የዱቤ (ክሬዲት) ሽያጭ እና የኢትዮ ቴሌኮም የባላንስ ብድር ሸሪዓዊ ብይን
""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
๏| ነሲሓ መጽሔት ቅጽ Vol2 ቁጥር 1 |๏
https://telegram.me/nesihablog ሀገራችን ሙስሊም ጥቂት የማይባለው ህዝብ የተሰማራበት የስራ ዘርፍ ንግድ ነው። ታዲያ በዚህ የንግድ ስራ ላይም ይሁን አገልግሎት ወይም ምርቶችን ስንገዛ ከሚያጋጥሙን የግብይት አይነቶች አንዱ የዱቤ ግብይት ነው። በዱቤ (ክሬዲት) የምንገዛው እቃ ወይ ደግሞ አገልግሎት (ሰርቪስ) ሲሆን፤ እቃውን ወይም አገልግሎቱን ተረክበን ወይም ተጠቅመን ክፍያውን ከተወሰነ ግዜ በኋላ በአንዴ ወይም ከፋፍለን የምንፈፅምበት የግብይት አይነት ነው። በዚህ ፅሁፍ የዚህን የግብይት ፊቅህ ቀለል ባለ መልኩ ለመቃኘት እንሞክራለን። በቅድሚያ ጭማሪ የሌለበት የዱቤ አሰራር እንዴት እንደሚታይ ከዳሰስን በኋላ በዱቤ ሽያጭ ላይ ስለሚደረገው ጭማሪ ብይን እንመለከታለን።
1/ ያለ ጭማሪ የሚፈጸም የዱቤ ግብይት (ነሲአህ) ሸሪዓዊ ብይን
በዱቤ መገበያየት የተፈቀደ መሆኑን የሚያመለክቱ ግልጽ ሐዲሶች ስለሚገኙ ሊቃውንቶች ተስማምተውበታል። ሆኖም እንደ ወርቅና ብር (ሲልቨር) ያሉ ጥቂት ሸቀጦችን እጅ በእጅ እንጂ ዱቤ ግብይት መሻሻጥን የሚከለክሉ ሀዲሶች ይገኛሉ። ይህ ግን ሁሉንም ግብይቶች አይምለከትም። በሚከለክሉት ሀዲሶች ተዘርዝረው ከተጠቀሱ ነገሮች ውጭ ባሉ ግብይቶች በዱቤ ሽያጭ መገበያየት ይፈቀዳልን በማለት አንዳንዶች ይጠይቃሉ።
روى البخاري ومسلم عَنْ عَائِشَةَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهَا أَنَّ النَّبِيَّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ اشْتَرَى طَعَامًا مِنْ يَهُودِيٍّ إِلَى أَجَلٍ وَرَهَنَهُ دِرْعًا مِنْ حَدِيدٍ.
ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሐዲስ እናታችን አዒሻ -ረዲየላሁ ዓንሀ- እንዳወሩት "የአላህ መልእክተኛ -ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም- ከአንድ የሁዲ ምግብ በዱቤ ገዝተው የብረት ጡሩራቸውን ማስያዣ ሰጥተውታል"
የዱቤ አከፋፈል በአንዴም ይሁን በተከፋፋለ ሁኔታ ቢደረግ ተመሳሳይ ሑክም/ብይን ይኖረዋል። ቡኻሪ የዘገቡት ሌላ ሐዲሥ ይህንን በሚያጠናክር ሆኖ እናገኘዋለን፤
عَنْ عَائِشَةَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهَا ، قَالَتْ : جَاءَتْنِي بَرِيرَةُ فَقَالَتْ : كَاتَبْتُ أَهْلِي عَلَى تِسْعِ أَوَاقٍ ، فِي كُلِّ عَامٍ وَقِيَّةٌ...
እናታችን አዒሻ፤ "በሪራ ወደኔ መጥታ ከአሳዳሪዎቿ ጋር (ቀድመው ነፃ አውጥተዋት) በየአመቱ የሚከፈል ዘጠኝ ወቂያ ልትከፍል መዋዋሏን ነገረችኝ" ማለታቸውን ቡኻሪ ዘግበውታል። [ወቂያ ማለት= 40 የሲልቨር ዲርሀም ነው]
እነዚህ ሁለት ሐዲሶች የዱቤ ግብይት መፈቀዱን ያስገነዝቡናል። ከሁለተኛው ሐዲስ ደግሞ የአከፋፈል ሁኔታው ቢለያይ ችግር እንደሌለው እንረዳለን። ይህም ማለት፤ ገዥ እዳውን በአንዴ ወይም በተወሰነ የመክፈያ የግዜ ሰሌዳ አቆራርጦ (በተቅሲጥ) ሊከፍል ይችላል።
2/ ከዋጋ ጭማሪ ጋር የሚፈጸም የዱቤ ግብይት ሸሪዓዊ ብይን
የዕቃው ወይም የአገልግሎቱ ሽያጭ በካሽ ሲፈጸምም ይሁን በዱቤ ሲሸጥ እኩል የዋጋ ተመን የሚኖርበት አሰራር ቢኖርም፤ የዱቤ ሽያጭ ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚደረግበት አሰራርም የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ፤ ገዥ የተለያዩ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸውን እንደ ቤት፣ መኪናና ማሽነሪዎች በረዥም ግዜ በሚከፈል ክፍያ በዱቤ በመውሰድ አሁን ካላቸው የገበያ ዋጋ ተጨማሪ ለመክፈል ይስማማል። በዱቤ በተሰጠው ዕቃ/አገልግሎት ላይ ይህ አይነቱ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ ብዙ ሰዎች ዘንድ ይህ ነገር ከሸሪዓ አንፃር ይፈቀዳልን? ከወለድስ በምን ይለያል? የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል።
