⬜️#ነጫጭ_ጥቁረቶች⬛️
ክፍል አንድ
(by
@Eyos18)
.
.
ይገርማል ወደዚህች ምድር ከመጣሁ አስራዘጠኝ ዓመታቶች
ነጎዱ ማለት ነዉ? እዚህች ምድር ከመጣሁ በልጅነት እንደ ልጅ
ከልጆች ጋር የተጫወትኩበት ፣ የእሳቱ እድሜ ደርሶ ልቤ አብጦ
ቤት ማንንም አልታዘዝም ያልኩበት እና ህይወትን ለመረዳት
የሚያስፈልጉ ወሳኝ ነጥቦችን የተረዳሁበት እድሜ ነጎደ። አሁን
ወደ ሀያኛ አመት ሩጫዉን ተያይዤዋለሁ።
በነዚህ ዓመታት ዉስጥ በህይወቴ ዉስጥ ብዙ ሰዎች አልፈዋል።
ብዙ የማይረሱ ተወዳጅ እና አናዳጅ ሰዎችን አዉቄያለሁ። አስራ
አምስት ዓመታትን መጨረሻዬን በመናፈቅ በትምህርት
አሳልፌያለሁ።
.
አሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ። ስሜ ፈዉዛን ይባላል። ጠይም እና
ተጫዋች ነኝ። ቁምነገር ላይ ቁምነገረኛ ፣ ቀልድ ላይ ደግሞ
ምርጥ ቀልደኛ ነኝ። በራሴ በጣም እተማመናለሁ። ብዙ ሰዎች
ጢባራም ነህ ይሉኛል። ከሩቅ ሲያዩኝ የሚጠሉኝ ቀርበዉ
የሚያዉቁኝ ደግሞ የሚወዱኝ አይነት ሰዉ ነኝ። ስለራሴ
እንደዚህ በድፍረት የማወራዉ ብዙዎች ከቀረቡኝ በኋላ ምን
ያህል ከሩቅ ሲያዉቁኝ ይጠሉኝ እንደነበር እና ሲቀርቡኝ እና
ሲያዉቁኝ በጣም እንደወደዱኝ በተደጋጋሚ ስለሚነግሩኝ ነዉ።
ለራሳችን ያለን አመለካከት ከሚገነቡበት መንገዶች አንዱ ሰዎች
ስለኛ በሚነግሩን ነገር ላይ የተመሰረተ መሆኑ እዉን ነዉ። ለዛ
እኮ ነዉ ቤተሰብ እምነት የሚጥልባቸዉ ልጆች ፣ ሁሌም
ጀግንነታቸዉን የሚነግራቸዉ ታዳጊዎች ከከፍታ መሰላል ላይ
ቆመዉ የምናየዉ። በአንፃሩ ደግሞ አታዉቅም እየተባሉና
ትንሽነታቸዉ እየተነገራቸዉ ያደጉ ልጆች ትንሽ እንደሆኑ ይቀራሉ።
በእርግጥ እየተሞገሱ የሚቀሽሙ እንደሚኖሩት ሁላ ከዚህ
የትንሽነት ቀንበር አምልጠዉ ታላቅ የሚሆኑ ጥቂቶችም
አይጠፉም።
.
እኔ ፈዉዛን ካመንኩበት ነገር ላይ ወደኋላ ዝንፍ አላዉቅም።
እንደወራጅ ዉሀ በተቀደደላቸዉ እንደሚፈሱ ከንቱ ሰዎች አሊያም
ወደነፈሰበት እንደሚነፍሱ ገለባዎች አይነት አይደለሁም። ሰዉ
ነኝ!! እንቢ የማለት አቅም አለኝ። ከአስተሳሰቤ እና ከማንነቴ ጋር
የሚጣረስን ነገር እምቢ ከማለት ወደኋላ አልልም። ሁሌም ቃሙ
ሲሏቸዉ ገረባ ሳይቀር የሚያኝኩ ፣ ጠጡ ሲሏቸዉ ፋራ
ላለመባል አተላ የሚጋቱ ፣ አጭሱ ሲሏቸዉ ከማን አንሼ ብለዉ
ኦ በጭስ ለመስራት አይናቸዉ ተጎልጉሎ እስከሚወጣ
የሚያጨሱ ምስኪን፣ እንቢ የማለት ወኔያቸዉ የተሰለበ ፣
የመጣዉ ጎርፍ ሁሉ እያላጋ የሚወስዳቸዉ፣ የማንነታቸዉን
ልዕልና ያላከበሩ ሰዎች ያሳዝኑኛል። በእንደዚህ አይነት ሰዎች
መካከልም ተከብቤ እነሱ የመጣዉ ጎርፍ ሁላ ሲያላጋቸዉ እኔ
በፅናት ቆሜ አዉቃለሁ። ለዛ ነዉ በድፍረት እንቢ የማለት አቅም
አለኝ የምለዉ።
.
