መሐርኒ ድንግል


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: не указана


ስለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በመለከተ ስለ ገድለ ቅዱሳን፣ መንፈሳዊ ጥያቄ ፣ ምክረ አበው እና የተለያዩ መንፈሳዊ ነገሮች ወደ እናንተ እናደርሳለን!

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
не указана
Статистика
Фильтр публикаций


👸እስቲ ለዚች ምስኪን እናት ምን ያህል like 💯👍 ይገባታል?😢...


4-3-3 ስፖርት ባይሆን በትንሹም አዳዲስ መረጃ እና ደስ የሚሉ Video ያገኙበታል ትወዱታላችሁ 👉 @all_football_0




እንኳን ለታላቁ ሊቅና ጻድቅ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

    ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ

  ቅዱስ አንስጣስዮስ በ4ኛው ክ/ዘመን የተነሳ ሶርያዊ የነገረ መለኮት ሊቅ: ገዳማዊ ጻድቅና የመንበረ አንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ነበር:: ቅዱሱ ርጉም አርዮስን ካወገዙ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው:: በወቅቱ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ሱባኤውንና ጉባኤውን የመሩ ሲሆን አንዱ ይህ ቅዱስ ነው::

ከ 5 ዓመታት በሁዋላም ብዙ ድርሳናትን ጽፎ: ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ330 ዓ/ም አርፏል:: ያረፈው ግን አርዮሳውያን ባቀረቡት ክስ በሃሰት ተመስክሮበት በግፍ ተሰዶ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ውለታው የውዳሴ ድርሳን ጽፎለታል::

      አቡነ ዓምደ ሥላሴ

   እኒህ ታላቅ ጻድቅ ሐዋርያዊ አባት አቡነ ዓምደ ሥላሴ የትውልድ ሃገራቸው ጎጃም ሲሆን የተወለዱት በዚሁ ዕለት (የካቲት 27) ነው:: ጻድቁ በአጼ ሱስንዮስ (በ17ኛው መቶ ክ/ዘ) የነበሩ ድንቅ ሠሪ : ተአምረኛና ገዳማዊ አባት ናቸው::

የካቲት 16 ቀን መንኩሰው ወደ ተጋድሎ ገብተዋል:: በዋልድባ በነበራቸው ቆይታም እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እንድትከበር ማድረጋቸውም ይነገራል:: ጻድቁ በሌሎች ገዳማትም የነበሩ ሲሆን ዛሬም ድረስ ረድኤታቸው የሚደረግበት : ስማቸው የሚጠራበት ገዳም ግን ማኅበረ ሥላሴ ይባላል::

ገዳሙ የሚገኘው በሃገራችን ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ : በመተማ በርሃ ውስጥ ነው:: ይህንን ቅዱስ ገዳም የመሠረቱትም ራሳቸው አባ ዓምደ ሥላሴ ናቸው:: ገዳሙ ዛሬም ብዙ ምሑራንና መናንያን ያሉበት : በደህና ሁኔታም የሚገኝ ነው:: ግን በርሃውን የኔ ብጤ ደካማ ሰው የሚችለው አይደለም::

ስለ ጻድቁ ዓምደ ሥላሴ ከሚነገሩ ታሪኮች ቅድሚያውን የሚይዘው የተዋሕዶ ጠበቃነታቸው ነው:: በ1603 ዓ/ም ዼጥሮስ (ፔድሮ) ፓኤዝ የሚባል ካቶሊካዊ እሾህ ወደ ሃገራችን ገብቶ ነበርና ንጉሡን ሱስንዮስን አባብሎ ተዋሕዶን አስካዳቸው:: ነገሩ ውስጥ ለውስጥ ሲበስል ቆይቶ በ1609 ዓ/ም በመገለጡ እነ ራስ ዮልዮስ ለሃይማኖታቸው ጠዳ ላይ ተዋግተው ግንቦት 6 ቀን ተሰው::

ይህ ነገር ሲሰማ ወንድ ሴት : ትልቅ ትንሽ ሳይመረጥ በገጠሩም : በከተማውም : በገዳሙም ያሉት ሁሉ የተዋሕዶ ልጆች መንቀሳቀስ ጀመሩ:: 7 ዓመታት እንዲህ አልፈው በ1616 ዓ/ም ግጭቱ በይፋ ተጀመረ::

"ተዋሕዶን ካልካዳችሁ" በሚል በቀን እስከ 8,000 ሰው በሰይፍ ታረደ:: ይህን ያደረጉት ደግሞ አልፎንሱ ሜንዴዝ : ንጉሡ ሱስንዮስና ጀሌዎቻቸው ነበሩ::

