የዕንቁ መምህሮቻችን ትምህርቶች🔥


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: не указана


የ ዕንቁ መምህሮቻችን ትምህርቶች የሚለቀቅበት ቻናል

Связанные каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
не указана
Статистика
Фильтр публикаций


እውነተኛ ወዳጅ፥ ወዳጅ መኾኑ የሚታወቀው ጓደኛውን መገሠጽ ሲችል ነው፡፡ ኹላችንም በየጊዜው ኃጢአት እንሠራለን፡፡ አብዛኞቻችን ደግሞ ኃጢአታችንን እንዳላየነው ኾነን ለማለፍ እንጥራለን፡፡ ለራሳችን ይቅርታ እንቸራለን፡፡ ወይም ምንም እንዳላጠፋ ሰው ለመምሰል እንሞክራለን፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰዓት እውነታውን በትክክል እናይ ዘንድ ዓይናችንን የሚከፍት እውነተኛ ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡

አንተ ሆይ! እስኪ ራስህን መርምር፡፡ ጓደኛህ እውነታውን እንዲያይ ታደርጋለህ? ጓደኛህ ኃጢአት ሠርቶ ሲያበቃ ለራሱ ይቅርታ ሲያደርግ ይቅርታው ያደረገው ይቅርታ ትክክለኛ እንዳልኾነ እንዲያውቅ ታደርጓለህን? እንዲህ እውነታውን ስትነግረው ምናልባት ጓደኛህ አለአግባብ ሊቈጣህ ይችላል፡፡ ታዲያ ሲቈጣህ ለመታገሥ ዝግጁ ነህን? ወይስ ከዚህ በተቃራኒ የጓደኛህን ኃጢአት አይተህ እንዳላየህ ነው የምትኾነው?

ጓደኛ ስንመርጥ ከእኛ ጋር እውነተኛ ወዳጅ ሊኾን የሚገባውን መኾን አለበት፤ ስንቈጣው እንኳን ቁጣችንን ታግሦ ስናጠፋ የሚያርመን ሊኾን ይገባል፡፡ እንደዚህ ካልኾነ ጓደኝነት ጥልቀት አይኖረውምና፤ ጓደኞች ነን መባባላችን ጥቅም የለውምና፡፡

ልናውቀው የሚገባን ነገር ግን አለ፡፡ ጓደኛችን በሚያጠፋበት ሰዓት ተግሣጽ አስመስለን እንዲሁ ክብሩን በሚነካ መልኩ ልንናገረው አይገባንም፡፡ ተግሣጻችን ኹልጊዜ እውነቱን ብቻ እንጂ የተጋነነና ሌላውን መልካምነቱን የሚክድ መኾን የለበትም፡፡ ጥፋቱን ስንነግረው ኹልጊዜ በቀና ልብ እንደምንነግረው እርግጠኛ እንዲኾን ማድረግ አለብን፡፡ ይህን የምናደርገው ከፍቅራችን የተነሣ እንጂ ከቅናት ወይም ከንቀት እንዳልኾነ እንዲያውቅ ማድረግ አለብን፡፡ እውነተኛ ወዳጅነት ማለት ይህ ነውና፡፡
@memhrochachn


“አንኳኩቼ አላገኘሁም” አትበል፡፡ ብቻ የለመንከው፣ ደጅ የጠናኸው አንተ የምትወደው ሳይሆን እግዚአብሔር የሚወድልህ ይሁን፡፡ ወደ እግዚአብሔር የተዘረጋ እጅ ፈጽሞ ባዶውን አይመለስም፡፡ ስለዚህ ራስህን፣ ልመናህን ምን ዓይነት እንደሆነ ፈትሽ እንጂ አንኳኩቼ አላገኘሁም አትበል፡፡ እንኳንስ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር ክፋት የሚስማማው ምድራዊ አባትም ለልጁ ጀሮውን አይደፍንም፡፡

አስቀድሞ ሕያዊት ነፍስን “እፍ” ብሎ እንዲሁ የሰጠን ጌታ፣ ኋላም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ልጁን ሳይራራ ከሰጠን እንደምን በዚህ ይታማል? እንደምንስ አይሰጠንም እንላለን? /ሮሜ.8፥32/፡፡ ልጁን የሰጠው እኮ ጭራሽ “ስጠን” ብለው ላልለመኑ አሕዛብም ጭምር ነው፡፡ ታድያ እንዲህ የምንለምን እኛማ እንዴት አብልጦ አይሰጠንም? የሚበልጠውን ሰጥቶን ሳለስ እንደምን ትንሹን አይሰጠንም እንላለን? ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀውን ሳናደርግ “እግዚአብሔር ጸሎቴን አይሰማም” የሚል የሰነፎች አባባል የምንናገር አንሁን፡፡ ጀሮን የፈጠረ ይሰማል!”

