"ሀፍሲ"
|| ክፍል አስራ አራት ∞ ①④
(የመጨረሻዉ መጨረሻ)
|| ፀሐፊ፦ ∞ ኑዕማን ኢድሪስ
... በኡስማን የሚመራዉ የዐመሉ ሷሊህን ጀመዓ አባላቶች አዲስ አበባ ገብተዉ ወደ ግል ስራቸዉ ከተመለሱ ሰነባበቱ። ሀፍሲ ለጀመዓዉ ስራ ወደ ሻሸመኔ ስትሄድ ጥናታዊ ፅሁፏን ያቋረጠችዉ ቢሆንም በቀራት የተወሰኑ ቀናቶች ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች።
ኡስማን፤ ሸህ አጃኢቡ ና ሙባረክ በጀመዓዉ ቢሮ ተገናኘተዉ ስለተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እያወሩ ቢሆንም በዋነኝነት ያገናኛቸዉ ነገር ሸህ አጃኢቡ የሀፍሲን ምላሽ ለኡስማን ሊነግሩት ነዉ። በወሬያቸዉ መካከል "በል ለሰርጉ ተዘጋጅ!" አሉት። ኡስማን እንደመደንገጥ አለና "ተስማማች እንዴ ኡስታዝ?" ብሎ ጠየቃቸዉ።
"ተስማምታለች ልጄ! የቀረዉን ተገናኝታችሁ አዉሩና ቶሎ ተጋቡ!" አሉት። ሸህ አጃኢቡ ለነኡስማን እንደ መምህር ብቻ ሳይሆን እንደ አባትም ያስቡላቸዋል። አጉል ቦታ ወድቀዉ ሀራም ነገር እንዲሰሩ አይሹም። በመሀል የሸህ አጃኢቡ ስልክ ጠራ ዴቭ ነበር የደወለላቸዉ።
"ሄሎ ልጄ ዳዉድ..." አሉት። ሙባረክ ሁሉንም ሚያወሩትን እያስተዋለ ነዉ። በሀፍሲ መኪና ወደ ሻሸመኔ ሲሄዱ ዴቭን እንደምታፈቅረዉና ልትጠይቀዉ እንደሆነ ነግረዋለች። ከሻሸመኔ ሲመለሱ ደግሞ ዴቭ ሚወዳት ልጅ እስልምናን ልትቀበል እንደሆነ ነግሯታል። "ኡስማንን እሺ ያለችዉ ምን አስባ ነዉ?" እያለ ማስተንተን ጀመረ።
ሸህ አጃኢቡና ዴቭ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኃላ የት እንዳሉና እንደሚፈልጋቸዉ ነገራቸዉ። ሀና ልትሰልም በመሆኑ ከሸህ አጃኢቡ ጣፋጭ አንደበት ሸሀዳ እንድትይዝ (የአላህን አንድነትና የተወዳጁን ነብይ ሙሀመድ መልክክተኝነት እንድትመሰክር) ፈልጎ ነዉ።
..."ዴቭ ደስተኛ ይመስላል ማሻ አላህ" አሉ ሸኽ አጃኢቡ። ሙባረክ በአይኖቹ ኡስታዙንና ኡስማንን እያፈራረቀ ከተመለከተ በኃላ ዉስጡን የሚረብሸዉን ነገር ሊናገር ፈለገ። "እኔ ግን በሀፍሲ ጉዳይ ያልገባኝ ነገር አለ" አላቸዉ። ኡስማን የሚጽፈዉን ነገር አቋርጦ ቀና አለ። "ምድን ነዉ ያልገባህ ሙቤ?" አለዉ። ኡስማን ከሙባረክ የሚደብቀዉ ነገር የለም። ሀፍን ማሰብ ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ሙባረክ የኡስማን ሚስጥረኛዉና አማካሪዉ በመሆኑ ሚደባበቁት ነገር የለም። ሸህ አጃኢቡም "ምንድን ነዉ እሱ ልጄ?" ብለዉ ጠየቁት።
