በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
📖📖መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ላንብብ📖📖
ክፍል ፩(1)
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ለሚያመልኩ በእውነተኛው የእምነት ሕይወት መመራት ለሚፈልጉ ሁሉ የእምነትን በጎ ሥራ ማጣፈጫ የውስጥን ማንነት መለወጫ የውጪን ገጽታ በስነ-ምግባር መገንቢያ መሣሪያ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ እውነተኛ ይዘቱ አኳያ ሊነበብ ይገባል! የማንበቡን ጥቅም 2ጢሞ 3፡17፤ ት.ሕዝ 3፡1፤መዝ 118፡103 "የሰው ልጅ ሆይ አፍህ ይብላ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ።እኔም በላሁት በአፌ ውስጥ እንደማር ጣፈጠ"
የእግዚአብሔር ቃል አንደበትን የሚያጣፍጥ ህሊናን በበጎ ነገር የሚማርክ ውስጥን እየወቀሰ የሚያርም ነው! ስለዚ ዘውትር ልንበላውና በአፋችን ሊጣፍጥ ይገባል።መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማንበብ እንዳለብን ወደሚጠቁመን መሠረታዊ ነጥብ ስናልፍ፦ሁለት መሠረታዊ ነገሮች መረዳት አለብን።
1. አፍአዊ(ውጫዊ) ዝግጅት
2. ውስጣዊ(የውስጥ) ዝግጅት
ሁለቱንም በቅደም ተከተል ስንመለከት
1. አፍአዊ ዝግጅት
አፍአዊ ዝግጅት የሚባለው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነበው አካል ለማንበብ ከመቅረቡ በፊት ከልቦናውና ከአይምሮው ውጪ ሊያዘጋጀውና ለያመቻቸው የሚገባን የሚያጠቃልል ነው።አፍአዊ ዝግጅትን የግል ዝግጅትና የማህበር ዝግጅት በማለት በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
1.1 የግል ዝግጅት(የግል ንባብ)
የግል ዝግጅት (የግል ንባብ) አንባቢው በግሉ ሊያረግ የሚገባውን ሁሉ የሚመለከት ነው።ማለትም
👉የራስ(የግል) መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት
መጽሐፍ ቅዱስ ዕለት በዕለት የኑሯችን የመንፈስ ምግብ በመሆኑ ሊለየን አይገባም።በሕይወታችን ዋጋ ከፍለን መግዛትም ሆነ ማንበብ ካለብን መጽሐፍ ቅዱስ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለን እራሳችንን የምንተረጉምበትን ማብራሪያ አልያዝንም ማለት ነው።ለሰዎች የሕይወታቸው የመጀመሪያው ሀብት መጽሐፍ ቅዱስ ነው።መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት መሆን ግድ ነው።
ኦ.ዘዳ 6፡6-9 "ይህን ቃል በልብህ ያዝ ለልጅህም አስተምረው በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድህም ስትሄድ ስትተኛም ስትነሳም ተጫወተው በእጅህ ምልክት አርገህ እሰረው በአይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።" የመጽሐፍ ቅዱስና የሰው ትስስር ይህን ያህል ሊሆን ይገባል።
👉የሚያነቡበትን ቦታና ጊዜ መምረጥ
መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ስናነበው ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገርን መሆኑን መዘንጋት የለብንም።ስለዚህ ንግግራችን የተዋከበ ያልተሰበሰበ ሕሊና የሚታወክበት እንዳይሆን የሚደረገውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንባብ ጫጫታ፣ወሬ፣ግርግር፣ በዓይን እየታዩ ሊረብሹ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ ይገባል።ይህንን ለማድረግ የምንመርጠው ቦታና ጊዜ ወሳኝ ነው።
👉ማስታወሻ መያዝ
አበው በብሂላቸው "በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል" እንዲሉ በቃል ብቻ ማንበብ ለጊዜው በአንባቢው ህሊና ውስጥ ከሚፈጥረው ስሜት በስተቀር ሊረሳ ይችላል።እንዲህ አይነቱን ችግር ለመፍታት ማስታወሻ መያዝ ጥቅሙ የላቀ ነው።መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ማስታወሻ የሚይዝ አንባቢ ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወታችንን ታላቁን ጥያቄ የምንመልስበት በመሆኑ ተገቢ ነው።
1ጴጥ 3፡15 "በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ"
👉የማህበር ዝግጅት
ይህ ዝግጅት መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ቦታና ጊዜ በጋራ የሚያነቡ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባቸውን ዝግጅት ያጠቃልላል።
2. ውስጣዊ ዝግጅት
ውስጣዊ ዝግጅት የሚባለው አንድ ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ከመቀመጡ በፊት በልቦናው ሊያደርገው የሚገባውን ዝግጅት ነው ሚያመለክተው
ጠቅለል ባለ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ፦
1. የመጽሐፍ ቅዱስን አከፋፈልና ቁጥሮች ማወቅ
2. በፈሪሀ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን በመፍራት) መኖር
3. የምናነበው እንዲገባን መጸለይ
4. ያልገባንን ንባብ የምንጠይቃቸውን መምህራን አጋር ማረግ እጅግ ወሳኝ ነው።
በቀጣይ
📖የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም
📖የመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤ
📖የመጽሐፍ ቅዱስ አከፋፈል
📖የመጽሐፍ ቅዱስ ህዳግ አወጣጥ
📖የግዕዝ ቁጥር
📖መጽሐፍ ቅዱስን በጊዜና በሰአት ከፋፍሎ የማንበብን ስልት ይዤ እቀርባለሁ
ይቀጥላል
https://t.me/Abalibanos333