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
(ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ #በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ገጽ 178)


"አንተ ራስህ ለገዛ ወንድምህ ጨካኝና ይቅር የማትል ኾነህ ሳለስ እግዚአብሔር እንዲራራልህና እንዲምርህ እንዴት መለመን ይቻልሃል?

"ባልንጀራህ ምናልባት ንቆህ ሊኾን ይችላል፡፡ አዎ! አንተ ግን እግዚአብሔርን ኹልጊዜ እንደናቅኸው ነው፡፡ በባልንጀራና በእግዚአብሔር መካከልስ ምን ንጽጽር አለ? ባልንጀራህ ምናልባት ጉዳት ሲደርስበት ሰድቦህ ይኾናል፤ አንተም በዚህ ተበሳጭተህ ይኾናል፡፡ አንተ ግን ምንም ሳይጎዳህና በአንተ ላይ ክፉ ሳያስብ ይልቁንም ዕለት ዕለት በረከቱን እየተቀበልክ እያለ እግዚአብሔርን ሰድበኸዋል፡፡ እንግዲህ ተመልከት! ነቢዩ፡- “እመሰ ኃጢአተኑ ትትዐቀብ እግዚኦ መኑ ይቀውም - አቤቱ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ ማን ይቆማል?” ብሎ እንደ ተናገረ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የምንፈጽመውን በደል ቢመረምር ኖሮ አንዲት ቀንስ እንኳን በሕይወት መቆየት አንችልም ነበር (መዝ.129፡3)፡፡

እያንዳንዱ በደለኛ ሰው ለራሱ የሚያውቀውንና ሌላ ሰው የማይመሰክርበትን እግዚአብሔር ብቻዉን ግን የሚያውቀውንስ ይቅርና የተገለጠውና ሰው ኹሉ የሚያውቀው ኃጢአታችንን እንኳን እግዚአብሔር ቢቈጣጠር ኖሮ ከእነዚህ ኃጢአቶች በኋላ የምንጠብቀው ምንድን ነው? እግዚአብሔር ንዝህላልነታችንንና ጸሎት ስናደርስ የምናሳየው ግድየለሽነታችንን፣ ሠራተኞች ለአሠሪዎቻቸው ወታደሮችም ለአለቆቻቸው ጓደኛሞች ለጓደኞቻቸው የሚያሳዩትን ፍርሐትና ክብር ያህልስ እንኳን ለጸሎትና ለልመና በፊቱ በቆምን ጊዜ አለማሳየታችንን ቢቈጣጠር ኖሮ ምን ነበር የምንኾነው?

አንተ ከጓደኛህ ጋር ስትነጋገር ለምታደርገው ማንኛውም ነገር ትጠነቀቃለህ፡፡ ስለ በደሎችህ እግዚአብሔርን ስትጠብቀው፣ ለብዙ መተላለፎችህ ይቅርታን ስትጠይቀው፣ ሥርየትን ለማግኘት ስታሳስበው ግን [በፊቱ ላይ] ኹልጊዜ ግድየለሽ ትኾናለህ፡፡ ጉልበትህ በምድር ላይ ተንበርክኮ ሳለ ልቡናህ ግን እዚህም እዚያም፣ በገበያ ሥፍራም፣ በቤት ውስጥም ይዋልላል፤ ከንፈርህ በከንቱና እንዲሁ ያነበንባል፤ ይህን የምንፈጽመው ደግሞ አንዴ ወይም ኹለቴ ሳይኾን ኹልጊዜ ነው።

እንግዲህ እግዚአብሔር ይህን ብቻ እንኳን ቢመረምር ይቅርታን ወይም ምሕረትን እንደምናገኝ ታስባለህን? በእውነት አይመስለኝም!"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ትምህርት_በእንተ_ሐውልታት_መጽሐፍ
ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው


ጌታችን ለወንበዴው


«ወደ መሬት ወድቀን በሰገድን ጊዜ ኃጢአት እንዴት ወደ ታች ጎትታ እንደጣለችን እናስታውሳለን። ዳግመኛም ከወደቅንበት በተነሣን ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ እና ምሕረት እንዴት ከመሬት እንዳነሣንና የሰማዩን ርስት እንደሰጠን እንመሰክራለን» ቅዱስ ባስልዮስ ዘየዐቢ


   ቃለ እግዚአብሔርን በአእምሮ ያይደለ በልብ መማር ወደ ፍቅር መልክ ያደርሳል፡፡ ሰፊ ጊዜን ሰጥቶ የአምላክን ቃል ከአንጀት መማር ፍቅርን ያሳድጋል፡፡ ለምን ቢሉ..."የእግዚአብሔር ቃል" በራሱ ፍቅር ነውና፡፡ እርሱ ሥጋ ለብሶ በዓለም ላይ የፍቅር ድምፆችን (ወንጌል) እንዳሰማ ሁሉ፤ ድምፁን ከእውነት በሰማን ጊዜ ፍቅርነቱ ከውስጣችን ሥጋ ይለብሳል፡፡ በአሳብ፣ በእቅድ፣ በድርጊት፣ በአኗኗር ውስጥ ዘልቆ ይገለጻል፡፡ ቃሉ "መንፈስና ሕይወት" ነው፡፡

@mehrochachn


"ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ የክርስቶስንም ፀጋና ክብር ሳይፈተኑ ማግኘት አይቻልም የዚህ ዓለም ፈተናና እሳት ቶሎ ያልፋል ይጠፋል ኃጢያተኞች የሚገቡበት የገሀነም እሳት ግን ለዘላለም እንደ ነደደ ይኖራል።"
#ቅዱስ_ሚናስ


ሰው ሁን!

✿ ሰው ከመሆንህ በፊት #ዶክተር (ሐኪም) አትሁን፡፡
✿ ሰው ከመሆንህ በፊት #መሐንዲስ አትሁን፡፡
✿ ሰው ከመሆንህ በፊት #መምህር አትሁን፡፡
✿ ሰው ከመሆንህ በፊት #ፖለቲከኛ አትሁን፡፡
✿ ሰው ከመሆንህ በፊት #ጋዜጠኛ አትሁን፡፡
✿ ሰው ከመሆንህ በፊት #መሪ፣ #መካሪ፣ #አውሪ፣ #ዘማሪ፣ #ጸሐፊ፣ #ለጣፊ፣ #ሰባኪ፣ #ሹመኛ፣ #ወገኛ.... ሌላም አትሁን፡፡

ዓለም፣ ኢትዮጵያ፣ ቤተ ክርስቲያንም ያጣችው ይህንን ሁሉ አይደለም፡፡ ሰው የሚሆንላትን እንጂ፡፡ ይልቁንስ ከሁሉ በፊት ሰው ሁን፡፡ ሰው መሆን ከእነዚህ ሁሉ የተሻለ ማንነት ነውና፡፡

"ሰብአዊነት የጎደለው ሙያ በመርዝ ዕቃ ላይ እንደተቀመጠ ጣፋጭ ምግብ ነው" ይላሉ አበው፡፡ የችግሮቻችን ሁሉ መነሻም ሰብአዊነት የጎደለው ግብራችን ነው፡፡

መጽሐፍስ ምን አለ? "ሰው ሁን፡፡" (1ነገ. 2፡3)

✿ሰው ለመሆን ያብቃን፡፡

(#ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)


"ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።

የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። "

