አጀብ!
ሳንታጀብ!
ይህ በግርግር ዘመን ላይ ቆሞ የሚደነቅ ዘመነኛ ድምጽ ነው። የብቻ መንገዱን እየተመናተለ የሚገፋ ሰው ህቅታ። በሚያየው አጉል ዳንኪራ የሚሳቀቅ ብክን ነፍስ ሲቃ ነው። ሰው የመሆንን ውል ላጣን፣ እንደ ሸርጣን እየተጓተትን ለምንደማ መናኛዎች የተወረወረ የመገረም ቃል ነው።
ኖሮ ከሚታዘብ፣ ትርምስምሱን በአርምሞ ከሚመለከት ነፍስያ የሚቀዳ መባከን ነው። ቡድናዊነት እንደ ብራቅ ከሚጮህበት፣ አጀቡ፣ ወጀቡ ከሚያናፈበት ቀዬ የተገኘ ዘመነኛ የሚያስተጋባው ቃል ነው። አጀብ! ያውም ለብቻ ቆሞ።
አንድ ቀን ሳይሞላ!?
ወደ ነበረ ሆድ፣ ወደ ዛሬ ጥላ
ከነፍን
ታለፍን
እኔና ዘመኔ
ሀሳብና ህይወት፣ ሆነውብን ቅኔ፤
እነሆ ዘመን እንደ ጥላ እያለፈ ነው። ቀን ቀንን እየተካ እየተሸበለለ እልም ይላል። የሰው ልጅ እግሮች ወደ ሞት ይሰግራሉ።
ይሄ ሁሉ የሚጥመለመል ትውልድ አንድ ቀን እንኳን ኖሮ አያልፍም። አንድ ቀን ማለት ባህርይው ብዙ ነውና። በተለይ ለገጣሚማ አንድ ቀን ውሉ ብዙ ነው።
እነሆ የፀሐይ መግባትና መውጣት በቀን የተተለመ አይደለምን። ፀሐይስ ምንድን ነው ቢሉ ብርሃን አይደለምን? በብርሃን ለመመላለስ የታደለ ትውልድማ ምንኛ የበቃ፣ የነቃ ነው?
ትናንት ላይ ለመድረስ ስንባክን፣ ነበርን ለመሻገር ስንዳክር ይሄው አንዲት እለት እንኳን አልሞላንም። መክነፋችን ፣ መትመማችን፣ ከነበር ላለመሻገር መሆኑ አያስቆዝምም ወይ?
እንደ ዋዛ ያለፍነው እልፍ ነው። ከነገ ለመድረስ ስንንጠራራ ከትናንት ጥላ አንዲት ጋት አልተሻገርንም። ዘመን እንደ ጥላ እያለፈ፣ ጊዜ እንደ አቡጀዲ እየተተረተረ እንዴት ሰው ነገን ማየት ያቅተዋል? እንዴት ሰው ብርሃን መመልከት ይከብደዋል?
አጀብ!
የግርንቢጥ
ሰርክ በተቃርኖ
ማን ልቡን ይሰጣል፣ በዋጋ ተምኖ?
አጀብ! ይገርማል እናንትዬ። የሰርክ መባከናችን አያሳዝንም፣ አያስገርምም ወይ? ነገራቸን ሁሉ የግርንቢጥ መሆኑ ምንኛ ያንግበግባል? ልብ ቦታዋ የት ነው? ቅንነት፣ ንጽህና አይደለምን? እሱን የንጹህ ነፍስ አድባርስ እንዴት በዘመን ዋጋ ይተምንታል? ዘመንስ ዋጋው ምን ያህል ነው? የትውልድ ቁዘማ ለልብ ይደርሳልን?
እነሆ መቃቃራችን ለከት የለውም። ጨለማው ያስፈራል። ጭካኔው ያስደነብራል። ልብ አልባ ሰው መሆን ይገማሸራል። ሰውነት ያለ ልብ ምንድን ነው? ልብ የአስተውሎት ሁሉ አድባር አይደለምን? ታዲያ ሰው መሆንን፣ አስተውሎትን የተነጠቀ ዘመን ምን ይባላል? ልብን በዲናር መዝኖ ለሚንከላወስ ድንጉጥ ዘመን ማርከሻው ምንድን ነው? በጨለማ የተሰነገ ልቡን አቅፎ ለየብቻው ለሚርበተበት ትውልድ ዘመንስ ዋጋው ምን ያህል ነው?
እንገዛ ነበር
እኛም ባገር ዋጋ፣ ልብን ከሥጋ እኩል
ቃል ያጠፋውን ስም፣ ላይስቅለን ነገር ከምንኮለኩል።
(አቡዬን)
መፅሀፍ -አያምንምና ቀድሞም ያልካደ
ደራሲ- ታዲዮስ አዲሱ
@zephilosophy