“ኧረ ደሴ ደሴ ገራዶ ገራዶ
አለቀልሽ ልቤ ተንዶ ተንዶ…”
አለ አዝማሪ… ወ‘ዶ አይደለም፡፡ በቆንጆዎቹ የፍቅር ከተማ ደሴ ፍቅር ከንፎ ነው፡፡
1885 ዓ.ም ንጉስ ሚካኤል `ላኮመልዛ” ብለውም ሰይመዋት ነበር፡፡ ቃሉ የአፋን ኦሮሞ ሲሆን ትርጉሙ “የቆንጆ ማሠሪያ” ማለት ነው፡፡ ደሴ በር (እነርሱ “ሸዋ በር” ይሉታል) ሲደርሱ ዐይን ቁልቁል ይወረወራል፡፡ የከተማዋ መንደሮች ከዚህ ይጀምራሉ፡፡
“ሰኞ ገበያ” ይባላል፡፤ ማዘጋጃ ያላያቸው የጨረቃ ቤቶች መናኸሪያ ይመስላል፡፡ ወደ ውስጥ ቀረብ ካሉ የገበያው ሽታ ያስነጥስዎታል፡፡ አፍንጫዎን ቢሸፍኑም የሸንኮራ ዝንቦች አስገድደው ይወርዎታል፡፡ ራስዎን ለመከላከል ወደ አንድ ካፌ ዘለው ይግቡ፡፡ የሴኔጋል አሜሪካዊው ድምፃዊ ኤኮን ፖስት ካርድ ሊያፈጥብዎ ይችላል፡፡ ከጐኑ ሽጉጥ ያላቸው ቼኮሌት እንስት ቀልብዎን ስባ “ማነች” ብለው ከጠየቁ ግን “የሠፈራችን ልጅ ሮዚና” የሚል ፈጣን መልስ ያገኛሉ፡፡ በነገራችን ላይ ሮዚና ባለፈው ዓመት ወደ ሀገር ቤት ተመልሳ ጦሣ ላይ ችግኝ ተክላለች ብለውኛል ጓደኛቼ፡፡ ሮዚና የኤኮን ሚስት ስትሆን አንድ ወንድ ልጅም አፍርተዋል፡፡ “ሙጋድ፣ ኢራዳና ሸርፍ ተራ” የአንድ ሠፈር ስም ናቸው፡፡ የደሴ የልብ ትርታም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ የሃላባ በርበሬ በሚመስሉ ቆርቆሮዎችና አዳዲስ ሕንጻዎች የተዥጐረጐረው ይህ መንደር ከወሎ አደስና አርቲ እስከ ወፍጮ ማሽኖች ድረስ ይቸበቸባሉ፡፡ ገበያው ጣራ ከነካብዎ እንውጣና ፒያሳ እንሂድ፡፡ ፒያሳን ወዲያው ወድጃታለሁ፡፡ በምኗ ይመስላችኋል? ጉያዋ ስር በወተፈችው ት/ቤት ነው፡፡ መንገዶቿም በመጽሐፍት ደርዳሪዎች ተጊጣለች፡፡
የልብ ወጌሻው ዶ/ር በላይ አበጋዝ በወ/ሮ ስሒን ወንበሮች ተቀምጦ የሩኅሩሕነትን ፊደል ለቅሟል፡፡ ነፍሡን ይማርና መምህርና ገጣሚ ብርሀኑ ገበየሁም የጥበብ ዘር የተጠናወተው እዚሁ ወ/ሮ ስሒን እንደነበር ሰምተናል፡፡ ብታምኑም ባታምኑም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂም የወ/ሮ ስሒን ግርፍ ናቸው፡፡ ኧረ እንደውም የስምንተኛ ክፍል ውጤታቸውን ዐይተናል፡፡ የአማርኛ ውጤታቸውም ከሰማንያ በላይ ነበር ያሉ የደሴ አዛውንቶች አጋጥመውኛል፡፡
ዛሬ ወ/ሮ ስሒን ኮሌጅ ኾኗል፡፡ ጠጋ ብዬ አየሁት፡፡ መክበድ ሲገባው ቀሎብኛል፡፡ ምናልባት ጭርታ ስለወረረው ይሆናል፡፡ ወይም የ፩ኛ እና የ፪ኛ ደረጃ ተማሪዎችን ማስተማር ስላቆመ?