በጊዜውም ከቤተ መንግሥት እነ ንግሥት ወልድ ሰዓላ (የሱስንዮስ ሚስት) : ከጻድቃን አበው ዘርዓ ቡሩክ ዘግሺ : ሐራ ድንግል ዘደራ : ምዕመነ ድንግል ዘጩጊ : ዓምደ ሥላሴ ዘማኅበረ ሥላሴ . . . ከቅዱሳት እነ ፍቅርተ ክርስቶስ : ወለተ ዼጥሮስ : ወለተ ዻውሎስ : እኅተ ዼጥሮስ . . . ለሃይማኖታቸው ተዋሕዶ ጥብቅና ቆመው ሕዝቡን አስተማሩ:: መከራም ተቀበሉ::

ብዙ ኢትዮዽያውያን የመከራ ጽዋን ተጐንጭተው ለክብር ከበቁ በሁዋላ የእግዚአብሔር ፍርድ ተገለጠ:: በጻድቃኑ እነ አባ ዓምደ ሥላሴ ሐዘን ንጉሡ ታመመ:: ምላሱ ተጐልጉሎ ወጣ::

በዚህ ጊዜ አቤቶ ፋሲለደስ ለአባ ዓምደ ሥላሴና ለሌሎቹ ቅዱሳን "አባቴን አድኑልኝ! ተዋሕዶም ትመለስ" አላቸው:: ጻድቁም ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጸልየው ንጉሡን አዳኑት:: በፈንታውም ይህንን አሳወጁ::

ፋሲል ይንገሥ!
ሃይማኖት (ተዋሕዶ) ይመለስ!
የሮም ሃይማኖት ይፍለስ!

ከዚህ በሁዋላ በ1624 ዓ/ም ፋሲል ሲነግሥ አባ ዓምደ ሥላሴ ለገዳማቸው ብዙ ቦታ አስከልለው : በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

አምላከ ቅዱሳን በቀናችው እምነት ተዋሕዶ ሁላችንም እስከ ፍጻሜ ዘመናችን ያጽናን:: ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን::

የካቲት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አባ አንስጣስዮስ ርቱዓ ሃይማኖት (ዘአንጾኪያ)
2.አቡነ ዓምደ ሥላሴ


ወርኀዊ በዓላት


1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
5.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
6.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
7.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

"የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::"
(1ዼጥ. 2:21-25)

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl






እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሆሴዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ

ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
- 15ቱ አበው ነቢያት:
- 4ቱ ዐበይት ነቢያት:
- 12ቱ ደቂቀ ነቢያትና
- ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

"15ቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
- ቅዱስ አዳም አባታችን
- ሴት
- ሔኖስ
- ቃይናን
- መላልኤል
- ያሬድ
- ኄኖክ
- ማቱሳላ
- ላሜሕ
- ኖኅ
- አብርሃም
- ይስሐቅ
- ያዕቆብ
- ሙሴና
- ሳሙኤል ናቸው::

4ቱ ዐበይት ነቢያት

- ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
- ቅዱስ ኤርምያስ
- ቅዱስ ሕዝቅኤልና
- ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

12ቱ ደቂቀ ነቢያት

- ቅዱስ ሆሴዕ
- አሞጽ
- ሚክያስ
- ዮናስ
- ናሆም
- አብድዩ
- ሶፎንያስ
- ሐጌ
- ኢዩኤል
- ዕንባቆም
- ዘካርያስና
- ሚልክያስ ናቸው::

"ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
- እነ ኢያሱ
- ሶምሶን
- ዮፍታሔ
- ጌዴዎን
- ዳዊት
- ሰሎሞን
- ኤልያስና
- ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
- የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
- የሰማርያ (እሥራኤል)ና
- የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
- ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
- ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
- ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)
- ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
ቅዱስ ሆሴዕ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ሆሴዕ 'ዖዝያ' በመባልም ይታወቃል:: ቅዱሱ ነቢይ የቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ-ቃል ባልንጀራ የነበረ ሲሆን በ4 ነገሥታት ዘመን (ዖዝያን : ኢዮአታም : አካዝና ደጉ ሕዝቅያስ) ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናግሯል:: የትንቢት ዘመኑም ከ70 ዓመት በላይ ነው::

ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሆሴዕ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራም በስፋት ተንብዩዋል:: 14 ምዕራፎች ያሉት የትንቢቱ ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል:: ሆሴዕ ማለት መድኃኒት ማለት ነው:: የመዳን ትምሕርትንና ትንቢትን ሊናገር ተመርጧልና::

  ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::

የካቲት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ (ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት)
2.ቅዱስ ሳዶቅ ሰማዕት
3."808" ሰማዕታት (ከቅዱስ ሳዶቅ ጋር የተሰየፉ)

ወርሐዊ በዓላት


1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንመለስ:: እርሱ ሰብሮናልና: እርሱም ይፈውሰናል:: እርሱ መትቶናል: እርሱም ይጠግነናል:: ከሁለት ቀን በሁዋላ ያድነናል:: በሦስተኛውም ቀን ያስነሳናል:: በፊቱም በሕይወት እንኖራለን:: እንወቅ:: እናውቀውም ዘንድ እንከተል . . . "
(ሆሴዕ 6:1-3)

