኝ ማለቱ ቅጣቱ
📌 አንድ ሰው ድሀ ሳይሆን ለፍርድ ቤት ሊከፈል የሚገባውን የዳኝነት ገንዘብ ላለመክፈል በማሰብ ብቻ በሐሰት ድሀ ነኝ ብሎ ድሀ አለመሆኑ እና ለዳኝነት ሊከፍል የሚችለው ገንዘብ ስለመኖሩ የተረጋገጠበት እንደሆነ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ መሠረት ችሎቱ ተገቢ ነው በማለት በሚያምንበት የሕግ ድንጋጌ ከ06 /ስድስት/ ወራት ቀላል እስራት እስከ 7 /ሰባት/ ዓመት ሊደስ በሚችል ጽኑ እስራት ሊያስቀጣው ይችላል።
©️ጠበቃ ቴዎድሮስ አብዲሳ
☎️ 09 10 61 69 50
በማንኛውም የፌዴራል ፍርድ ቤት
ጠበቃና የሕግ አማካሪ