ዋናውን የአዲስ አበባ መቀሌ መንገድ ወደ ታች ወረድኩ፡፡ በግራና በቀኝ የሃብታም ቤት አጥር የሚያክሉ ረጃጅም ህንፃዎች ተደርድረዋል፡፡ ሼል፣ ቅዳሜ ገበያ፣ ሆጤ፣ መናፈሻ፣ ፔፕሲ፣ አሬራ /ዕውቀት ጢቅ ሰፈር/ ውልሎ፣ ሮቢት፣ ቧንቧ ውሃ፣ ዶልፊን... እና ሌሎች ስማቸው ያልተነገረኝ የደሴ ሠፈሮችን ገብቼ ወጣሁባቸዉ፡፡
ከከተሞች አሳልፋ በመስጠት የሚወዳደራት የለም ይባላል፡፡ በተለይ ሴቶቹን ወደ አረብ ሃገራት መላክ ከጀመረች ቆይታለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ደሴን ከበው የተመሠረቱት እነ ሐይቅ-መርሳ-ኩታበር-ወረኢሉ የተባሉ የገጠር ከተሞች ዋነኛ ግብዓት ናቸው፡፡ ይህ ባሕል ፊደል ቀመስ ወደሆኑት ወጣቶችም ተሸጋግሯል፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንደነገረኝ ከአምስቱ የመጀመሪያ ድግሪ ተማሪ ዶርም ተጋሪዎቹ መካከል ወደ ደሴ ፊቱን የመለሠው አንዱ ብቻ ነው፡፡ አራቱ በራሳቸው ሲቀልዱ እንዲህ ይላሉ፡፡
“ወሎ መውለድ እንጂ ማሳደግ አያውቅም
በረጅም አውቶብስ ይሠደዋል የትም፡፡”
ደሴ ውስጥ የሃይማት ልዩነት አያሳስብም፤ ሁሉም በፍቅር ይኖራል፡፡
መምሕር አካለወልድና ሼህ ሑሴን ጀብሪል አንድ ማዕድ ይቋደሡ ነበር ብላችሁ ታምናላችሁ? ግን እውነቴን ነው፡፡ እነዚህ ታላላቅ አባቶች በደሴ ትርክት ውስጥ ጉልህ ስፍራ አላቸው፡፡ ሼህ ሑሴን ጂብሪል በ1811 ዓ.ም በወርሂመኖ ተወለዱ፡፡ ለ97 ዓመታት በዚህ ምድር ላይ የቆዩት ሼህ ሑሴን እንደ ነብይ የሚቆጠሩ ሰው ነበሩ፡፡ ሼኪው በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መጻዒ ሁኔታዎች ላይ የሚሠጧቸው ትንበያቸው መሬት ጠብ የማይሉ ነበሩ፡፡
በሌላ በኩል መምሕር አካለ ወልድ ለትምህርት ባላቸው ልዩ ፍቅር በአካባቢው ኅብረተሠብ ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ በሕይወት ዘመናቸው የመሠረቱት ት/ቤትም ዛሬ እስከ መሠናዶ ድረስ ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡ ሁለቱ ሠዎች በጣም ጓደኛ ስለመሆናቸዉ የታሪክ አዋቂዎች ይመሠክራሉ፡፡ መምህር አካለ ወልድና ሼህ ሑሴን ጂብሪል ቡናቸውን እየጠጡ ስለ ሃገራቸው እድገትና ተስፋ ሃሣብ ይለዋወጡ ነበር፡፡ ስለ ማኅበረሠባቸው ልማትና ስኬት ይጨዋወቱ ነበር፡፡ ትኩስ እንጀራቸውን በወተት እያወራረዱም ኑሮ ያስተማሯቸውን ልምድ ይለዋወጡ ነበር - ነበር - ነበር፡፡