ማቴ. 5÷43-47


«ለመተኛት ወደ አልጋህ ባመራህ በቀረብህ ጊዜ አልጋዬ፡ ምን አልባት በዚህ ሌሊት ለእኔ መቃብሬ ልትኾኚ ይኾን ይኾናል፤ በጊዜአዊው ዕንቅልፍ ፈንታ በዚህ ሌሊት ያኛው እንቅልፍ (ሞት) ይመጣብኝም እንደ ኾነ አላውቀውም በላት ።ስለዚህ ነጻ እግሮች እያሉህ ከመልካም ሥራ በኋላ ሩጥ፤ ከታሠሩ መፈታት በማይችሉበት ማሰሪያ ከመታሠራቸው በፊት፡፡ የእጆችህ ጣቶችም እስካሉህ ድረስ ሞት ከመምጣቱ በፊት በጸሎት ፊትህንና መላ ሰውነትህን በተእምርተ መስቀል አማትብ፡፡ ዐይኖች እስካሉህ ድረስ በአቧራ ከመሽፈናቸው በፊት በእንብዕ(በእንባ) ምላቸው።ሰው ሆይ ከዚህ ዓለም መለየትህን አስብ፣ እንዲህም በል፡- እነሆ የታዘዘ መልአክ ከበር ቆሞአል (ደርሶአል)፣ እኔንም ይከተለኛል። ለምን ሊል ዘሊል እኾናለሁ? መመለሻ የሌለው ዘለዓለማዊ መንገድ አለ፡፡መለኮት ደግነት የተነሣ የሰውን ልብ የሚገዛውና ነፍስን ወደ ሕይወት የሚመራት የመጀመሪያው ትምህርት ተዘክሮተ ሞት ነው።.ተዘክሮተ ሞት በሰይጣን እጅግ በብዙ ይጠላል፡፡ እርሱም ከሰው ተዘክሮን ለመንቀል በሙሉ ኃይሉ መሞከርን አይተዉም፡፡ የሚቻለውስ ቢኾን በምድራዊ ሕይወት አሳብ ተብትቦ ተዘክሮተ ሞትን ከሰው ልብ (አእምሮ) ለማስወገድ ምድራዊ መንግሥታትን ለሰው በሰጠው ነበር፡፡ አታላዩ ሰይጣን ተዘክሮተ ሞት በሰው ሁልጊዜም ካለ፣ አሳቡ ለአሁኑ ሕይወት መታለሎች የተጣበቀ ኾኖ እንደማይቀር አልያም የሰይጣን ማታለሎች ሰውን ሊቀርቡት እንደማይችሉ ያውቃል፡፡"

ማር ይስሐቅ ሶርያዊ

@memhrochachn


#ትሕትና

በትክክል ትሑት የኾነ ሰው ማን እንደ ኾነ ማወቅ ትወድዳለህን? በእውነት ያለ ሐሰት ትሑት የነበረውን ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስን ተመልከት፡፡ መምህረ ዓለም፣ መንፈሳዊ አንደበተ ርቱዕ፣ ንዋይ ኅሩይ፣ ወጀብ የሌለበት ወደብ፣ የማይናወጽ ግንብ፣ በአካለ ሥጋ ትንሽ ሲኾን አክናፍ እንደ ተሰጡት ኾኖ ምድርን ኹሉ ያካለለውን ጳውሎስን ተመልከት፡፡ ያልተማረው ግን ደግሞ የተራቀቀውን፣ ድኻ ግን ደግሞ ባለጠጋ የኾነውን ይህን ቅዱስ ሰው ተመልከት፡፡ እልፍ ጊዜ መከራዎችን የተቀበለው፣ አእላፋት ጊዜ ዲያብሎስን ድል የነሣው፣ “ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም፤ ከኹላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ” ብሎ የተናገረው ተወዳጅ ጳውሎስን በእውነት ያለ ሐሰት ትሑት ነው ብዬ እጠራዋለሁ (1ኛ ቆሮ.15፡10)፡፡ ብዙ ጊዜ መታሰርን፣ ብዙ ጊዜ መገረፍን፣ ብዙ ጊዜ በድንጋይ መወገርን፣ [ከበረኻ አራዊት ጋር መጋደልን፣ በባሕር ውስጥ ለሦስት ቀናት ሲዋኝ ውሎ ሲዋኝ ማደርን፣ ቀንና ሌሊት ብዙ ጦምን፣ በብርድና በራቁትነት መኾንን] የታገሠ የተቀበለ፣ በመልእክታቱ ዓለምን በወንጌል መረብነት ያጠመደ፣ ከሰማያት በመጣ ሰማያዊ ቃል የተጠራው እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ፡- “እኔ ከሐዋርያት ኹሉ የማንስ ነኝ” ያለውን ብፁዕ ጳውሎስ አማን በአማን ትሑት ነው ብዬ እጠራዋለሁ (2ኛ ቆሮ.11፡23-27)፡፡