በተማርኩባቸዉ ትምህርት ቤቶች ዉስጥ ሁሉ ዝነኛ ነበርኩ።
የትምህርት ቤት ክበባት ውስጥ መሳተፍ አዘወትር ነበር።
ስነፅሁፍ እወዳለሁ። አንዳንዴ እሞነጫጭራለሁ ብዙ ጊዜ ግን
የሌሎችን የስነ ፅሁፍ ስራዎች መድረክ ላይ ማቅረብ ይዋጣልኝ
ነበር። እናም ከዚህ ስብዕናዬ ጋር ብዙ ጓደኞችን አፍርቻለሁ።
ብሩክ እና ሄኖክ የልጅነት ጓደኞቼ ናቸዉ። ከብሩክ እና ሄኖክ ጋር
የተዋወቅነዉ የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነን ነዉ። አንድ
ትምህርት ቤት ከመማራችን በዘለለ ሰፈራችንም አንድ ነበር።
ብሩክ በአቋራጭ የሚከብርበትን መንገድ ዘወትር የሚያስብ
አይነት ሰዉ ነዉ። የሰዉ ታሪክ ማዳመጥ ይወዳል በተለይ የፍቅር
ታሪክ። አንድ ሰዉ የፍቅር ግንኙነት ዉስጥ ገብቶ ካገኘዉ ልምድ
ሊያወራ ከሚችለዉ በላይ ብሩክ የፍቅር ግንኙነት ዉስጥ
ለመግባት ከመፈለጉ የተነሳ ብዙ ይቀባጥራል። እኔ ከብሩክ ጋር
የምካፈለዉ የህይወቴ ጎን የፍቅር ህይወቴን ነዉ። ማዳመጥ
ስለሚፈልግ እነግረዋለሁ።
ሄኖክ ደግሞ ቀላ ያለ አጭር ቁመት ያለዉ ሚስኪን ልጅ ነዉ።
መልካም ልብ አለዉ። ወደ መልካም ነገር የሚጠራዉ ሰዉ ካለ
ሁሌም መልካም ለማድረግ ዝግጁ ነዉ። ነገር ግን የኔ የሚለዉ
አቋም የለዉም። እኔ ጋር ሲመጣ ከኔ ጋር ያነባል ፣ ከብሩክ ጋር
ሲሆን ደግሞ ከሱ ጋር ለመመሳሰል ይሞክራል። ከጊዜያት በኋላ
ሄኖክ ሰፈር ቀይሮ ከኛ ሰፈር ትንሽ ራቅ ወዳለ ቦታ ስለሄደ
ግንኙነታችን እየቀዘቀዘ መጣ። በአንፃሩ ደግሞ ከብሩክ ጋር
በጣም እየተቀራረብን ሄድን። ቀናት ቀናትን እየወለዱ ወራት
ከወራት ጋር እየተጋቡ ይኸዉ አስራ ዘጠኝ አመት አልፎኝ ወደ
ሀያ ሩጫዉን ተያያዝኩት።
.
ዛሬ ዉስጤ ላይ የመሰበር ስሜት ይሰማኛል። ሁሌም ጠንካራ
ነበርኩ ፣ ዛሬ ግን በህይወቴ ዉስጥ በፍፁም ሊከሰት ይችላል
ብዬ የማልጠብቀዉ ነገር ተከስቷል። ዉስጤ የመሰበር ስሜት
ይሰማኛል። ለካ የኛ ያልናቸዉ ሰዎች የእምነት ባንዲራችንን
ቀድደዉ በተቃራኒ ወገን በኩል ሲሰለፉ ፣ ያመናቸዉን ልባችንን
ፊት ሲነሱ ፣ ያጎረሷቸዉን እጆቻችንን ሲነክሱ በጣም ያማል።
ህመሙ የልብ ምታችንን ከወትሮዉ በተለየ እንዲመታ
ሲያስገድደዉ ፣ አይናችንን ከእንቅልፍ ጋር ሲያጣላዉ ፣ ስሜቱን
መግለፅ ሲከብደን ፣ በደፈናዉ ስብራት እንለዋለን። አዎን ሁሉም
ቀጥ ብሎ የቆመዉ የህይወት መዘዉራችን ሲናጋ ፣ ምንም
ባይገልፀዉም እንኳ መሰበር እንለዋለን። አዎ ዛሬ እኔም
ተሰብሬያለሁ። የስብራቴ ሁሉ ምንጭ ደግሞ ከክብር ዙፋኔ
ወርጄ አብሬያት የተጫወትኩት ፣ ለማንም ያላረከስኩትን እኔነቴን
ያረከስኩላት የህይወቴ ትልቋ ደስታ፣ ስህተት እና ስብራት
ኢክራም ናት።
ኢክራም ቆንጆዋ!! ኢክራም ሀዘንተኛዋ!! ኢክራም አፍቃሪዋ!!
.
ይቀጥላል...
SHARE
@Ye_Hagere_WegochSHARE
@Ye_Hagere_Wegoch