ደሴ እምብርት ላይ ቆሜያለሁ፡፡ አጠገቤ የአረብ መስጊድ አለ፡፡ ቀና ካሉ የመድኃኔ ዓለምን ቤተክርስቲያን ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህ የእምነት ተቋማት ካያችኋቸው በመቻቻል ፍቅራቸው ትቀናላችሁ፡፡ በመረዳዳት ባሕላቸው ትደመማላችሁ፡፡ በተመሳሠብ ወጋቸው ትኮራላችሁ፡፡ በዚህ ሠዓት ለሼክ ሁሴን ጂብሪል እና ለመምህር አካለ ወልድ ኮፍያችሁን ከፍ ታደርጋላችሁ፡፡ በፍቅር የተጣመሙትን በሮች በርግደው የሚበሩ ውብ ልጃገረዶች አሏት፡፡ አፍ የሚያስከፍቱ - ልብ የሚያስደነግጡ እና ሆድ የሚያላውሡ የእናቶች ፈገግታና ፍቅር ደሴ አለ፡፡ እውነቴን ነው እንስቶቹ እንደ ወንዶቹ ኮስታራ አይደሉም፡፡ መግባባት ይችሉበታል፡፡ ጨዋታ ያውቃሉ፡፡ እምነታቸውንም ወዲያው ይሠጣሉ፡፡ “ሸጋው ማደርያ ፈልገሃል እንዴ?” ብለውኛል መናኸሪያ ያገኙኝ አንዲት እናት፡፡
በመጨረሻም ደሴ የሆነ አዚም አላት፡፡ አዲስ እንግዳን እያናደደች ቢሆንም ቤተኛ ታደርጋለች፡፡ እያበሳጨችም ቢሆን የግሏ ታደርጋለች፡፡ እያቃጠለችም ቢሆን ታቀዘቅዛለች፡፡
“ደሴ ደረቅ ወይራ ገራዶ ቢላን፣
የስንቱ መወክል ለከፈኝ እኔን፡፡…”
የተባለው እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልጆቿ ግን ግጥሙን ሆነ የተገጠመላትን ከተማ የሚታገሱበት አንጀት ያላቸው አይመስሉም፡፡ ጥለዋት “እብስ” እያሉ ነው፡፡ ሊቢያ-ጅዳ-ጁባ-አሜሪካ... ከስምንት ዓመት በፊት ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደሴ ተከስቶ ነበር፡፡ ትዝብቱንም በእፍታ የዘገበውን አስቂኝ ትረካዎች ላይ እንዲህ አስፍሯል፡፡ “...ደሴን ተዘዋውሬ አየኋት አርጅታለች፡፡ በእውነቱ በጣም አርጅታለች፡፡ በተራሮች መሰል የተወተፈችው ደሴ ለከተማ ምቹ ባልሆነ ሥፍራ መመስረቷ ላለማደጓ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም፡፡” እና ያገሬው ሠው “አገር ሲያረጅ ደሴን ይመስላል” እያለ ይቀልዳል፡፡ ሲዘፈንለት የኖረውን የጦሣን ተራራም አየሁት፡፡ ደሴን ተጭኗታል፡፡
ከደሴ ልመለስ ነው፡፡ አሳዘነችኝ፡፡ ደግሞም አናደደችኝ፡፡ እንደጠበኳት አላየኋትም፡፡ እንደፈለኳት አላገኘኋትም፡፡ እንደናፈቅኳት አልጠገብኳትም፡፡ ግን አልጨከንኩባትም፡፡ “በሃገርና በሃገር ልጅ ማን ይጨክናል፡፡” እባካችሁ ደሴን ያያችሁ...
***
“የቦርከና ውሀ እባብ ያንሻልላል፤
ያንቺ ልብ እንዴት ነው የኔ ይዋልላል፡፡”
@amehamarie