በመዲናዋ በስድስት ክፍለ ከተሞች የስምና ንብረት ዝውውር ታገደ በአዲስ አበባ ከተማ ለመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሥራ ሲባል ለቀጣይ 5 ወራት በስድስት ክ/ከተሞች በተመረጡ ወረዳዎች የስምና ንብረት ዝውውር ታገደ።
የከተማዋ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጄንሲ ለፋና ዲጂታል እንዳስታወቀው፥ ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ለዚህም ዘመናዊ ሁለገብ ካዳስተር ግንባታ ስርዓት በመዲናዋ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን አመልክቷል፡፡
አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት ውስጥ 54 በመቶ ለሚሆነው የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሥራ መሰራቱ ተጠቁሟል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ በ136 ቀጠናዎች የሚገኙ ይዞታዎችን አረጋግጦ ለመመዝገብ እየተሰራ ነው ተብሏል።
በዚህ መሠረትም የይዞታ ማረጋገጥ ስራው በተመረጡ ስድስት ክ/ከተሞች በቀጣይ አምስት ወራት ውስጥ እንደሚከናወን ተጠቅሷል።
ክፍለ ከተሞችም የካ፣ ለሚ ኩራ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፣ቦሌ እና ኮልፌ ቀራኒዮ መሆናቸው ተመላክቷል።
ለመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሥራው ሲባልም ምዝባ በሚካሄድባቸው የክ/ከተሞቹ ወረዳዎች እስከ ቀጣየዩ ሚያዝያ ወር መጨረሻ አካባቢ የስምና ንብረት ዝውውር መታገዱ ተገልጿል።
ባለይዞታዎች ከታሕሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 10 ቀናት የይዞታ ይረጋገጥልኝ ማመልከቻ እንዲያቀርቡም ጥሪ ቀርቧል።
Facebook.com/EthioTube Twitter.com/EthioTube Youtube.com/EthioTube Instagram.com/EthioTube https://t.me/ethiotubehttps://whatsapp.com/channel/0029VaCq8Gs2kNFzFeZTGh3L