እንግዲህ የቅዱስ ጳውሎስን የትሕትናው ታላቅነት ታያለህን? ራሱን ዝቅ አድርጎ ታናሽ ነኝ ሲል ትመለከታለህን? “እኔ” አለ ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ከሐዋርያት ኹሉ የማንስ፤ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ፡፡” በትክክል ትሕትና ማለት ይህ ነው - በኹሉም ረገድ ራስን ዝቅ ማድረግ! ራስን እንደ ታናሽ መቊጠር! እነዚህን ኃይላተ ቃላት የተናገራቸው ማን እንደ ኾነ በነቂሐ ልቡና በሰቂለ ሕሊና ኾነህ አድምጥ! የሰማይ ሰው የምድር መልአክ የሚኾን ጳውሎስ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ዓምድ የሚኾን ጳውሎስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስን እጅግ አብልጬ የምወደውም ለዚህ ነው፡፡ ምግባር ትሩፋት ሥጋ ለብሳ ሥግው ኾና ተውባ ተሞሻሽራ የማያት በእርሱ በብፁዕ ጳውሎስ ዘንድ ነውና፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ፊት በዓይነ ሕሊናዬ ተቀርፆ የሚሰጠኝን ተድላ ደስታ ያህል የብርሃን ጮራዋን የምትለግሰው ፀሐይ ለዓይኖቼ ደስታን አትሰጠኝም፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ፀሐይ የሥጋ ዓይኖቼ በብርሃን እንዲያዩ ታደርጋቸዋለች፤ ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ ግን ዓይነ ልቡናዬ አክናፍ ኑሮት ወደ ሰማየ ሰማያት እንድወጣ ያደርግልኛል፡፡ ነፍስን ከፀሕይ ይልቅ ጽድልት፣ ከጨረቃም ይልቅ ልዕልት እንድትኾን ያደርጋል፡፡ የምግባር የትሩፋት ኃይሏ ሥልጣኗ ይህን ያህል ነውና - ሰውን መልአክ ታደርገዋለች ፡፡ ነፍስ አክናፍ አውጥታ ወደ ሰማየ ሰማያት እንድትበር ታደርጋለች፡፡ ተወዳጅ ጳውሎስም የሚያስተምረን ይህንን ነው - ምግባርን ! ስለዚህ ነቅተን ተግተን በምግባሩ አብነት እናደርገው፤ እርሱን እንምሰል፡፡

#ንስሓና_ምጽዋት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው


ቤተክርስቲያንን በሁለት መንገድ ማወቅህን አረጋግጥ። እንደ አሕዛብ ጠላቷ እንዳትሆን #በትምህርት_ዕወቃት፤ እንደ ፈሪሳውያን እንዳትሆን #በኑሮ_ዕወቃት። ለሥርዓቷ ታማኝ ሁን፥ አንተ ወደ ሥርዓቷ እደግ እንጅ ሥርዓቷ ወደ አንተ ፈቃድ እንዲወርድልህ አትውደድ፤ ሰማያውይቷን ቤተክርሰቲያን ምድራዊት እንድትሆንልህ አትፍቀድ።

በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አንድነቶች ካልተሳተፍክ ከቤተክርስቲያን አንድነት እየተለየህ እንደሆነ እወቅ። እሊህም፦ ኪዳን ማስደረስ፥ ማስቀደስና ንስሐ ገብቶ መቁረብ፥ በምህላ ጸሎቶቿ በአዋጅ አጽዋማቷ መተባበር ናቸው።

ከቤት ከሚጸለይ አሥር ጸሎት ይልቅ በቤተክርስታያን የሚደረግ አንድ ጸሎት እንደሚበልጥ አውቀህ በየቀኑ ወደ እርስዋ ገሥግሥ። በሕይወትህ ሁሉ ቤተክርስቲያናዊ ሁን!