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl




እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡፋና እና ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አባ አቡፋና

ታላቁ አባ አቡፋና፦
በምድረ ግብጽ ተጋድሏቸውን የፈፀሙ፣
በመዐልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊትም አምስት ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልዩ የነበሩ፣
በአርባ ቀን አንድ ጊዜ ብቻ እህል ይቀምሱ የነበሩና ሙሉ ዘመናቸውን በበርሃ በታላቅ ጽሙና የፈፀሙ አባት ናቸው።

ጻድቁ በጣም የሚታወቁት ከማበጡ የተነሳ እጅግ ግዙፍ በነበረ እግራቸው ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስለ መድኃኔ ዓለም ፍቅር አልቀመጥም፤ አልተኛም ብለው ለአሥራ ስምንት ዓመታት በመቆማቸው ነው።

አሥራ ስምንት ዓመት የመቆማቸው ዜናስ እንደምን ነው ቢሉ፦
አንድ ቀን "እኔ ግን ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ይሆን?" ሲሉ አሰቡ። በእርግጥ ይህንን ሐሳብ ብዙ ሰዎች ሊያስቡት ይችላል። ሐሳቡ ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው።
1. "ጠቃሚ ነው።" ያልኩት አንድ ሰው ሞት እንዳለ ካወቀ ወይም 'መቼ ነው የምሞተው' ብሎ ካሰበ ንስሐ ይገባል፤ ክፋትን ይተዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ወገኔ ሁሉ እንደ አውሬ ሲባላ፣ ደም ሲያፈስ፣ ክፋትን ሲጐነጉን የሚውል "እሞት ባይ" ሳይሆን "እኖር ባይ" ሆኖ ነውና።
ግን ሞት በቅርቡ እንዳለ በኃያሉ አምላክ ፊት ራቁቱን ለፍርድ እንደሚቀርብ ለወገኔ ማን በነገረው!
2. "ያልተፈቀደ ነው።" ያልኩት ደግሞ በሁለት ምክንያት ነው።
"ኢትበሉ ለጌሰም (ለነገ አትበሉ።)" የሚል አምላካዊ ቃል ስላለ።
ማቴ. ፮፥፴፬
ሰው (በተለይ ዓለማዊው) የሚሞትበትን ቀን ቢያውቅ አጭር ጊዜ ከሆነ ሽብር ጭንቀት ይበላዋል። ወዲህ ደግሞ ጊዜው ረዥም ቢሆን እንደ ሰብአ ትካት (ማለትም በኖኅ ዘመን እንደ ነበሩ ሰዎች) 'ብዙውን ልዝናናበት (ኃጢአት ልሥራበት')ና ንስሐ እገባለሁ።' ይላልና ነው።

በዚያውም ላይ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ሰውና የነቢያት አለቃ ቅዱስ ሙሴ የሞቱን ጊዜ ጠይቆ እጅግ መቸገሩን መጥቀሱ በራሱ በቂ ነው። ጌታ "ዓርብ ቀን ትሞታለህ።" ብሎት ለሁለት ዓመታት ዓርብ ዓርብ ሲገነዝ ሲፈታ ኑሯል።

በመጨረሻም ዓርብ ቀን ድንገት መልአከ ሞት መጥቶበታል። ስለዚህ "ወድልዋኒክሙ ንበሩ - ተዘጋጅታችሁ ኑሩ። መባላችንን አስበን ልንኖር ግድ ይለናል።
ማቴ. ፳፬፥፵፬

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አቡፋና ይህንን የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ "ተርፈከ አሠርቱ ወሰመንቱ - አሥራ ስምንት ቀርቶሃል።" አላቸው። እርሳቸውም "ጌታዬ አሥራ ስምንት ምን?" ሲሉ ቢጠይቁትም ሳይመልስላቸው ተሠወረ።

ከደቂቃ እስከ ኢዮቤልዩ ብዙ አሥራ ስምንቶች አሉ። እርሳቸው ግን "አሥራ ስምንት ቀን ነው!" ብለው ለጌታ ተሳሉ። ስዕለታቸውም "ከዚህ በኋላ አልቀመጥም።" የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ለአሥራ ስምንት ቀናት ቆሙ። ሞት አልመጣም።

"አሥራ ስምንት ሱባኤ ይሆን!" ብለው አሥራ ስምንት ሱባኤ (መቶ ሃያ ስድስት ቀናት) ቆመው ጸለዩ። አሁንም ሞት አልመጣም። "አይ! አሥራ ስምንት ወር ሊሆን ይችላል።" ብለው ለአሥራ ስምንት ወራት (ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር) ቆመው ተጉ። አሁንም ግን ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

ይህን ጊዜ ግን ወደ ፈጣሪ ለመኑ። "ጌታዬ! ያልከኝ ምን አሥራ ስምንት ነው?"
ቅዱስ መልአኩም መጥቶ "አቡፋና ሆይ! የቀረህ አሥራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና።" ብሏቸው ተሰወረ። ልብ በሉልኝ "እስክሞት አልቀመጥም።" ብለው ተስለዋል።

