ለጥምቀት ያልሆነ ወግ...
(በእውቀቱ ስዩም)
ዓመት በአል በመጣ ቁጥር እልል ያልሁ አማኝ ነኝ፤ ጥምቀትንማ ከልደቴ በላይ ነው የማከብረው፤ ጎረምሳ ሳለሁ እኔና ይሁኔ በላይ አብረን ጥምቀት እንሄድና የጊዮርጊስን ታቦት እናጅባለን፤ ከዚያ የሎሚ ውርወራ ክፍለጊዜ ይቀጥላል ፤
ሎሚ ውርወራን የፈለሰፈው ኢትዮጵያዊ ደብተራ ግን ምንኛ ደንቅ ሰው ነው! ለምሳሌ የስፔን ሕዝብ በአል የሚያከብረው ቲማቲም በመወራወር ነው፤ አንድ ክፍለከተማ የሚመግብ ቲማቲም ሲወራወር ይውልና ፥ ሲመሽ ቀይ ወጥ ውስጥ የዋኘ ይመስል፥ ተጨመላልቆ ወደ ቤቱ ይገባል፤ እኔ ራሴ ባለፈው ዓመት ተሳትፍያለሁ፤ ቱሪስት ነው ብለው ሳይራሩልኝ፥ ያልታጠበ የድግስ ድስት አስመሰለው ለቀቁኝ ! በአልንስ አበሻ ያክብራት!
በጉብዝናየ ወራት፥ የጥምቀት ቀን ፥ ከይሁኔ በላይ ጋራ ሰንተራ ሜዳ ላይ እንሰማራለን፤ እኔ ከትርንጎ ጋራ የተዳቀለ ጠንካራ ሎሚ ታጥቄ ቆነጃጅቱን አማትራለሁ፤ ይሁኔ በላይ እንደኔ የሀብታም ልጅ ስላልበረ፥ ሎሚ afford ስለማያረግ እምቧይ ይወረውራል፤
ከዝያ “ ወርወሬ መታሁት ፥ ጥላሽን በእንቧይ”ብሎ ያንጎራጉራል፤
“ጥላዋን ከመታኸው እንደ ጥላ ስትከተልህ ትኖራለች “ የሚል ፈሊጥ ነበረው’
ሎሚ የምወረውርላቸው ሴቶች ባብዛኛው ይሽኮረመማሉ፤ ትዳር እንኳ ባይሆን ፈገግታ ይለግሱኛል፤ አንደኛዋ ግን ሎሚ ስወረውርላት “ አላማ አለኝ “ አለችና በእግሯ መልሳ ብትለጋው ግንባሬ ላይ ግልገል አናናስ የሚያህል እጢ በቀለ፤
ቅድም፥ ይህንን እያስታወስኩ፥ ሀያሁለት ማዞርያ ላይ፥ ቆሜ አላፊ አግዳሚውን እመለከታለሁ፤የለበስኩት ቲሸርት ከፊትለፊቱ የፋሲል ግንብ ተስሎበታል፤ ከሁዋላ ደግሞ የመጥምቁ ዮሀንስን ምሰል ይዟል፤
ዘናጭ ሴቶች በፊቴ እያለፉ ነው፤
ከሴቶች ጋራ ማውራት ያምረኛል ፤ ግን እንዴት እንደምጀምር ግራ ይገባኛል፤
አንዲቱ አጠገቤ ስትደርስ፥
“ ይቅርታ” ብየ ጀመርሁ፥
“ ምንም አይደል “ ብላኝ መንገድዋን ቀጠለች፤
ቀጣይዋ ከፊቴ ብቅ ስትል፥
“ እናት !” ስላት፥
“ አገር “ አለችኝ፥
ምን አይነቱን ከይሲ ትውልድ ነው ፈትቶ የለቀቀብን ብየ፥ ተስፋ ቆርጨ በማየት ብቻ ተወሰንኩ ፤ ሶስተኛይቱ ባጠገቤ ስታልፍ ዞር ብላ ፈገግ ያለችልኝ መሰለኝ ፤
“ እንኩዋን አደረሰሽ “ አልኳት፤
“ የጆቭሀ ምስክር ነኝ “
እንኳን አደረሳችሁ ❤️❤️❤️