የገጠር ትልቅ ድስት ይባላል ሰታቴ!
(በእውቀቱ ስዩም)
ያኔ የዩንቨርስቲ ተማሪ እያለን አንድ ክልስ ጓደኛ ነበረን፤ ቶማስ ይባላል፤ አባቱ ጣልያን ሲሆን እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ናት፤ ጠጉሩ የበቆሎ እሸት መነሳነስ ይመስላል፤ በክልስነቱ የሚሰነዘርበት አሉታዊ አስተያየት ምቾት አይሰጠውም ነበር፤አንድ ቀን፥ የአድዋ በአልን ለማክበር በተዘጋጀ ተውኔት ላይ እንደ ጀኔራል ባልዴሴራ ሆኖ እንዲጫወት ሲጠየቅ በጣም ተናደደ “ ሲጀመር የምታስቡትን ያክል ፈረንጅ አልመስልም! ብመስል እንኳ፥ ያንን በስባሳ ጄኔራል ሆኘ አልጫወትም! ከፈለጋችሁ ያጤ ምኒልክ አማካሪ የነበረውን ስዊዘርላንዳዊ ኢልግን ሆኘ መተወን እችላለሁ” ብሎ መለሰ:
:
ተውኔቱን የጻፈው እና ምኒልክን እና ባልቻን ደርቦ የሚጫወተው ተኮላ ግን ገገመ፤
“ እሺ ጄኔራል ባልዴሴራን ሆኖ መተወን ከደበረህ የጣልያኑን ንጉስ ኡምበርቶን ሆነህ ተጫወትልን ”
ቶማስ ንዴቱን መቆጣጠር አልቻለም ፤
“ እናትህን ንጉስ ኡምበርቶ ይርዳልህ! ሲጀመር አንተ የኡጋንዳውን ፕሬዚዳንት ኢዲ አሚንን ዳዳን እንጂ ምኒልክን አትመስልም! እኔ ንጉስ ኡምበርቶን ሆኘ የምተውነው አንተ የንጉሱን ዙፋን ሆነህ ከተጫወትክ ነው” በማለት አንባረቀ ፤
ቶማስ ብዙ ጊዜ ከጣልያን ጋር ግኑኝነት ያላቸውን ቃሎችን ላለመጠቀም ይጠነቀቃል፤ ለምሳሌ ማኪያቶ ላለማለት፥ ካፌ ገብቶ “እስቲ የቡና እና የወተት ብርዝ አምጡልኝ “ ብሎ ያዝዛል፤ “ጓንት” የሚለውን ቃል አይጠቀምም፤ “የእጅ ፓንት “ የሚለውን ቃል ይመርጣል፤
በግጥም ምሽት ላይ የሚያቀርባቸው ግጥሞች ባብዛኛው ለኢትዮጵያዊነቱ አጽንኦት የሚሰጡ ነበሩ፤
‘የገጠር ትልቅ ድስት ይባላል “ሰታቴ”
ጥርጥር የለኝም በኢትዮጵያዊነቴ”
የሚለው ስንኙ አይረሳኝም፤
የሆነ ጊዜ ላይ ሰይጣን ልጁን ሲድር ፥ ለሰርጉ ድምቀት ግቢያችን ውስጥ የብሄር ግጭት አስነሳ! የተወሰኑ ተማሪዎች በሁለት ብሄሮች ተቧድነው መሸካሸክ ጀመሩ፤ የዚህች ወግ ጸሀፊን ጨምሮ ብዙ ተማሪዎች ዶርማቸውን ቆልፈው መሸጉ፤ አመሻሽ ላይ ቶማስ ግጭቱ በርዷል ብሎ በመገት ወደ ካፌ እየተራመደ እያለ ፌሮና ድንጋይ የታጠቁ ጥቂት ተማሪዎች ወደሱ ሲሮጡ ተመለከተ፤ ባልበላ ጉልበቱ ትንሽ እንደሮጠ ስቴድየሙ አካባቢ ደረሱበት፤
ቶማስ እጁን ወገቡ ላይ አድርጎ ባጭር ባጭሩ እየተነፈሰ እንዲህ አለ፤
“ ወንድሞቼ ! እኔ ብሄር የለኝም ! እልል ያልሁ ጣልያን ነኝ ! እኔን በመደብደብ ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ህብረት ጋር ደም እንዳታቃቧት"
@Samuelalemuu