ቅዱሱ ገዳማዊ በቃላቸው የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያን ነበሩና ለአሥራ ስምንት ዓመታት እንደተተከለ ምሰሶ ቆመው ጸለዩ፣ ጾሙ። እንዲህ ያሉትን ቅዱሳን ሊቃውንት፦
"ሰላም ለከ ጽኑዕ ከመ ዓምድ
ዘኢያንቀለቅሎ ሞገድ።"
(ማዕበለ ዓለም የማያናውጸው ብርቱ ምሰሶ ሆይ! ምስጋና ይገባሃል።) የሚሏቸው።

ስለ ቅዱሱ የተጻፈ አርኬም፦
"ሰላም ለቁመተ አቡፋና ዘአልቦ ኑታጌ
እስከ ተመሰለ እግሩ ከመ እግረ ነጌ።" ይላል። ከመቆም ብዛት አካላቸው ደቆ እግራቸው የዝሆን እግር እስኪመስል ወፍሮ ነበርና።

   አባ አቡፋና በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን አርፈዋል።

    ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት

* ቅዱስ እንጦኒ በትውልዱ ከሶርያ ዐረቦች ሲሆን በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ካህናትን ይደበድብ፣ አብያተ ክርስቲያናትንም ያቃጥል ነበር። እግዚአብሔር በንስሐ ሲጠራው ግን ደግ፣ ጻድቅና ምርጥ ዕቃ ሆኖ ተገኘ። በመጨረሻም ከብዙ መከራ በኋላ ለሰማዕትነት በቅቷል።

   አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ትጋት፣ ጽናት፣ ፍቅርና በረከት ያድለን። ከማስተዋልም አያጉድለን።

የካቲት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
2.ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት
3.ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞናና ሉቅያ ድንግል (የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዛሙርት)
4.ቅዱስ ቶና ዲያቆንና ሰማዕት
5.ቅዱስ ሚናስ ዘሃገረ ቁስ

ወርኀዊ በዓላት


1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

"ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ። አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ። ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።"
(፩ጢሞ ፩፥፲፪-፲፫)

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl




እንኳን ለአባታችን ቅዱስ አጋቢጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዱስ አጋቢጦስ

   ቅዱስ አጋቢጦስ:-
- ይህንን ዓለም ንቆ ለበርካታ ዘመናት በፍፁም ምናኔ የኖረ::
- ምድራዊ ሃብትና ሹመት ሞልቶለት ሳለ ከሁሉ የክርስቶስን ፍቅር የመረጠ::
- ከደግነቱ ብዛት የተነሳ ምግብ ሲያዘጋጅ ሽምብራውን ከክቶ ለሌሎች ከሰጠ በሁዋላ ለራሱ የሚመገበው ገለባውን (አሠሩን) ነበር::

ሌሊቱን በጸሎት ለመትጋት ማታ ማታ አመድ ይመገብ ነበር:: በዚህም ቅዱስ ዳዊት "አመድን እንደ እህል በላሁ" ያለው በዚህ ቅዱስ ሕይወት ላይ ተገልጧል:: (መዝ. 101:9)

ቅዱስ አጋቢጦስ በዘመኑ ከሠራቸው ይህኛው እጅግ ይገርመኛል:: እርሱ በበርሃ የነበረበት ዘመኑ የሰማዕታት በመሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች በርጉማን መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ ተገድለዋል:: ቅዱሱን ግን በአካባቢው የነበረ ሃገረ ገዢ ከበዓቱ አስወጥቶ ወደ ውትድርና ሥራ አስገብቶታል::

ሰይጣን በዚህ ከተጋድሎና ከቅድስና ሕይወት እንደሚያርቀው ተማምኖ ነበር:: ቅዱስ አጋቢጦስ ግን በወታደሮች መካከል ሆኖም ተጋድሎውን ቀጠለ:: የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ቢሾሙትም እርሱ ከበጐ ማንነቱ ፈጽሞ አልተለወጠም::

ክርስቲያን ማለት እንዲህ ነውና:: ክርስትና ሲመቸን : ሲመቻችልን : በአጋጣሚ ወይም በምክንያት የምንኖረው ሕይወት አይደለም:: ፍጹም ፍቅር የጊዜ : የቦታ : የሁኔታ ገደብ የለውምና አባቶቻችን በጊዜውም : ያለ ጊዜውም ጸንተው ክርስቶስ መድኃኒታችንን አስደሰቱ::

ከቅዱስ ዻውሎስ ጋርም እንዲህ ሲሉ ዘመሩ:- "መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ" (ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል!)

ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አጋቢጦስ ለዘመናት ሰው ሳይገድል : ፈጣሪውን ሳይበድል : ከጾም ከጸሎት : ከምጽዋትና ትሕርምት ሳይጐድል ኖረ:: በዚህም ሰይጣንን አሳፈረ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

በዚህ ጊዜም ወደ በዓቱ ለመመለስ መንገድን ይፈልግ : ይጸልይም ገባ:: እግዚአብሔርም ወደ በርሃ የሚመለስበትን መንገድ በቸርነቱ አቀናለት::
ነገሩ እንዲህ ነው::
ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ራትዕ (የቀና) ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነገሠ:: ስደት ቆመ:: የታሠሩ ተፈቱ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጹ:: ለክርስቲያን ቀደምቶቻችንም ታላቅ ተድላ ሆነ::

ጊዜው ለሁሉ ክርስቲያን የተድላ ቢሆንም አንድ ወጣት በደዌ ሰይጣን ያሰቃየው ነበር:: ወጣቱ የንጉሡ የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ባለሟል : ባለብዙ ሃብት : መልኩ ያማረ ነውና ሁሉ ያዝንለታል:: ይልቁኑ ቅዱሱ ንጉሥ ተጨነቀለት::

አንድ ቀን ግን ከወታደሮቹ አንዱ ያን ወጣት "አንተንኮ አጋቢጦስ ይፈውስህ ነበር" ይለዋል:: ወጣቱ ግን አላወቀምና "ከመቼ ወዲህ የጦር አለቃ እንዲህ አድርጐ ያውቃል?" ሲል በጥያቄ ይመልስለታል:: ወታደሩ ግን ቀስ አድርጐ ምሥጢሩን ይነግረዋል::

ይህ ነገር ሲያያዝ ከንጉሡ ደርሶ ቅዱስ አጋቢጦስን አስጠርቶ "እባክህ ፈውስልኝ?" ይለዋል:: "ካዳንክልኝም የፈለግኸውን አደርግልሃለሁ" ሲል ያክልለታል:: ቅዱስ አጋቢጦስም ወደ ፈጣሪው ለምኖ ሰይጣንን ይገስጸዋል:: በቅጽበትም በክርስቶስ ኃይል ወጣቱ ይድናል::

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስም ከደስታው ብዛት "ምን ላድርግልህ?" ቢለው ቅዱሱ "ከሹመቴ ሻረኝ : ወደ በርሃ አሰናብተኝ" ብሎ መሻቱን ገለጸለት:: ቅዱሱ ንጉሥም በመገረም ቡራኬውን ተቀብሎ ወደ በርሃ ሸኝቶታል::

ወገኖቼ! . . . በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊው እርከን ስልጣንን የሚንቁ ሰዎችን ካላገኘን መፍትሔው ሩቅ ነው:: እኛም ከሥልጣን መሻት እንራቅ:: ማር ይስሐቅ እንደ ነገረን ሰይጣን ያደረበት ሰው ሹመትን (ሥልጣንን) በመሻቱ ይታወቃልና::

ቅዱሱ በፍፃሜ ዘመኑ እረኝነት (ዽዽስና) ተሹሞ ብዙ ኢ-አማንያንን ወደ ክርስትና መልሶ: ድውያንን ፈውሶ: እውራንን አብርቶ: በርካታ ተአምራትንም አድርጎ በዚህች ቀን አርፏል::

  ልመናው በረከቱ ይደርብን::

የካቲት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
2.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት (ዘጋዛ)
3.ቅዱስ ሚናስ ዘቆዽሮስ


ወርኀዊ በዓላት


1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምሕረ ትሩፋት)
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)

"የሚያሳድዷችሁን መርቁ . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ:: ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ:: እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ:: የትዕቢትን ነገር አታስቡ:: ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ::"
(ሮሜ. 12:14-16)

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl


[📲የስልካችሁን የመጨረሻ ቁጥር
ንኩ ከዛ በሚፈጠረውን ነገር ተዝናኑ።📱




ከርዕሰ ውጪ

በቅዱስ ጊዮርጊስ ረዳዕነት አደዋን ድል አደረግን

እንኳን ለ129ነኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ዕለት አደረሳቹ 🇪🇹




እንኳን ለታላቁ ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ ፖሊካርፐስ እና ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

   ቅዱስ ፖሊካርፐስ

  ቅዱስ ፖሊካርፐስ:-
- ከ70 እስከ 156 ዓ/ም የነበረ::
- ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ከመሰከረላቸው 7ቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ (የሰርምኔስ) ዻዻስ የነበረ::
- ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቃል በቃል የተማረና ደቀ መዝሙሩ የነበረ አባት ነው::

ታላቁ አግናጥዮስ (ምጥው ለአንበሳ) የዚህ ቅዱስ ባልንጀራ ነበር:: ከ46 ዓመታት በላይ በፍፁም ትጋት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎ አረማውያን በ86 ዓመቱ በአደባባይ በእሳት አቃጥለው ገድለውታል:: አባቶቻችን "ሐዋርያዊ" ሲሉ ይጠሩታል::