"ወደ ሻሸመኔ ሀፍሲ ጋር እንደሄድኩ ታዉቃላችኃ?" አላቸዉ ሙባረክ። ሁለታቸዉም አንገታቸዉን ወደ ላይና ወደ ታች በመነቅነቅ እንደሚያዉቁ ገለፁለት።
"... ከሀፍሲ ጋር ስሄድ ዴቭን እንደምታፈቅረዉና ሻሸመኔ ፍቅሯን አዉጥታ እንደምትነግረዉ ነግራኝ ነበር። እንዲያዉም..." ብሎ ንግግሩን ቀጠለ ኡስማንና ሸህ አጃኢቡ በትኩረት እያዳመጡት ነበር። "... እንዲያዉም የዚያን ቀን ማታ ራት ሊበሉ አብረዉ ወጥተዉ ነበር።..." ኡስማን አንገቱን ነቀነቀ። ወደ ሸህ አጃኢቡ ዞሮ እኔና አንቱ መኪና ዉስጥ ተቀምጠን" ሲላቸዉ እሳቸዉም አስታወሱ። ሙባረክ ንግግሩን ቀጠለ "ዴቭ ሚወዳት ሴት እንዳለችና ከሷም ልጅ እንዳለዉ ሳይነግራት አይቀርም" አላቸዉ። ሁለቱም ደነገጡ ስለ ዴቭ ምንም ነገር አያዉቁም።
"እዉነትህ ነዉ?" አለዉ ኡስማን።
"አዎ ይሄንን የሰማሁት ከዴቭ ጋር ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ሚወዳት ልጅ ደዉላለት እስልምናን ልትቀበል እንደነበር ነግራዉ በጣም ደስተኛ ሆኖ ነበር!" ብሎ አረጋገጠላቸዉ። ሸህ አጃኢቡ ዳዉድ የሚወዳት ልጅ እስልምናን ልትቀበል በመሆኗ ደስ ስላላቸዉ "ማሻ አላህ!" አሉ። ሙባረክም ያልተዋጠለትን ነገር ለመጠየቅ ሁለቱም በየተራ ካዬ በኃላ "ሀፍሲ ዴቭን እያፈቀረችዉ የኡስማንን ጥያቄ እንዴት ተቀበለች?" ብሎ ጠየቀ። በመካከላቸዉ ጸጥታ ሰፈነ። በየራሳቸዉ መንገድ ነገሮችን ወደ ኃላ መለስ ብለዉ ማጤን ጀመሩ።
.
ቀናቶች እየነጎዱ ነዉ። ሀፍሲ የጥናት ጽሁፏን የዴቭ ፍቅር እያጎሳቆላትም ቢሆን በማጠናቀቅ ላይ ነች። ስትሄድ፤ ስትነሳ፤ ስትቀመጥና ስተትኛ በየትኛዉም ሁኔታ ላይ የዴቭ ፍቅር ልቧን እንደሰለባት ነዉ። ከዉስጧ የማይወጣ ነበልባል ሆኖባታል። ሀና እስልምናን ስለተቀበለች ዴቭ የልጁን እናት ለማግባት እየተሰናዳ ነዉ። የሰርጋቸዉ ቀን ተወስኖ ለዘመድ አዝማድ፤ ለወዳጅ ጓደኛ የሰርግ ጥሪ ወረቀት ተበትኗል። የዴቭ የሰርግ ጥሪ ከደረሳቸዉ የቅርብ ጓደኞች መካከል አንዷ ሀፍሲ ናት!። ህመሟ ብሷል። ነገሮች ፈጥነዉ የዴቭን ፍቅር ለመርሳት ኡስማን እንዲያገባት ተመኘች!።
... መኝታ ክፍሉ አልጋዉ ላይ ጋደም ብሎ ነገሮችን በጥልቅት ያስታዉስ ጀመር። "እንደ ወንድሜ ነዉ የማይህ!" የሚለዉ የሀፍሲ ንግግር ጆሮዉ ስር ያቃጭልበታል። "ሀፍሲ አታፈቅረኝም። የትዳር ጥያቄዬን የተቀበለችዉ ምናልባት የምታፈቅረዉ ሰዉ የሌላ ሰዉ ስለሆነ ይሆናል። ..." በተረጋጋ መንፈስ እያስተዋለ ነዉ። በዚህ መካከል ሀያት የስልክ መልእክት