በኢትዮጵያ 10 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ሲጋራ የሚያጨሱ ሲሆን የሴት አጫስ ተማሪዎች ቁጥር ጨምሯልከአየር ንብረት ለዉጥና ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ በርካታ ዜጎች እንደ ሳንባ በሽታ ላሉ የመተንፈሻ አካል በሽታዎች ተጋላጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻልና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሄድ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ በመተንፋሻ አካላት ጤና ዙሪያ የሚያደርገዉ የምርምር ስራ ተጠቃሽ ነዉ።የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ራሄል አርጋዉ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ማህበሩ ባለፋት አስርት አመታት በጤናው ዘርፍ በተለይም ሳንባ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የምርምር ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
ማህበሩ የ10 ኛ አመት የምስረታ ቀኑን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ በሳንባ እና በፅኑ ህሙማን ህክምና ያሉትን የምርምር ዉጤቶችን ለማስተዋወቅ ያለመ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።በመድረኩ የቀረቡት አብዛኛዎቹ የምርምር ዉጤቶች በሳንባ በሽታ ላይ ትኩረት ማድረጋቸዉን ፕሬዝዳንቷ ገልፀዉ በሽታዉ በኢትዮጵያ ከህመም አልፎ ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ ተናግረዋል።ኢትዮጵያ በሽታዉን ለመከላከል የተለያዮ ጥረቶችን ብታደርግም በሳንባ በሽታ ዙሪያ የተለያዮ ጥያቄዎች ይነሳሉ ሲሉ የተናገሩት ዶክተር ራሄል የቲቢ በሽታ የዘረ መል ዉጤትን እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለዉን ግኝት አስመልክቶ በመድረኩ የዳሰሳ ጥናቶች ቀርበዋል።
ከአየር ንብረት ለዉጥና ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ ብዙዎችን ለበሽታዉ ተጋላጭ እያደረጋቸዉ ስለሚገኝ በሽታዉን መከላከልና ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 10 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ሲጋራ ማጨስ እንደሚጀመሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲሉ የገለፁት ፕሬዝዳንቷ ይህም በቀሪ ዘመናቸዉ ሱሰኛ ሆነዉ እንዲቀጥሉ እና የጤና እክል እንዲገጥማቸዉ የማድረግ እድሉ ከፍተኛ ነዉ በማለት ስጋታቸዉን ገልፀዋል። 8 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች መሆናቸዉ ተጠቁሟል።
በተለይም የሳንባ ካንሰር ዋነኛ አጋላጭ መንስኤዉ ሲጋራ ማጨስ እንደሆነ ጠቁመዉ የሚመለከተዉ አካል ለጉዳዮ ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ጤናማ ዜጋን ማፍራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማህበሩ ያደረጋቸዉን የምርምር ዉጤቶች ለሚመለከተዉ አካል ለማቅረብና በጋራ በመስራት ችግሩን ለመፍታት ታስቧል በማለት የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ራሄል ጨምረው ለጣቢያችን ገልፀዋል።
በቅድስት ደጀኔ
https://t.me/EthioGlobal_News