#ርዕሰ_ሊቃውንት_አባ_ገብረ_ኪዳን


የሕይወትህን መንገድ ወደ እግዚአብሔር ብታደርግ ያን ጊዜ እውነተኛውን እረፍት ታገኛለህ።

አባ ሙሴ ጸሊም


እንዳይፈረድብህ በባልንጀራህ ላይ አትፍረድ

በአንድ ወቅት በግብጽ ገዳማት አንድ ወጣኒ መነኩሴ “ጥፋት አጠፋ፣ ሥርዓተ ገዳም አፋለሰ” ተብሎ መናንያኑ ጉዳዩን እንዲያዩና እንዲወስኑበት ከየበአታቸው ተጠሩ፡፡ ከተጠሩት መነኮሳት መካከል አንዱ ጥቁሩ ኢትዮጵያዊው ሙሴ ጸሊም ነበር፡፡ እርሱም ሁሉም ከተሰበሰቡ በኋላ ዘግይቶ በተቀደደ አቁማዳ አሸዋ በጀርባው አዝሎ አሸዋውን ከኋላው እያፈሰሰ መጥቶ በመሃላቸው ተገኘ፡፡

የተሰበሰቡት መነኮሳትም አባ ሙሴን ይህን ስለምን አደረግከው ብለው በጠየቁት ጊዜ በሀዘን ተውጦ “በጀርባዬ የማላያቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኃጢአቶቼን ተሸክሜ ሳለሁ በወንድሜ ለመፍረድ መጥቻለሁ” አላቸው፡፡ መነኮሳቱም እጅግ ተጸጸቱ፡፡ ጉባኤውም ፍርዱን ትቶ ተበተነ፡፡

“እንዳይፈረድብህ በባልንጀራህ አትፍረድ” የሚለውን የወንጌል ቃልም በተግባር አስተማራቸው፡፡ልብን በሚነካ በዚህ በጎ ትምህርቱም መነኮሳቱን ከመፍረድ ሃጢአት ታደጋቸው፡፡


አንድ በጣም ትልቅ ቆሻሻ የጫነ ጋሪ የሚገፋ ሰው ወደ ቤትህ መጥቶ "እባክህ በርህን ክፈትልኝና ይህን ቆሻሻ አንተ ቤት ላራግፈው?" ቢልህ፣ "ውይ የሚጥልበት ቢያጣ ነው። ባይቸገር ወደ እኔ አይመጣም ነበር" ብለህ ደጅህን ከፍተህ ታስገባዋለህ? በፍጹም፤ እንደውም "እንዴት ብታስበኝ ነው? ምነው ስታየው ቤት አልመሰለህም? እንዴት ሰው በሚኖርበት ቤት ቆሻሻ ካልደፋሁ ትላለህ? ስትል ለጠብ ትጋበዛለህ። መደፈርህ እያንገበገበህ "እምቢ!" ብለህ ትቆጣለህ። በእርግጥም ያስቆጣል።

ግን ሌላ የሚከፋ ሽታ ያለው ቆሻሻን ጭኖ ለመጣ ባላጋራ እኮ በፈቃድህ የከፈትከው ቤት አለ። "የምን ቤት?" ብለህ ብትጠይቀኝ "ልብህ ነዋ" ብዬ እመልስልሃለሁ፤ "ማን ይኖርበታል?" ካልኸኝም "እግዚአብሔር ነዋ" እልሃለሁ።

አንተ ለመኖሪያ ቤትህ ጽዳት የምትጠነቀቀውን ያህል የያዕቆብ አምላክ ለሚያርፍበት ኅሊናህ ተጠንቅቀህ ታውቃለህ? ሰይጣን ጭኖ የሚያመጣውን የኃጢአት ቆሻሻ ሁሉ እሺ ብለህ ወደ ልብህ በማስገባት የፈጣሪህን መቅደስ ለምን ታቆሽሻለህ? ንጹሑ እግዚአብሔር የሚያድርበትን ቤት ሊያቆሽሽ በመጣ ሰይጣን ላይ እንዴት አልተቆጣህም? ድፍረቱ ለምን አላብከነከነህም?

እግዚአብሔር አንተ ልትኖርበት ከምትፈልገው ንጹሕ ቤት የበለጠ ጽዱ መቅደስ የማይፈልግ ይመስልሃል?

