እግዜር ሸማኔ ነው።
ይሸምናል ሕይወት
ይቋጫል ነጠላ
ዳሩ አይመሰገን እጁ በሽመና
አዳውሮ መተርተር ልማዱ ነውና።
ይህ የእንጉርጉሮ ውዳሴ በሲጋራ ሽታ እና በሁካታ ድብልቅ በተሞላው ጠጅ ቤት ውስጥ በአንድ አዝማሪ ልሳን ለመለኮት የቀረበ ዝማሬ ነው፡፡ አዝማሪው ከሁካታው በላይ ድምፁን ጎላ አድርጎ እያንጎራጎረ፣ መሰንቆውን እየተጫወተ ዓይኑን ባዶው ቦታ ላይ ያንከራትታል፡፡
ግንባሩን ቁጥር እና አገጩን ከፍ አድርጎ ዙሪያውን ይገረምማል፡፡ በጠጅ ቤቱ ውስጥ የተሰባሰቡት በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎች አፍላአፍ ገጥመው ወጋቸውን መጠረቅ ይዘዋል፡፡ ልጅ እግሩ አዝማሪ ከሁሉም በላይ ድምጹን ከፍ አድርጎ ማንጎራሩን ቀጠለ፡፡ ድምፁ በሁሉም አቅጣጫ የሚያስተጋባ ኃይለኛ ቢሆንም የቅዳሜ ከሰዓቱን የጠጅ ቤት ግለት እና ሁካታ ማሸነፍ የሚችል አልነበረም፡፡
ይህ ልጅ እግር አዝማሪ ስሙ ጥጋቡ ይሰኛል፡፡ በጥንቱ ዘመን ነገሥታቱን ከሚያጫውቱ በትውልድ አዝማሪዎች ከሆኑ ቤተሰቦች ይወለዳል፡፡ አዝማሪዎች ለዘመናት ነገሥታቱን እና መሳፍንቱን የሚያገለግሉ፣ ፖለቲካውን የሚሸረድዱ፣ ለድሃው የልቡን በሰምና ወርቅ በዜማ አዋዝተው የሚናገሩ፣ የሰላ ማኅበረሰባዊ ነቀፌታ የሚሰነዝሩ አስቂኝና ቧልተኞች ብቻ ሳይሆኑ የማኅበረሰብ ሐያሲዎች ነበሩ፡፡
ለዘመናት ለዙፋኑ ቅርብ ሆነው አንዳንድ ጊዜም ከዙፋኑ ተጋፊዎች ጎራ ተሰልፈው የአጫዋችነቱን ሚና ወስደው ባህልን በማሳለጥ፣ በማጎልበት ሂደት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
ጥጋቡ ከጠጅ ቤት ወደ ጠጅ ቤት ይንከራተታል፡፡ የሰከሩ ደንበኞች ቢጎነትሉም ወይም ለዜማ ጥሪው ትኩረት ቢነፍጉትም በጽናት አዝማሪነቱን ቀጥሎበታል፡፡ መጀመሪያ የጨዋታ ማሟሻ ይሆነው ዘንድ ወዲያውም የአዝማሪነት ችሎታውን ለመግለጥ የእግዚአብሔርን ኃያልነት፣ የሕይወትን ኃላፊ ጠፊነት የሚያመሰጥር ግጥሙን በዘለሰኛ እንጉርጉሮ ለታዳሚዎቹ አቀረበ፡፡
ቀስ በቀስ ስልቱን እየለወጠ ወደ የፍቅር ዝማሬ፣ ጎንደር ከተማንና ጎንደር ያፈራቻቸውን ታላላቅ ሰዎች የሚያወዳድሱ እዚያው በዚያው የተሰናኙ ግጥምና ዜማዎች ወደ ማቅረብ ተሸጋገረ፡፡ ደንበኞች የቱንም ያህል በሚያቀርባቸው ዜማዎች ቢፈነድቁ አዝማሪው ግን ስሜቱን ገዝቶ መጫወቱን ይቀጥላል፡፡
-
-
-
-
(የፒያሳ ቆሌዎች፣ የአዝማሪው እግዚኦታ፣ ገጽ 27-28)
ተጻፈ፣ በኢተሱሺ ካዋሴ (ዶ/ር)
ትርጉም፣ በያዕቆብ ብርሃኑና ዓለማየሁ ታዬ