Репост из: የተዋሕዶ ፍሬዎች
ሰሞኑን በተነሳው በቅዱሳት ገድላትና ድርሳናት ዙሪያ እንዲሁም በጥንተ አብሶ ዙሪያ
፩
@yetewahedofera
@yetewahedofera
፩
፦ እስካሁን በተመለከትኩት ገድላት አያስፈልጉም መወገድ አለባቸው የሚል ንግግርም ጽሑፍም ከኦርቶዶክሳውያን አልሰማሁም። ምክንያቱም ገድላትና ድርሳናት የወንጌል ትርጉሞች ናቸው። የቅዱሳን ሕይወት የሚታይ የሚዳሰስ የወንጌልን ቃል በተግባር የሚያሳይ ነውና።@yetewahedofera
፪፦ ነገር ግን በአንዳንድ ገድላትና ድርሳናት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ስሕተቶች ሊገኝባቸው ይችላል። ይህ እንዳይፈጠር የሊቃውንት ጉባኤያችን ጠንክሮ ማዕከላዊ የቅዱሳት መጻሕፍት ኅትመት ቢኖረውና በዚያ ቢታተሙ መልካም ነው። ብሔርን ከብሔር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን የሚያስተላልፉ ሐሳቦች በግል በሚታተሙት ገድላት ይስተዋላል።
፫፦ ለምሳሌ ቡና ይጠጣል ወይስ አይጠጣም የሚለው ክርክር ምንጩ ገድልና ድርሳን ነው። ለምሳሌ እኔ ከአምስት የገድላትና የድርሳናት መጻሕፍት ቡና እንደማይጠጣ የሚገልጽ አግኝቻለሁ። በተማርኩባቸው ጉባኤ ቤቶችና በየትኛውም የመጻሕፍት ትርጓሜ ጉባኤ ቤት ቡና አይጠጣም የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት የለውም። ታዲያ ጉባኤ ቤቶች ይህንን ሐሳብ ቀጥታ የመቀበል ግዴታ አለባቸውን?
፬፦ ባለፈው መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚእ አሰፋ (የጠቅላይ ቤተክህነት የትምህርትና ሥልጠና ክፍል ኃላፊ) ማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በነበረው ሥልጠና እንደማሳያ ብለው ብዙ የተአምረ ማርያም ቅጅዎችን እንዳዩ ገልጸውልን ነበር። እና በአንዱ የብራና ተአምረ ማርያም ቅጂ አጼ ቴዎድሮስን እጅግ በጣም አክፋፍቶ የሚገልጽ እንዳገኙ ገልጸውልን ነበር። አስተውሉ በአንዱ ቅጂ ነው የተገኘ እንጂ በሁሉ አይደለም። ትክክልነቱ ምን ያህል ነው? የሚለው ጥናት ይጠይቃል።
፭፦ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ ላይ ዮሐንስ አሥር ጊዜ ከተለያዩ እናቶችና አባቶች እንደተወለደ የሚገልጽ አግኝቻለሁ። ዮሐንስ መጀመሪያ የተወለደ ከአዳምና ከሔዋን ሲሆን ስሙም ያን ጊዜ "ሔና" ነበረ ይላል። ከዚያ በየዘመናቱ እየተወለደና መጨረሻ ላይ ከዘካርያስና ከኤልሳቤጥ ተወለደ ይላል። ይህ በአንድ ወቅት ደብረ ሊባኖስ ገዳም ግጭት ፈጥሮ ነበር። በወቅቱ በገዳሙ የነበሩት የንታ ብሩክ ይህ መስተካከል አለበት ሲሉ አንዳንድ ከመጻሕፍት ሩቅ የነበሩ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ስለሌለ እንዳለ እንቀበላለን አሉ። ነገሩ ግን ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር መመርመር አለበት። ይህ በአንዳንድ የገድለ ዮሐንስ መጥምቅ ቅጂዎች አይገኝም።
፮፦ ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ላይ እስከ ዕለተ ምጽአት የጎጃም ሕዝብ ይቅር እንደማይባል ይገልጻል። በሌሎች ገድሎችና ድርሳኖች ለምሳሌ በገድለ አቡነ ሰላማ፣ በድርሳነ ኡራኤል፣ በገድለ ተከሥተ ብርሃን፣ በገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ ደግሞ እስከ ዕለተ ምጽአት ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብለው እግዚአብሔርን የሚያመልኩና እግዚአብሔርም የሚወዳቸው በሃይማኖታቸውና በምግባራቸው የተመሰከረላቸው የጎጃም ሰዎች ናቸው ይላል። እና የትኛውን እንቀበለው? መመርመር አለበት። ራእየ ማርያም ላይ ሻን*ቅላ ለዘለዓለም እንደማይጸድቅ የሚናገር አለ። በእውነት ይህን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት የተናገረችው? ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር አይጋጭም?