(Dn Abel Kassahun Mekuria )
@memhrochachn


#ጾም መድኃኒት ናት፡፡ አወሳሰድዋን በትክክል ላላወቁ ግን ጥቅም የላትም፡፡ ይህችን መድኃኒት የሚወስድ ሰው በየስንት ሰዓቱና በምን ያህል መጠን እንደምትወሰድ፣ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው አከባቢና የአየር ኹናቴ እንደምትወሰድ፣ ከእርሷ ጋር የሚኼዱና የማይኼዱ ምግቦችን እንዲሁም ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ሌሎች ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡

እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብቶ የማይወስዳት ሰው ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ታመዝንበታለች፡፡ አንድ በሐኪም የታዘዘልንን የደዌ ዘሥጋ መድኃኒት እንዲያሽለን ስንፈልግ በጥንቃቄ ልንወስደው ያስፈልጋል፤ የነፍሳችንን ደዌና በአእምሮአችን ውስጥ ያሉ ቁስሎችን ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ የበለጠ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
በእንተ ሐውልታት መጽሐፍ፣ ድርሳን 3፥8


“እንደ እባብ ልባሞች ኹኑ” /ማቴ.10፡16/

እባብ ራሱን (ጭንቅላቱን) ለማዳን ሲል ሌላው ሰውነቱን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ኹሉ አንተም እንዲህ አድርግ፡፡ ሃይማኖትህን ለመጠበቅ ስትል ሀብትህን ወይም ሰውነትህን ወይም የዚህ ዓለም ሕይወትህን ወይም ያለህን ኹሉ እንኳን መስጠት ካለብህ ይህን በማድረግህ በፍጹም አትዘን! አንተ ሃይማኖትህን ይዘህ ወደ ወዲያኛው ዓለም ስትሔድ እግዚአብሔር ደግሞ ኹሉም ነገር እጅግ ውብ አድርጎ ይመልስልሃል፤ ሰውነትህን በታላቅ ክብር ያስነሣልሃል፤ ከሀብት ከንብረት ይልቅም ከመግለጽ ኃይል በላይ የኾኑ በጎ በጎ ነገሮችን ይሰጥሃል፡፡ ኢዮብ ዕራቁቱን ኾኖ በአመድ ላይ ከሞት እልፍ ጊዜ የሚከፋ ሕይወትን እየመራ የተቀመጠ አይደለምን? ነገር ግን ሃይማኖቱን ስላልጣለ አስቀድሞ የነበረው ኹሉ እጅግ በዝቶ ተመልሶለታል፤ ጤናውና ውብ የኾነ ሰውነቱ፣ ልጆችን፣ ሀብቱን፣ ከዚህ ኹሉ የሚበልጥ ደግሞ አክሊለ ትዕግሥትን አግኝቷል፡፡

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - #ገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ)


"አዳም ወደ ነበረበት ምግብን ያልተመረኮዘ ኑሮ ምን እንደሚመስል ለማየት የምትፈልግ ከሆነ ብቸኛው መንገድ ጾም ነው፡፡ አብዝቶ የሚጾም ሰው ከምግብ ምርኮኛነት ወጥቶ የጥንተ ተፈጥሮ ማንነቱን ለማግኘት የሚታገል ሰው ሲሆን በዚህም ብዙዎች ተጠቅመው በሕይወት ሳሉ የገነትን ኑሮ ምንነት ተረድተዋል፡፡ እንደነ አባ እንጦንስ ያሉትን ጾመኞች ሰይጣን 'ከመጀመሪያው ሰው አዳም ወዲህ አንዲህ ያለ ሰው አልገጠመኝም' ብሎ የተደነቀባቸው ለዚህ ነው፡፡ ጾም አያስፈልግም እያለ የሚከራከር ሰው ደግሞ 'እርግማኔን አትንኩብኝ ምግብን አንደተደገፍኩ ልኑር' የሚል ይመስላል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ 'ሆዳቸው አምላካቸው' ከተባሉት ወገን ነው፡፡ ፊልጵ. ፫፥፲፱"

"የብርሃን እናት" በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

እኛስ እየጾምን ነው ወይስ 'የቄሶች ጾም ነው' ብለን ትተነዋል⁉️

@memhrochachn


✝ የተስፋ ቃላት

📖 እኛ ዛሬ ወደፊት የምንኖርባት #የእግዚአብሔር ሀገር በተስፋ ዓይኖቻችን ልንመለከት እንጂ ይሁን ሁካታና ግርግር የበዛበት ዓለም ልንመለከት አይገባም።

