ኅዳር ፫ /3/
በዚች ቀን ከቆሮንቶስ አገር ቅዱስ አባት ኪርያቆስ አረፈ። የዚህም አባት ወላጆቹ ሃይማኖታቸው የቀና የከበሩ ናቸው የቤተክርስቲያንን ትምህርትና የቀናች ሃይማኖትን አስተማሩት ከዚህም በኋላ የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነ ወደ አባ ጴጥሮስ አቀረቡት እርሱም በላዩ ጸልዮ አናጒንስጢስነት ሾመው።
ከዚህም በኋላ ዘወትር መጻሕፍትን የሚያነብ የቃላቸውንም ትርጓሜ የሚመረምር የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓቷንና ሕጓን የሚያጸና ሆነ በትምህርቱና በእውቀቱም ከብዙዎች ከፍ ከፍ አለ መጻሕፍትንም በሚያነብለት ጊዜ ኤጲስቆጶሱ በእርሱ ደስ ይለው ነበርና። ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት በሆነ ጊዜ ሚስትን ያጩለት ዘንድ ወላጆቹ ጠየቁት እርሱ ግን ይህን አልወደደም ግን ከገዳማት ወዳንዱ ይሔድ ዘንድ እንዲአሰናብቱት ወላጆቹን ለመናቸው የከበረች የምንኲስናን ልብስ ሊለብስ ወዶ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ከኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ ከአባ ቄርሎስ ጋር ተገናኝቶ ስለ ምንኲስና ኀሳቡን ሁሉ ነገረው።
እርሱም በጎ ሥራን ወደሃል አለው ታላቅ አባትም እንደሚሆንና በእርሱም የብዙዎች ነፍሳት ብሩሃን እንደሚሆኑ ትንቢት ተናገረለት ። ከዚህም በኋላ የመነኰሳት አባት ወደ ሆነ በፍልስጥዔም ወደ ሚኖር ወደ ክቡር አባ ሮማኖስ ላከው እርሱም በደስታ ተቀብሎ የምንኵስናን ልብስ አለበሰው። ከዚህም በኋላ በጾም በጸሎት በስግደት በመትጋት በታላቅ ድካም በቀንና በሌሊት በገድል ተጸምዶ በትዕግሥት በትሕትና በቅንነት ኖረ።
እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጥቶት ወደርሱ የሚመጡትን በሽተኞች ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ:: ከዚህም በኋላ በመልካም ሽምግልና እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ :- መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️