   ዳግመኛ በዚህ ዕለት በ1888 ዓ/ም በቅዱስ ጊዮርጊስ ምልጃና ረዳትነት አባቶቻችን አድዋ ላይ ጣልያንን ድል አድርገዋል:: ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ደጉን ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እናስባቸው ዘንድ ይገባል::

   ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት

በቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር ከሆነ ቅዱሳን ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ አውሳብዮስ ነው:: ተወልዶ ያደገው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘ ነው:: አባቱ ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እናቱም ቡርክት ሶፍያ ትባላለች::

ሰማዕቱ ቅዱስ መቃርስ ትንሽ ወንድሙ መሆኑም ይታወቃል:: ቅዱሳን እነ ፊቅጦር : ገላውዴዎስ : ቴዎድሮስ : ዮስጦስ : አባዲር . . . ባልንጀሮቹ ሆነው ኑረዋል::

ቅዱስ አውሳብዮስ የቅዱስ ፋሲለደስ ፍሬ ነውና ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር ሆነ:: በቤተ መንግስት ውስጥ ስንት የተደላደለና የተቀማጠለ ነገር እያለ እርሱ ግን እንደ ቡሩክ አባቱ ንጽሕናን መረጠ:: የወርቅ ካባ ደርቦ ሲሰግዱ ማደር ምን ይደንቅ!

ያ ዘመን እጅግ ግሩም የሆኑ ቅዱሳን በቤተ መንግስት የታዩበት ነበር:: ቅዱስ አውሳብዮስ በምጽዋት : በጾምና ጸሎት የሚኖር ቢሆንም በየጊዜው ወደ ጦርነት ይላክ ነበር:: ምክንያቱም እርሱ ኃያል የጦር ሰው : የሠራዊቱም ሁሉ አለቃ ነውና:: በሔደበት ሁሉም በእግዚአብሔር ኃይል ድል ያደርግ ነበር::

አንድ ጊዜም ከፋርስ ቁዝ ሰዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ:: ይህንን ጦርነት በበላይነት እንዲመሩ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በኑማርያኖስ (ንጉሡ ነው) ተሹመው ወደ ሠልፍ ገቡ::

በጦርነቱ ጐዳና ላይ ሳሉ ግን አንድ አታላይ ሰላይ በጠላት እጅ እንዲወድቁ አደረጋቸው:: የተማረኩና የታሠሩ ዮስጦስና ሠራዊቱ ሲሆኑ ቅዱስ አውሳብዮስ ይህን ሰምቶ አለቀሰ:: ወደ ፈጣሪውም እየተማጸነ ለመነ::

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አረጋጋው:: ድል መንሳትንም ሰጥቶት አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ዮስጦስን አስፈታው:: ጠላቶቻቸውንም እያሳደዱ አዋረዷቸው:: "ወመጠውከኒ ዘባኖሙ ለጸርየ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ::

ከዚህ ሠልፍ በሁዋላ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በድል አድራጊነት ወደ አንጾኪያ ሲመለሱ ግን አንጀትን የሚቆርጥ ዜና ደረሳቸው:: አምላከ አማልክት ክርስቶስ ተክዶ ጣዖታት (እነ አዽሎን : አርዳሚስ) እየተሰገደላቸውም ደረሱ:: ይህንን ያደረገ ደግሞ የሰይጣን ታናሹ የሆነ ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ነው::

ቅዱሳኑንም ለጣዖት ስገዱ ሲል በአደባባይ ጠየቃቸው:: ድፍረቱ ያናደደው ቅዱስ አውሳብዮስ ግን ሰይፉን መዞ ወደ ንጉሡ ተራመደ:: ያን ጊዜ ንጉሡ ሸሽቶ ሲያመልጥ መሣፍንቱን ሜዳ ላይ በተናቸው:: አባቱ ቅዱስ ፋሲለደስ ባይገለግለው ኖሮ ኃያል ነውና ባላተረፋቸው ነበር::

ከቀናት በሁዋላ ግን ቅዱስ አውሳብዮስ በጾምና ጸሎት ሰንብቶ ሰማዕት ለመሆን ልቡ ቆረጠ:: ቅዱስ ሚካኤልና አባቱ ፋሲለደስም በምክር አበረቱት:: እርሱም በአጭር ታጥቆ በከሐዲው ንጉሥ አደባባይ ላይ ቆመ::

"እኔ ክርስቲያን ነኝ:: ክርስቶስን አመልካለሁ:: ለእርሱም እገዛለሁ:: ጣዖታት ግን ድንጋዮቸ ናቸውና አይጠቅሙም:: የሚሰግድላቸውም የረከሠ ነው::" ሲል አሰምቶ ተናገረ:: ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ እዚያው ሊገድለው ፈልጐ ነበር:: ቅዱሱ ተወዳጅ ሰው ነበርና ሁከት እንዳይነሳ አውሳብዮስ ወደ አፍሪቃ (ግብጽ) ሒዶ እንዲገደል ተወሰነበት::