📖 ለእኛ በጣም አስቸጋሪ መስሎ የሚታየን ችግር #በእግዚአብሔር ዘንድ መፍትሔ አሉትም። ማንኛውም የተዘጋ በር ለመክፈት በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ቁልፍ አንድ ብቻ ሳሆን ብዙ ቁልፎች ናቸው። በእንደዚህ ዓይነት መንገድ የተከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም ፡፡ ራዕ 3፥7።

📖 ተስፋ ፍርሀትን ጭንቀትን ግራ መጋባትን በመከላከል ዕረፍትን ይሰጣል።ተስፋ ዕረፍትን ከመጠቱ በላይ በተስፋ ደስ እንዲለን ተነግሮናል። ሮሜ 12፡2

📖 መጥፎውን ወደ በጎ መቀየር የሚቻለውን #የእግዚአብሔር አሠራር ሳትይዝ ወደ ችግሮችህ ብቻ አትመልከት።

📖 #እግዚአብሔር ሁሉም አጋጣሚዎች እርሱ በወደድው መንገድ ማስኬድ ይቻለዋል።

📖 በሰዎች ድካም ሊደረግ የማይቻለው ሁሉ #በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ይቻላል። የሰዎች ጥበብ ሊወጣው ያልቻለውንም #የእግዚአብሔር ጥበብ ያመጣዋል።

📖 ምንጊዜም በመለከታዊ ዕርዳታ የተከበብክ ስለሆንህ ብቻህን ላለመሆንህ እርግጠኛ ሁን፡፡
የሰማያት ወዳጆቻችንና ቅዱሳን ሁሉ በአንተ ዙርያ ሁነው ስለ አንተ እንደሚማልዱም እወቅ።

#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ
የተስፋ ሕይወት ከሚለው መጽሐፋቸው


....አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ! ታዲያ በራስህ ላይ ብዙ ጉዳትን የምታከማቸው ለምንድን ነው? አንድ ሰው የቱንም ያህል ጉዳት ቢያደርስብህም እንኳን አንተ በራስህ ላይ የምታደርሰውን ጉዳት ያህል እርሱ በአንተ ላይ ጉዳት አያደርስብህም፡፡ ጉዳት ካደረሰብህ ሰው ጋር ባለመታረቅህ ሕገ እግዚአብሔርን ከእግርህ በታች ረግጠሃልና፡፡ ጠላትህ ሰደበህን? ታዲያ እስኪ ንገረኝ! እግዚአብሔርን የምትሰድበው በዚህ ምክንያት ነውን? ከጠላትህ ጋር አለመታረቅ ማለት ጠላትህን መበቀል ማለት ሳይኾን ታረቁ ብሎ ሕግን የሰጠ እግዚአብሔርን መስደብ ነዋ!

ስለዚህ ባልንጀራህን አትናቀው፤ ያደረሰብህን በደልም አግንነህ አትመልከተው፡፡ ከዚህ ይልቅ በሕሊናህ እግዚአብሔርንና ፈሪሐ እግዚአብሔርን ስታስብ የሚከተለውን ነገር ልብ በለው፡፡ አዎ! ስፍር ቍጥር የሌለው በደል ደርሶብህ ሊኾን ይችላል፡፡ ውስጥህ ብዙ ተጎድቶ ሊኾን ይችላል፡፡ አንተ ግን ራስህን በኃይል ከዚህ አውጣው፡፡ አውጣውና ጎዳኝ ከምትለው ሰው ጋር ታረቅ፡፡ ይህን ስታደርግም ይህ እንዲደረግ ባዘዘው በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ የኾነ ባለሟልነትን ታገኛለህ፡፡ ታላቅ የኾነ ክብርን ትጎናጸፋለህ፡፡ አንተ ትእዛዙን በመተግበር እግዚአብሔርን በዚህ በምድር አክብረኸዋልና እርሱም በላይ በሰማያት በታላቅ ክብር ይቀበልሃል፡፡ አንተ አሁን ላሳያሃት ጥቂቷን እርሱም በሰማያት እልፍ ዕጥፍ አድርጎ ይከፍልሃል፡፡

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - አምስቱ የንስሐ መንገዶች - ገጽ 45-46 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ)

Показано 20 последних публикаций.

2 146

подписчиков
Статистика канала