ትንሽ ደግሞ ከቁም ነገር ያልተኛ ያላናቀላፋ እውነት እንማር።
አንድ ገበሬ ሊሸጠው የሚፈልገው በግ ስለነበረው ወደ ገበያ ወሰደው ይባላል። አራት ወንበዴዎች አይተውት በጎቹን በብልሃት ሊሰርቁት ተስማምተው ወደ ገበያ በሚወስደው መንገድ ጥግ ጥግ ያዙ። የበጎቹ ባለቤት ወደ ገበያ የሚያልፍበት መንገድ ላይ አንደኛው ሌባ ተቀምጧል። ሁለተኛው ከመጀመሪያው ሌባ ራቅ ብሎ ተቀምጧል። ሶስተኛው ከግማሽ እርቀት በኋላ ተቀመጠ። አራተኛው መንገዱ ከማለቁ ጥቂት እርምጃ የሚቀረው ቦታ ላይ ተቀመጠ። እናም የበጎቹ ባለቤት በመጀመሪያው ሌባ በኩል አለፍ ብሎ ሰላምታ ሰጠው። ሌባው ወደ ገበሬው ዘወር ብሎ እንዲህ አለው፦ “ውሻውን ለምን አሰርከው?”
ገበሬው “ይህ ውሻ ሳይሆን በግ ነው ወደ ገበያ ልሸጠው ነው”
ትንሽ እራቅ ካለ በኋላ ሁለተኛውን ሌባ አገኘውና እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ለምን ይህን ውሻ ከኋላ አስረ ትመራዋለህ?!”
ገበሬውም ሌባውን አይቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ በግ ነው ገበያ ልሸጠው ነው።” ነገር ግን ጥርጣሬ በልቡ ውስጥ ዘልቆ መግባት ስለጀመረ ከሁለቱ ሰዎች እንደ ሰማው ውሻ መሆኑን ለማረጋገጥ በጉን መመልከት ጀመረ። ከተወሰነ ርቀት በኋላ ሶስተኛውን ሌባ አገኘውና እንደ ቀድሞው ጥያቄ ጠየቀው፦ “ውሻውን ለምን ከኋላ አስርከው?”
የበጎቹ ባለቤት ግራ መጋባቱ በጣም እየጨመረ መጣ። ወደ ሌባው ዞር ብሎ ተመለከተ። ግን ለጥያቄው መልስ አልሰጠም ምክንያቱም ውሻ እንጂ በግ እንዳልሆነ ተገንዝቧል። ከተወሰነ እርቀት በኋላ አራተኛውን ሌባ አገኘውና ሰላምታ እየሰጠው የፈጠነ እንዲህ አለው፦ “ሰውዬ ውሻውን አስረ ከኋላህ እየመራህ የመትሄደው ምን ችግር ቢገጥምህ ነው!?” እዚህ ላይ የበጉ ባለቤት ውሻ እንጂ በግ እንዳልሆነ አረጋግጧል። ግን አራቱንም ውሸታም ናቸው ማለት ምክንያታዊ አይደለም። ከዚያም ወደ ሌባው ዘወር ብሎ እንዲህ አለው፦
“በችኮላ ይኼ ውሻ በግ ነው ብዬ አስሬው ወደ ገበያ ወስጄ ልሸጠው ነበር። እስከ አሁን ድረስ ውሻ እንደሆነ ግልጽ አልሆነልኝም። ሳስበው ዛሬ ልክ አይደለው መሰለኝ” አለና በጉን ፈትቶ ወደ ቤቱ በችኮላ በጉን ፍለጋ ወደ ቤት አቀና። በዚህም ሌቦቹ በጉን ይዘው በደስታና በጭፈራ ወደመጡበት ሄዱ!።
አስተምሮቱ፡-
በዚህ መልኩ ነው የህዝብ አስተያየት በጥቂት ባለስልጣኖች ይፈጠራል። እና የሚያታልሉትም በአለም አቀፍ ሚዲያዎች አማካኝነት ተጠቅመው ነው። ለዚህም የተቻለውን ሁሉ በማድረግ እውነታውን በማጭበርበር፣ በማጣመም፣ የቅዠት ትዕይንቶችን ፈጥረው በማሳሳት እና በማታለል በአእምሮ መጫወት ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም ሚድያዎች ውሸት እየመገቡን ውሸቱን እውነት ያደርጉታል። በአዕምሮ ይጫወታሉ አዕምሮአችንን ያስቱናል። አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ በጉ በአዕምሮአችን ውስጥ ሳይሆን በእውነታው አለም ነው። በዋቴ የተፈጠረ የህልም ውሻ መጨረሻው እኛን ቀረጣጥፎ መብላት ነው። ስለዚህ እምነታችንን፣ ባህላችንን እና እውቀታችንን በሌቦች እጅ መተው የለብንም በተለይም በአዕምሮ ሌቦች!።