ከላይ በቁጥር 1 ማብራሪያ እንዳየነው ያለ ጭማሪ የሚደረጉ የዱቤ ሽያጮች እንደሚፈቀዱ አያወዛግብም። ሆኖም፤ በዱቤ ሽያጭ ላይ ጭማሪ ክፍያን መጠየቅ እንደሚቻል የሚጠቁም ግልፅ መረጃ ባለመኖሩ ኡለማዎችን አወዛግቧል። ከሸሪዓዊ የግብይት ህጎች አንፃር ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት ስንሞክር፤ መስፈርቶችን እስካሟላ ድረስ ጭማሪ መጠየቅን የሚከለክል መረጃ ባለመኖሩ ግብይቱ የተፈቀደ መሆኑን እንረዳለን። ይህንን አቋም የሚያጠናክሩ የተለያዩ መረጃዎችን እናገኛለን። ስለዚህም አራቱን የፊቅህ መዝሐቦች ሊቃውንት ጨምሮ ብዙሀኑ ታላላቅ ኡለማዎች (ጁምሑር) ይህንን ሁክም (ብይን) የሚያሳዩ መረጃዎችን በመጥቀስ እንደሚፈቀድ ያረጋግጣሉ።
ከነዚህ መረጃዎች መካከል፤
1) አላህ እንዲህ ብሏል፤
وأَحَلَّ اللَّهُ الْبَيْع
"አላህ ግብይትን ፈቅዶላችኋል" አልበቀራ 275
ይህንን አንቀፅ እና መሰል መረጃዎችን መነሻ በማድረግ የፊቅህ ጠበብቶች ማንኛውም የግብይት መስተጋብሮች ትክክለኛ በሆነ መረጃ ክልከላ እስካልመጣባቸው ድረስ የተፈቀዱ መሆናቸውን በመግለፅ መሰረታዊ መርሆ ያስቀምጣሉ። ይህ አንቀፅ የትኛውንም የግብይት አይነት ያካትታልና በዱቤ ለሚሸጥ እቃ የዋጋ ጭማሪን የሚያደርግ ግብይትም በዚሁ አንቀፅ ማዕቀፍ ውስጥ ይገባል። ስለዚህም ግብይቱ እንደሚፈቀድ ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መካከል አንቀፁ ተቀዳሚ ሆኖ ይጠቀሳል።
2) ሌላኛው መረጃ ደግሞ ተከታዩ አንቀፅ ነው፤
يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لا تَأْكُلُوا أَمْوَالَكُمْ بَيْنَكُمْ بِالْبَاطِلِ إِلا أَنْ تَكُونَ تِجَارَةً عَنْ تَرَاضٍ مِنْكُمْ
"እናንተ ያመናችሁ ሆይ በመሀከላችሁ ገንዘባችሁን ያለአግባብ አትብሉ። ወዳችሁ በምትፈፅሙት ግብይት ካልሆነ በስተቀር" ኒሳእ 29
የዚህ አንቀፅ ጥቅል መልዕክት እንደሚያመለክተው፤ በሁለቱም ወገኖች መካከል መፈቃቀድ እስካለ እና በፍቃደኝነት ግብይቱን እስከፈፀሙ ድረስ ግብይቱ የተፈቀደ መሆኑን ነው።
3) ከሚጠቀሱ መረጃዎች መካከልም ተከታዩ ሐዲሥ አንዱ ነው፤
عَنْ ابْنِ عَبَّاسٍ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا قَالَ : قَدِمَ النَّبِيُّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ الْمَدِينَةَ وَهُمْ يُسْلِفُونَ بِالتَّمْرِ السَّنَتَيْنِ وَالثَّلَاثَ فَقَالَ: مَنْ أَسْلَفَ فِي شَيْءٍ فَفِي كَيْلٍ مَعْلُومٍ ، وَوَزْنٍ مَعْلُومٍ، إِلَى أَجَلٍ مَعْلُومٍ . رواه البخاري
ኢብን ዓባስ -ረዲየላሁ ዓንሁማ- እንዳወሩት "ነቢዩ -ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም- መዲና የገቡ ግዜ (የመዲና ሰዎች ሲገበያዩ) ከሁለትና ሶስት አመት በኋላ ለሚፈጸም የተምር ርክክብ አስቀድመው ሲከፍሉ አገኟቸው። እሳቸውም ለአንዳች ነገር አስቀድሞ የሚከፍል ሰው በሚታወቅ ስፍር፣ በሚታወቅ ክብደት፣ በሚታወቅ ጊዜ ያድርግ አሉ" ቡኻሪ ዘግበውታል
በዚህ ሐዲስ የተጠቀሰው “ሰለም” የተባለው የግብይት አይነት ሲሆን፤ እርሱም የእቃውን ዝርዝር ሁኔታ ከተረዱ በኋላ በቅድሚያ መክፈል ነው። ይህ ግብይት እንደሚፈቀድ ግልጽ መረጃ ከመጠቀሱ ባሻገር የኡለማዎች ስምምነት “ኢጅማዕ” አለበት።
ግብይቱን ካስተዋልነው በይዘቱ የዱቤ ግብይትን ይመስላል። “ሰለም” እንደሚፈቀድ ኡለማዎች ሲያብራሩ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከል፤ ገዥ በዋጋ ቅናሽ ተጠቃሚ ሲሆን ሻጭ ደግሞ በቅድሚያ ከሚቀበለው ክፍያ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የሚያሳየው የክፍያ መዘግየት (ዱቤ) ከዋጋ ተመን ላይ እራ