በምድረ ግብጽም አረማውያን በእሳትም : በግርፋትም : በስለትም ብዙ አሰቃዩት:: ቅዱስ ሚካኤል ግን ገነትን አሳይቶ ከደዌው እየፈወሰ ተራዳው:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ገድለውት አክሊለ ክብርን ተቀዳጅቷል::

  አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታት ጽናታቸውን አድሎ ከበረከታቸው ይክፈለን::

  የካቲት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያዊ ሰማዕት (የሰርምኔስ ዻዻስ)
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት)
3.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት (የቅዱስ ፋሲለደስ ልጅ)
4.ቅዱስ አውስግንዮስ ሰማዕት

ወርኀዊ በዓላት


1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
3.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
4.አባ ሳሙኤል
5.አባ ስምዖን
6.አባ ገብርኤል

   "በሰርምኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልዐክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- ሞቶ የነበረው: ሕያውም የሆነው: ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል:-
'መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ . . . እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን: የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ::"
(ራእይ 2:8)

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

የካቲት 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


     አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

+ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
*እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ
ተሰኝተናል!
*ቅዱሱ አባታችን:- "ቡላ-የእግዚአብሔር አገልጋይ"
ብለን እንጠራሃለን::
*ዳግመኛም "አቢብ-የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን::

+እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም
እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን::
*አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
*ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን
የተቀበለ!
*ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን
የሚያወርስ!
*የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና
ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ
ይገባሃል እንላለን::

   ልደት

+አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/
ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት::
ወላጆቹ ቅዱስ
አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ::
ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ::

+በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ
ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም
ሳይተክለው
የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን
ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ:
ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"

    ጥምቀት

+ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት
ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን
በዱር
በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን
ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ
'አጥምቀው' አለችው::

+ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ:
እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ
ቅዱስ አሐዱ
ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ::
ከሰማይም ሕብስና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ
ቀድሶ ሁሉንም
አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን"
ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::

    ሰማዕትነት

+የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገውት ድንገት
ሕዳር 7 ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ
ኃላፊነትን
የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት
ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ
መኮንን
"ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ::

+በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ 18 ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል::

     ገዳማዊ ሕይወት

+ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ::

+ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ
ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው::

     ተጋድሎ

+አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን
ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል:
ፊቱን
በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል:
ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል::

+በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ
ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት
እያሰበ ይቀበላል::
ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት
ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር::

የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ
ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም
ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም
መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት
ነሕና ስምህ
አቢብ (ሃቢብ) ይሁን" አለው::

"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ:
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ:
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል::


          ዕረፍት

+አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ
መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት
እየተጨዋወተ
ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ10 ጊዜ በላይ ሙቶ
ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት
ተሞላ::
+ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ!
ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን
እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ
'አምላከ አቢብ ማረኝ' ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ
የሚለምነኝን: በስምሕ እንኳ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ
እምርልሃለሁ"
ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ
ተደረገ::

አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን::

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

እንኩዋን ለቅዱስ "አናሲሞስ ሐዋርያ" እና ለእመቤታችን "ቅድስት ድንግል ማርያም" በዓል በሰላም አደረሳችሁ

   ድንግል ማርያም

የአምላክ እናቱ እመ-ብርሃን ድንግል ማርያም:-
- በ3 ወገን (በሥጋ: በነፍስ: በልቡና) ድንግል
- በ3 ወገን (ከኀልዮ: ከነቢብ: ከገቢር) ንጽሕት
- ሳትጸንስ: በጸነሰች ጊዜና ከጸነሰች በሗላ ድንግል
- ጌታን ሳትወልድ : በወለደችው ጊዜና ከወለደችው በሗላ ድንግል ስትሆን እናትም ድንግልም መሆኗን አምነን እመሰክራለን::

እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ በላይ ክብርትና ንዕድ ናት:: ሊቃውንት አበው እንዳስተማሩን በዚህ ዕለት እንዲህ ብለን እንጸልያለን::
"ረስዪ ፍና ትሕትና አእጋርየ ይሑሩ:
ትዕቢትሰ ለአምላክ ጸሩ"
(እመቤቴ ሆይ ትዕቢትን አምላክ ይጠላልና እግሮቻችን በትሕትና እንዲሔዱ አድርጊ)

  ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ

  በዘመነ  ሐዋርያት ምስጉን ከነበሩ አበው አንዱ ቅዱስ አናሲሞስ ነው:: ስለ ቀና አገልግሎቱና መልካም እረኛነቱ አባቶቻችን ሐዋርያት አብዝተው በቀኖናቸው መስክረውለታል:: እርሱ ከኃጢአት ኑሮ ወደ ዘለዓለማዊ የቅድስና ሕይወት መጥቷልና::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