፯፦ እንደዚህ እርስ በእርሱ የሚጋጩ ጉዳዮች ገድላት ላይና ድርሳናት ላይ ይስተዋላሉ። ይህ በተለያየ ምክንያት ነው። አንዳንድ መምህራን ሚሲዮናውያን ኢትዮጵያውያንን ለማለያየት ያስገቧቸው ናቸው ይላሉ። ይህ ሁሉ ቢሆንም ገድላትና ድርሳናት የሚታረሙት እየታረሙ በማዕከላዊነት በጠቅላይ ቤተክህነት ቢታተሙ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ይቻላል።
፰፦ በጥንተ አብሶ ዙሪያ ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ባሳተመው ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በጻፉት መጽሐፍ የሰው ልጅ ከጥንተ አብሶ የሚላቀቅ ሲጠመቅ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ጥንተ አብሶ በክርስቶስ መሰቀል ተወግዷል። ከዚህ በኋላ ሰው ቢኮነን እንኳ ራሱ በሠራው ኃጢአት እንጂ በጥንተ አብሶ አይደለም ይላሉ። (በጉባኤ ቤቶች ያለው አስተምህሮ ይህኛው ነው። በክርስቶስ መስቀል የውርስ ኃጢአት ጠፍቷል የሚል ነው። የእኔም አቋም ይህ ነው)። ጥንተ አብሶ የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን የበደል መጀመሪያ ማለት ነው። ይኸውም አዳምና ሔዋን የሠሩት በደል ነው። ይህ በደል ለአዳምና ለሔዋን ብቻ ይነገራል። የእነርሱ የበደል ውጤት (መርገም) ከእነርሱ ወደሚወለዱት ልጆች ተላልፏል። ይህን ውጤቱን የውርስ ኃጢአት እንለዋለን። ቅድስት ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት የለባትም። ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል እንዲል ከማኅፀን ጀምሮ ራሱ እግዚአብሔር ጠብቋታልና።
፱፦ በሚዲያ ዞር ዞር ስል ሕዝቤ ለሁለት ተቧድኖ ይቧቀሳል። በሁለቱም ወገን ያለው በእመቤታችን ንጽሕናና ቅድስና ይስማማል። ጠቡ በቃላት ያለመግባባት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሁሉም ጽንፍ ይዞ የአንዱ ደጋፊና የአንዱ ነቃፊ ሆኖ በየራሱ ትርጉም ክፉ ስም ይሰጣጣል እንጂ ቆም ብሎ አንዱ አንዱን ለማዳመጥ ጊዜ ቢሰጣጡ ተመሳሳይ አረዳድ ላይ ይደርሱ ነበር። አንዳንዱ ደግሞ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር የለም። ነገር ግን በደጋፊነትና በነቃፊነት ጎራ ይተራመሳል። የዚህ መፍትሔው ከፍ ያሉ ጉዳዮች ላይ ዝም ብሎ ማዳመጥ የተሻለ ነው።
፲፦ ወቅት እየጠበቁ የሚያከራክሩ ጉዳዮች አሁንም ብዙ አሉ። ለምሳሌ የልደት ጾም በዘመነ ዮሐንስ ህዳር 15 ይጀመራል ወይስ 14? ጥምቀት ሰኞ ሲውል ቅዳሜና እሑድ ይጾማል ወይስ እሑድ ብቻ የመሳሰሉ ጉዳዮች ይነሳሉ። (እነዚህን የጠቀስኳቸው ታዋቂ ስለሆኑ እንጂ ሌላም ቀኖናዊ ያልሆኑ ከፍ ያሉ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ለጊዜው ከዚህ አልጠቅሳቸውም)። አሁን ዘመኑ የሚዲያ ስለሆነ ሁሉም የየራሱን አብነት እየያዘ ከሚወጋገዝ በማዕከላዊነት ሊቃውንት ተሰብስበው ወጥ የሆነ እይታ እንዲኖር ማድረግ ግድ ይላል። የሊቃውንት ጉባኤ ከዘመኑ መቅደም አለበት። EOTC Tv ከአሉባልታና ከጳጳሳት ውዳሴ ወጥቶ ዘመኑን የሚመጥንና ጥያቄዎችን ቀድሞ የመመለስ ሥራ ሊሠራ ይገባል።
ኦርቶዶክሳዊው መንገድ ጉዳይ ተኮር ነው። ክርስቶስ ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አልጠላም ብሏል። ይህ ጉዳይን በጉዳይነቱ መሞገት እንደሚገባ ያስረዳናል። ሁሉም ሰው የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ከውስጥም ከውጭም ጠላቶች መጠበቅ አለበት። ሲጠብቅ ግን እውነትን መሠረት አድርጎ እንጂ በተሳሳተ ፍረጃ፣ ስምን በማጥፋት፣ በስድብ ሊሆን አይገባም።
© በትረ ማርያም አበባው
@yetewahedofera
@yetewahedofera