በግራኝ አሕመድ ወረራ ዘመን ለኢትዮጵያ ክርስትና መትረፍ ሰበብ የሆኑ በቀድሞ ሕይወታቸው ሙስሊም የነበሩና ክርስትናን የተቀበሉ ሁለት ሰዎች ነበሩ። አንደኛዋ የሐዲያዋ ተወላጅ ጥበበኛዋና ውቧ ንግሥት እሌኒ (በሌላ ስሟ የዘይላ ንግሥት) ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ የመናዊው ባለ ብሩህ አእምሮ በቀድሞ ስሙ አቡ አል-ፈት በክርስትና ስሙ አባ ዕንባቆም ነበሩ። ንግሥት እሌኒ በፖለቲካና በወታደራዊው መስክ፣ አባ ዕንባቆም ደግሞ በመንፈሳዊ መስክ የሠሩት ሥራ የኢትዮጵያን ክርስትና ከጥፋት ታድጓል። በተለይም አባ ዕንባቆም የግራኝን ሠራዊት ያሸነፈውን ንጉሥ ገላውዴዎስን ከልጅነቱ ጀምሮ በማስተማር፣ ከዚያም በጦርነቱ ዘመን የእስልምናን ሐሰተኝነት የሚገልጡ ጽሑፎችን (ለግራኝ ለራሱ ደብዳቤዎችን መጻፍን ጨምሮ)፣ በኋላም በጦርነቱ የወደሙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተካት እንዲሁም ከክርስትና የወጣውን ሕዝብ ወደ እምነቱ በመመለስ ረገድ ያበረከተው አስተዋፅዖ የሚረሳ አይደለም። የእነዚህ ሁለት ሰዎች በወቅቱና በቦታው መገኘት የእግዚአብሔር ተዓምራዊ ሥራ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም። የአባ ዕንባቆምን የሕይወት ታሪክና ጽሑፎች በተመለከተ አንድ ብዙ ዓመታትን የፈጀ ምሑራዊ ጽሑፍ በቅርቡ በሀገራችን ለሕትመት እንደሚበቃ መረጃው አለኝ።