ላከችለት። "አሰላሙዓለይኩም ኡስሚ እንዴት ነህ? የዉስጤን አዉጥቼ ሳልነግርህ ከአንድ አመት በላይ አፍቅሬሀለሁ ስሜቴን ከነገርኩህ በኃላ ግን መልስህን በመጠበቅ በጣም ጓጉቻለሁ!" አለችዉ። መልእክቱን ካነበበዉ በኃላ የኃሊት ተምዘግዝጎ የሸህ አጃኢቡን ምክር ማስታወስ ጀመረ። "የምትወዳት ሳትሆን የምትወድህ ናት የምትንከባከብህ!" ሸህ አጃኢቡ ልብን ሰርስሮ የሚገባ እዉነተኛ የሆነን ምክር ነበር የመከሩት። "ኡስታዝ ልክ ናቸዉ!" ብሎ አሰበ። "ለኔ የምትሆነኝ ሀያት እንጂ ሀፍሲ አይደለችም!። ዴቭን ስታጣ ለመሸሸጊያ የምትጠቀምብኝ ሳትሆን ከልቧ የምታፈቅረኝ ሀያት ናት የምታስፈልገኝ!" ብሎ ለራሱ ወሰነ። ስልኩን አንስቶ ለሀፍሲ አጠር ያለ መልእክት ጻፈላት።
"አሰላሙዓለይኩም ሀፍሲ ሸህ አጃኢቡን ልኬብሽ ነበር። ነገር ግን ሳስበዉ እኔ ላንቺ አልሆንሽም!። ይቅርታ!!።"
ከወራቶች በኃላ ... ዴቭ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ፍቅረኛዉ ከነበረችዉ ሴት ከሀና ጋር ተጋብተዉ ልጃቸዉን አብረዉ ማሳደግ ጀምረዋል። ሀያትና ኡስማን ደግሞ ተገናኝተዉ ስለሰርጋቸዉ መነጋገር ጀምረዋል። ኡስማን ቶሎ የማግባት ፍላጎት ስላለዉ ሀያትም ሀሳቡ ፍላጎቷ ስለሆነ ተስማምታለች።
... ሀፍሲ ደግሞ የምታፈቅረዉ ዴቭን ስትከተል የሚያፈቅራትን ኡስማንን አጥታለች። ሸህ አጃኢቡ ለኡስማን ምክር በሚሰጡበት ወቅት "ቁንጅና የትዳር ዋነኛ መስፈርት አይደለም።" ብለዉት ነበር። የዚህ ምክር ትክክለኛ ባለቤት ሀፍሲ ናት። እድሜ ሲገፋ ሲጨምር የመጠፋ ቁንጅናዋን ተማምና ሁሉም ወንድ ይፈልጉኛል በሚል ስሜት ታዉራ ለትዳር የሚፈልጓትን ብዙ ወንዶች ገፍታለች። የሚያፈቅራትንና እንደ ንግስት ሊንከባከባትን የሚችልን ወንድ (ኡስማንን) ገፍታ በሌላ ሰዉ ፍቅር ታዉራ ኖራለች።
... ህይወት እንደዚህ ነች። ፈላጊ ተፈላጊን ሲያባርር ይኖራል። ፈላጊዉ ተፈላገጊዉ ላይ አይደርስበትም ወይም ፈላጊዉ በተፈላጊዉ ላይ ይደክመዉና ተስፋ ቆርጦበት ማበረሩን ያቆማል። ፈላጊዉ ኡስማን ተፈላጊዋ ሀፍሲን ማባረር ደክሞት ትቷታል። ፈላጊዋ ሀፈሲ በተፈላጊዉ ዴቭ ተስፋ ቆርጣለች!።
"የምንፈልገዉን ስንከተል የሚፈልገንን እናጣለን!"
●▩● ተፈጸመ ●▩●
===========================
|| አጫጭር መሳጭ ጣፋጭ ታሪኮች ያገኛሉ ።
Telegram|
https://t.me/Ahnemszafacebook| www.fb.com/EIMN.News
TUBE| www.youtube.com/channel/UCOSAeOty5pST4tsJrqdnjwA