የኒስፍ ሸዕባን ሌሊት
(ተሻሽሎ የቀረበ)
=============
የዛሬዋ ለሊት የሸዕባን ወር ዐስራ አምስተኛው ለሊት ናት። የተባረከች ሌሊት ናት። ታላላቅ ትሩፋቶች እንዳላት የሚጠቁሙ በርካታ ሐዲሶች ተነግሮላታል። ሐዲሶቹ እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉ እና ሐሰን የተሰኘው የሐዲስ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ዐሊሞች ተናግረዋል። ዶዒፍ የሐዲስ ዘገባዎችም ቢሆኑ በእንዲህ ባሉ የመልካም ስራን ትሩፋት በሚያብራሩ ጉዳዮች ላይ በቂ መረጃዎች መሆናቸው በዐሊሞች ዘንድ ስምምነት ያለበት ነጥብ ነው።
አብዛኞቹ የአራቱ መዝሀብ የፊቅህ ሰዎች የሻዕባን አጋማሽ ሌሊትን በዒባዳ ህያው ማድረግ እንደሚወደድ ያምናሉ።
ይኸውም በበርካታ የሐዲስ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ ነው። ለአብነት ያህል ተከታዮቹን እናንሳ: ‐
⚀ ሙዐዝ ኢብኑ ጀበል [ረዐ] እንደዘገቡት ነቢዩ [ﷺ] እንዲህ ብለዋል: ‐ «አላህ ሰዎችን በሙሉ [በእዝነት] ይመለከታል። ከአጋሪ ሙሽሪክ እና ከቂመኛ በስተቀር ሰዎችን በሙሉ ይምራል።» ጦበራኒ ዘግበውታል።
ይህንኑ ሐዲስ በዝ‐ዛር እና አሕመድ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐምር በተገኘ ዘገባም አስፍረውታል። ነገርግን ግማሹ የሐዲስ ቃል «ከነፍሰ ገዳይ እና ከቂመኛ በስተቀር ሰዎችን በሙሉ ይምራል።» በሚል ተለውጧል። ኢማም ኢብኑ ሐጀር አል‐ሀይተሚይ "ዘጋቢዎቹ ታማኞች ናቸው።" ብለዋል።
⚁ ከምእመናን እናት ሰይዳ ዐኢሻ [ረዐ] እንዲህ ተዘግቧል: ‐ «በአንድ ሌሊት ላይ ነቢዩን [ﷺ] አጣኋቸው። ከዚያም እርሳቸውን ለመፈለግ ከቤት ወጣሁ። በቂዕ ላይ ጭንቅላታቸውን ወደ ሰማይ ከፍ አድርገውም አገኘኋቸው። እንዲህም አሉኝ: ‐
«ዓኢሻ ሆይ አላህ እና መልክተኛው ይበድሉኛል ብለሽ ፈርተሽ ነው?»
እኔም «የአላህ መልክተኛ ሆይ ይህን ፈርቼ አይደለም። አንደኛዋ ባለቤትዎ ጋር ሄደው ከሆነ ብዬ ገምቼ ነው!» አልኳቸው።
እርሳቸውም እንዲህ አሉኝ: ‐ «አላህ በሸዕባን ወር ዐስራ አምስተኛ ሌሊት ላይ ወደ ቅርቡ ሰማይ (በእዝነቱ) ይወርዳል። ከልብ (ከሚሰኙ ጎሳዎች) የፍየል ፀጉር ቁጥር በላይ ለሆኑ ሰዎች ምህረትንም ይሰጣል።» ቲርሚዚ፣ ኢብኑ ማጀህ እና አሕመድ ዘግበውታል።
⚂ ዐሊይ ኢብኑ አቢጧሊብ [ረዐ] እንደዘገቡት ነቢዩ [ﷺ] እንዲህ ብለዋል: ‐ «የሸዕባን ወር ዐስራ አምስተኛው ሌሊት ሲሆን ሌሊቱን ቁሙበት ቀኑን ፁሙት። ፀሀይ ከጠለቀ ጀምሮ አላህ [በእዝነቱ] ወደ ምድር ይወርዳል። 'ምህረት የሚለምነኝ የምምረው ማነው? ሲሳይ የሚለምነኝ ሲሳይን የምሰጠው ማነው? መከራ የደረሰበት ከመከራ የማወጣው ማን ነው? እንደዚህ እንዳደርግለት የሚለምነኝ የሚፈልገውን የማደርግለት ማነው?…' ንጋት እስከሚቀድ ድረስ እንደዚህ በማለት ይጣራል።» ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል።
እነዚህ ሐዲሶች ሌሊቷ ልዩ ትሩፋት እንዳላት የሚያስረዱ ግልፅ መነሻዎች ናቸው። የአላህ እዝነት እና ምህረት በይበልጥ የሚንሰራፋባት ሌሊት መሆኗንም ያመለክታሉ።
ይህንን ትሩፋት ለማግኘት በዚክር፣ በሶላት፣ በዱዓ እና በቁርኣን ራሱን ያቀረበ ሰው የተባረከውን የአላህ ችሮታ የማግኘት እድሉ እንደሚሰፋ ግልፅ ነው። በዚች ሌሊት ሶላት ማብዛትም ተወዳጅ ነው። ዱዓ ተቀባይነት ከሚያገኝባቸው ልዩ ጊዜያት መካከል የምትመደብ ሌሊትም ናት።
⚀ ኢማም ሻፊዒይ [ረዲየላሁዐንሁ] "አል‐ኡም" በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ: ‐
