⭐️⭐️
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ስያሜዎች፩. ዕለተ ሰኑይ ☀️
➡️
ሀ. አንጽሖተ ቤተ መቅደስ፡- በዚች ዕለት መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ በዚያም በደረሰ ጊዜ ቤተ መቅደሱ የጸሎት የመሥዋዕት ቤት መሆኑ ቀርቶ የንግድ ቤት ሆኖ ቢያገኘው ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው ገርፎም አስወጣቸው፡፡ ይኸውም የእርሱ ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን ኃጢአት ሰፍኖበት ቢያገኘው ራሱ ተገርፎ ተገፍፎ መከራ መስቀልንም ሁሉ ተቀብሎ ከሰውነታችን ኃጢአትን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ.፲፱፥፵፮)
➡️
ለ. መርገመ በለስ፡- ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግስቱ ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ፤ በመንገድም ሲያልፍ ቅጠል ያላት በለስን ከሩቁ ተመለከተ፡፡ ወደ በለሲቱም በቀረበ ጊዜ ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ያንጊዜም ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ከአንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር›› ሲል በለሲቱን ረገማት፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህንን ሰሙት፡፡ በዚህም ምክንያት ይህች ዕለት በለሲቱ የተረገመችባት ቀን ናትና መርገመ በለስ ተብላ ትጠራለች፡፡ (ማር.፲፩፥፲፩-፲፬)
በዚህ አገላለጽ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ስትሆን ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ነው፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈልጎ አላገኘባቸውም፡፡ እስራኤል፦ ሕዝበ እግዚአብሔር፣ የአብርሃም ዘር መባልን እንጂ የአብርሃምን ሥራ በመሥራት በምግባር በሃይማኖት ጸንተው መኖር አይፈልጉምና ደግ ሰው አልተገኘባቸውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በለስ የተባለች ኦሪት ናት፡፡ ኦሪት በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛትም አማናዊ ድኅነትን የምታሰጥ ሆና አላገኛትም፡፡ ይሁን እንጂ በእርሷ ድኅነት ባይገኝባትም ‹‹ኦሪትና ነቢያትን ከመፈጸም በቀር ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ›› በማለት ሕገ ኦሪትን ፈጽሟታል፡፡ ከዚህም ባሻገር በለስ የተባለች ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አግኝቷታል፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ለጊዜው ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም በአንቺ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ሲል ነው፡፡ በለሲቱ ስትረገም ፈጥና መድረቋም በአዳም ምክንያት ያገኘን በደል በእርሱ እንደጠፋልን ለመግለጽ ነው፡፡ 💖💖
@orthodox_graphics_tube_et 🌟