በሮም ከተማ የሚኖር ፊልሞና የሚባል አንድ ባለጸጋ ነበር:: ይህ ሰው በስብከተ ቅዱስ ዻውሎስ አምኖ ከርስቲያን ሆነና በመንፈሳዊ አገልግሎት ተጠመደ:: ነገር ግን ከአገልጋዮቹ መካከል ያላመነ አንድ ሰው ነበር:: "ተጽዕኖ አላደርግበትም" ብሎ ዝም ይለዋል:: ግን ክርስትና እንዲገባው ለተልዕኮ መንፈሳዊ በሚሔድበት ሥፍራ ያስከትለው ነበር::
አገልጋዩ ግን በመለወጥ ፈንታ ሌብነትን ለመደ:: ይባስ ብሎም የአሳዳሪውን (የፊልሞናን) ገንዘብ ሠርቆ ወደ ሮም ጠፍቶ ተመለሰ:: ቅዱስ ፊልሞናም ለገንዘቡ ሳይሆን ለሕይወቱ አዘነ::

ያ ሠርቆ የጠፋው አገልጋይ ግን በሮም ከተማ ሲመላለስ ስብከተ ወንጌልን ይሰማል:: ሰባኪው ደግሞ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ነበር:: ቁጭ ብሎ ሲማርም ልቡናው በርቶለት ተጸጸተ:: ከሐዋርያውም ዘንድ ቀርቦ ኃጢአቱን ተናዞ ተጠመቀ::
ከዚያች ዕለት ጀምሮም ብርቱ ክርስቲያን ሆነ:: በጥቂት ጊዜም የተጋ ሰባኪ : ርሕሩሕ እረኛ ሆነ:: ፈጣሪውንም ደስ አሰኘ:: ነገር ግን ስለ አንድ ነገር ፈጽሞ ያዝን : ይተክዝም ነበር::

የድሮ አሳዳሪው ቅዱስ ፊልሞና እንዳዘነበት እያወቀ ዝም ማለት ባያስችለው ለመምህሩ ቅዱስ ዻውሎስ ነገረው:: ያን ጊዜም ሐዋርያው በእሥራትና በግርፋት ይሰቃይ ነበር:: በሮም ሳለም አጭር ክታብ (ደብዳቤን) ጽፎ ለዚህ ደቀ መዝሙሩ ሰጠውና ወደ ቀድሞ አሳዳሪው ወደ ፊልሞና ላከው::
ይህች ጦማር (ክታብ) ዛሬም ድረስ ከ81ዱ አሥራው መጻሕፍት : ከቅዱስ ዻውሎስ 14 መልዕክታት አንዷ ሆና ተቆጥራ እንጠቀምባታለን:: ክታቧ እጅግ አጭር ብትሆንም ምሥጢሯ ግን ሰፊ ነው::

ያ የተላከ ክርስቲያንም ያችን ክታብ ወስዶ ለቅዱስ ፊልሞና (ለቀድሞ አሳዳሪው) አስረከበ:: ቅዱስ ፊልሞናም በደስታ አቅፎ ሳመው:: ቀድሞውንም ያዘነ በወጣቱ አገልጋይ የነፍስ እዳ እንጂ በገንዘቡ አልነበረምና:: ያ ተላኪ ሰውም በአካባቢው ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ቅዱስ ዻውሎስ ተመልሷል:: ደቀ መዝሙሩ ሆኖም ብዙ አገልግሏል::
ቅዱስ_አናሲሞስ ማለት . . . የቀድሞ የሰው አገልጋይ . . . ዛሬ የክርስቶስ ባሪያ . . . ቀድሞ ሠራቂ . . . ዛሬ ግን ለመንጋው የሚራራ ሰው የሆነው ይህ ክርስቲያን ነው::

በ67 ዓ/ም ቅዱስ ዻውሎስ መሰየፉን ተከትሎ እርሱንም አሳድደው : አሰቃይተው : ጭኑንም ሰብረው አሕዛብ ገድለውታል:: በሰማይም የሐዋርያነትና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጅቷል:: (ጢሞ. 4:6-8, ፊልሞና 1:1-25)
አምላከ ቅዱሳን የአናሲሞስን መመለስ : ንስሃና በረከት ያድለን::

የካቲት 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ (የቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዝሙር ሲሆን ከ14ቱ መልዕክታት አንዱ የሆነው 'ወደ ፊልሞና' የተጻፈው በዚህ ቅዱስ ምክንያት ነው:: ፊል. 1:11)
2.አባ ዘካርያስ ዘሃገረ ስሃ
3.አባ አካክዮስ ጻድቅ
4.አባ ገብርኤል ሊቀ ዻዻሳት
5.አባ ገብርኤል (የኢትዮዽያ ዻዻስ)

ወርኀዊ በዓላት


1.ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

ስለ ጽዮን ዝም አልልም . . . አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ:: የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ:: በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ:: +"+ (ኢሳ. 62:1-3)

(ወስብሐት ለእግዚአብሔር)

@mehereni_dngl

Показано 20 последних публикаций.