«በእነዚህ ሌሊቶች (ለይለቱ ኒስፍ‐ሻዕባንን ጨምሮ) ዙርያ የተዘገቡ ነገሮችን በሙሉ ተወዳጅ ናቸው ብዬ አምናለሁ።»
[ሻፊዒይ የተዘገቡ ነገሮች ያሏቸው ሶላት፣ ዱዓ እና ዚክርን ነው።]
ታላቁ የሻፊዒዮች ልሂቅ ኢማም ኢብኑ ሐጀር አል‐ሀይተሚይ እንዲህ ይላሉ: ‐
«ይች ሌሊት ታላቅ ትሩፋት አላት። ልዩ ምህረት እና ልዩ የዱዓ ኢስቲጃባ የሚገኝባት ሌሊት ናት።» አልፈታዋ አል‐ፊቅሂየቱል‐ኩብራ የተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ ማየት ይቻላል።
⚁ ታላቁ የሐነፊዮች ሊቅ ኢብኑ ኑጀይም በበኩላቸው እንዲህ ብለዋል: ‐
«የረመዷን የመጨረሻ ሌሊቶችን፣ የሁለቱን ዒድ ሌሊቶች፣ የዙል‐ሒጃን ቀዳሚ ዐስር ሌሊቶች፣ የሸዕባን አጋማሽ ሌሊትን በዒባዳ ማንጋት የተወደደ ነው። ሐዲሶችም ተዘግበዋል።» አል‐በሕሩ አር‐ራኢቅ በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ የተናገሩት ነው።
⚂ "ታጁል‐ኢክሊል" በተሰኘው መፅሀፍ ላይም «ይችን ሌሊት በሶላት ማሳለፍ ይወደዳል።» ተብሏል። መፅሀፉ የማሊኪዮች ታዋቂ መፅሀፍ ነው።
⚃ የሐንበሊዮች መዝሀብም ይኸው ነው። የሐንበልዮቹ ልሂቅ ኢማም አል‐ቡሁቲይ «ሸርሑ ሙንተሃል‐ኢራዳት» በተሰኘው መፅሃፋቸው ላይ በግልፅ ተናግረዋል። ኢብኑ ተይሚያም መጅሙዑል‐ፈታዋ በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል: ‐
«የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት ትሩፋቶችን አስመልክቶ በርካታ ሐዲሶች እና የሰለፎች ልማድ ተዘግበዋል። አንዳንድ ሰለፎች ሌሊቱን ሲሰግዱ ያድሩ እንደነበርም ተነግሯል። ስለዚህ አንድ ሰው ለብቻው በሌሊት ሲሰግድ ቢያድር ከቀደምቶቹ መሀል የአንዱን ሰለፍ ስራ ሰርቷል። ማስረጃም ተከትሏል። እንዲህ አይነት ነገርን መቃወም አይገባም።»
በመጨረሻም ሁለት ነገሮችን እዚህ ላይ እናስታውስ: ‐
⚀ ይህንን ሌሊት በሶላት አሳልፉ የተባለው ለየብቻ ነው፤ በጀመዓ አይደለም። በመስጂድም ሆነ ከመስጂድ ውጪ መሰባሰብ አያስፈልግም። ለየብቻችን ጌታችን ፊት እንቁም።
በአራቱም መዝሀብ በርካታ የፊቅህ ሰዎች በጀመዓ ተሰብስቦ ማደር ጠልተዋል።
⚁ በዚች ሌሊት የሚሰገድ የተለየ ሶላትም ሆነ የአሰጋገድ መንገድ የለም። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ "አስ‐ሶላቱል‐አልፊያ" የሚባል በዚህ እለት ብቻ የሚሰገድ ሶላት አለ። መቶ ረከዐ ይሰግዳሉ፤ በየረከዐው ከፋቲሓ በኋላ ዐስር ጊዜ ሱረቱል‐ኢኽላስን ይቀራሉ። ይች ሶላት ድንጉግ አይደለችም። ዐሊሞች ተቃውመዋታል። ስለዚህ መነሻ የሌላት ውድቅ ተግባር ናት።
ስለዚህ በዚህ ሌሊት ከአንድ ሙስሊም የሚጠበቀው ለብቻው ሆኖ ጊዜውን በሶላት ማሳለፍ ብቻ ነው። ከዚያ በዘለል ዱዓ ማብዛት፣ ለአላህ መዋደቅ ተገቢ ነው።
ኢማም ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: ‐
«ሶላቱር‐ረጋኢብ» የሚሏት ሶላት አለች። (የረጀብ የመጀመሪያው ጁሙዐ ላይ በመግሪብ እና በዒሻእ መካከል የሚሰግዷት ሶላት ናት።) የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት ላይ የሚሰግዷት ሶላትም አለች። እነዚህ ሁለቱም ሶላቶች የተወገዙ እና የተጠሉ ቢድዓዎች ናቸው።»
በዚህ ሌሊት: ‐
⚀ ይቅር እንባባል። ቂምና ጥላቻን እናስወግድ።
⚁ ሌሊቱን በሶላት፣ ቁርኣን በማንበብ፣ በዚክር እናሳልፈው።
⚂ ቀኑን በጾም እናሳልፈው።
⚃ ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን እና ለሀገራችን ዱዓ እናብዛ። ሌሊቱ ዱዓ ተቀባይነት ከሚያገኝባቸው ልዩ ቀናት መካከል አንዱ ነው!
አላህ ተውፊቅ ይስጠን!
https://t.me/fiqshafiyamh