Репост из: የሕይወት እምሻው ወጎች/ Hiwot Emishaw
‹‹የጥምቀት ወግ››
++++++
እንደ ጥምቀት የምወደው በዓል የለም፡፡
ነፍሴ ነው፡፡
ገና ጥር ከመግባቱ ያቁነጠንጠኛል፤ ደረሰ ደረሰ እያልኩ፡፡
ዋነኛው መንፈሳዊና ሐይማኖታዊ ፋይዳው እንዳለ ሆኖ ጥምቀት ለእኔ ህዝባዊ ፌስቲቫል፣ ገፋ ሲልም የካርኒቫል ቀለምና ስሜት ያለው ወደር የለሽ የአደባባይ ነጻ የህዝብ በዓል ነው፡፡
ጥምቀት ባለህብረ ቀለም የባህል አውደ ርእይ፣
የውበት አውድማ፣
ግዙፍ የህዝብ ቡፌ ነው፡፡
ልብ ላለው፤ ከከተራ ጀምሮ ያለው መንፈሳዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ህዝባዊና ባህላዊ ትእይንት ልብን ይሰውራል፡፡
እንኳንም ኢትዮጵያዊ ያደረገኝ ያሰኛል፡፡
በደስታ ያፍነከንካል፡፡፡፡
‹‹እነሆ ጥምቀት ደረሰ
ነጭ ነጩን እየለበሰ
ህዝቡ ወደ ባሕር ገሰገሰ
ታቦቱን እያነገሰ››
እየተባለለት መምጣቱ የሚበሰርለት የጥምቀት በዓል ለወንዱም ለሴቱም፣ በተለይ ደግሞ ለአፍላዎቹ የመታያ፣ የመዋቢያና፣ የመፍኪያ ወቅት ነው፡፡
ወንዶች ሌላ ጊዜ ችላ የሚሉትን በመፈተል ብዛት የተቆጣጠረ ፀጉራቸውን ብን አድርገው ያበጥራሉ፣ እንደ ኪሳቸው ውዱን ይለብሳሉ፡፡
ሴቶች ሹሩባቸው በዘመኑ ፋሽን ይቆነደዳሉ፤ የቻሉ ሂውማን ሄራቸውን ልቅም ተደርገው ይሰፋሉ፣ ታጥበውና ታጥነው፣ እንሾሽላ ሞቀው፣ ሳውና ባዝ ውለው፣ ተቀሽረውና አስደንጋጭ ውበታቸውን ይዘው እንደ ኪሳቸው ባማረው ቀሚስ ተውበው ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡
‹‹ይሄ ሁሉ ቆነጃጅት የት ተደብቆ ነው›› እስኪባል…
ቀይ ቢባል፣ ጠይም ቢባል፣ ጥቁር ቢባል…ውበት…ሃበሻዊ ውበት ሁሉም በየአይነቱ
… ከባለ ግቢ ትልቅ ብረት በር፣ ከቀበሌ ቤት ደጃፍ፣ ከየኮንዶሚኒየሙ ቤት ያለማቋረጥ ይፈሳል፡፡
ከብዛቱ የተነሳ ያፈዛል፣ ያደነዝዛል፡፡
እንደው ለመሆኑ ለጥምቀት የማያምርባት ሴት የትኛዋ ናት?
ከቤት ሰራተኛ እስከ የሃብታም ሚስት..
ከአጎጠጎጤ ኮረዳ እስከ ቀብራራ እመቤት..
ከቫዝሊን እስከ ውድ ሜክአፕ የተቀቡ ፊቶች እንደ ፀሃይ እያበሩ በጃንጥላ ተከልለው መንገዱን ሲያጥለቀልቁት ማየት እውነትም ጥምቀት የእኩልነት በአል ነው አያሰኝም?
በዓመት አንዴ የሚያገኙትን ብስኩት፣ ለስላሳና ሎሊፖፕ አከታትለውና ደራርበው የሚያላምጡና የሚጠጡ ከደሃና ባለጸጋ ማህጸን የወጡ ህጻናት በደስታ ሲቦርቁ ሰታይ ልብን ደስ አይልም?
ዶሮ ግዙልኝ፣ ሰንጋ እረዱልኝ፣ ዳቦ ድፉልኝ፣ ቶርታ ሸምቱልኝ ሳያስብል ሁሉንም እንዳቅሙ አስውቦና አስጊጦ በአደባባይ እኩል የሚያደርግ የሁሉም በዓል ነው ጥምቀት!
ታቦት አንግሶ ሲያበቃ፤
ለጥምቀት በዓል አደባባይ ወጥቶ ያልዘፈነ፣ ሆ ብሎ ያላስባለ ጎረምሳ፣
ግጥም ተቀብላ በስሜት ያልደገመች፣ ያላጨበጨበችና እስክስታ ያልወረደች ኮረዳ፣
በሃርሞኒካ ግጥምና ዜማው ስሜት የማይሰጥ ግን በስሜት የተሞላ ‹‹ሲሲ..ፓራራ›› ሙዚቃ ያልተናጠ ወጣት ምኑን ወጣት ሆነ?
ይሄ ሁሉ ሲሆን በክቡ ጥግ ቆመው ወጣቶቹን በግብረገብ ሚዛን ላይ የሚያስቀምጡ ተቆጪ አዛውንትና በአለፈብኝ ቁጭት የሚወዘወዙ ጎልማሶች ካልታዩበት ምኑን ጥምቀት ሆነ!
እንዲህ ያለውን ምስቅልቅል ግን ውብ ስእል እንካችሁ የሚል ሌላ በአል የለም፡፡
ጥምቀትን የሚመስል አንዳችም ነገር የለም፡፡
የሚገርመኝ ለወትሮው የሚያንገሸግሸኝ ጩኸትና ሁካታ፣ የድምፅ መጋጨትና መሳከር፣ የብዙ ነገር መደበላለቅ ለጥምቀት ሲሆን የሚጥመኝ ነገር ነው ፡፡ ጭራሽ ድምጽ ካልተማታብኝ፣ ነገር ካልተሳከረብኝ፣ ቀለም ካልተደባለቀብኝ ቅር ይለኛል፡፡
አለ አይደል…
እዚያ ማዶ ….
‹‹ነይ ነይ እምዬ ማርያም
ነይ ነይ ቤዛዊት ዓለም ››
ወይ ደግሞ
‹‹እጣን እጣን ይሸታል መሬቱ
አባቴ ገብርኤል ያደረበቱ ››
እያሉ በመዝሙር የህዝቡን ስሜት የሚገዙ ዘማሪዎችን ስሰማ…
ከወዲህ ደግሞ
››አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ
የአንገትሽ ንቅሳት ውበትሽን እያየ ››
እያሉ እየጨፈሩ ልጃገረዶችን የሚባብሉ ጎረምሶችን ዘፈን ስሰማ ደስ ይለኛል እንጂ አልረበሽም፡፡
ምድሪቱ ላይ ያለ ምግብን አንዱን ባንዱ ላይ እየደራረብኩ ስበላ አሁንም ደስ ይለኛል እንጂ አይጣላኝም፡፡
ጥምቀት ነዋ! ካልተደባለቀ ምኑን ጥምቀት ሆነው!
ስለዚህ ዛሬ በከተራ
ድብልቅልቅ፣ ሽብርቅ፣ ድምቅና ፍልቅልቅ ያለ የጥምቀት በዓል ስመኝላችሁ ከደስታ በቀር የሚሰማኝ አንዳችም ስሜት የለም፡፡