❤ "በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ኅዳር ፲፬ (14) ቀን።
❤ እንኳን #ለአገረ_ጠራክያ_ኤጲስ_ቆጶስ ለቅዱስ አባት #ለአባ_መርትያኖስ_ለዕረፍት_በዓል፣ ለፋርስ ንጉሥ ተአምራት ላደረገና ክቡር ይግባንና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላሳመነ #ለአባ_ዳንኤል_ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱሳን #ሱራስጦስ_ከእንድራዎስ_ከመብራኖስ_ከራጢስና #ከይስጥ_ከጋርሴስ_ከበጥላንና ከመታሰቢያቸው #በደብረ_ቀልሞን ከተሠራች ቤተ ክስትያን ከከበረችበት ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #የአገረ_ጠራክያ_ኤጲስ_ቆጶስ_አባ_መርትያኖስ፦ ይህ ቅዱስ ሶርያ ከምትባል አገር ነው ወላጆቹም ክርስቲያን ናቸው እርሱም በገድል የተጠመደ ተጋዳይ ነው። አርዮሳውያንንም የሚቃወማቸው ከሀድያን የሚላቸው አውግዞም የሚያሳድዳቸው ሆነ። ስለዚህም በእርሱ ላይ ታላቅ መከራ ደረሰበት። በሚያልፍባትም ጎዳና ጠብቀው ይይዙታል አብዝተውም ገርፈው እግሩን ይዘው በሜዳ ውስጥ ይጎትቱታል እንዲህም ብዙ ጊዜ አደረጉበት።
❤ ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው ሸሽቶ ወደ ሩቅ አገር ተጒዞ ከኤርትራ ባሕር ዳር ደረሰ ከምድር የሚበቅሉ ቅጠሎችን እየተመገበ በዚያ ዋሻ ውስጥ ብዙ ዓመታትን ኖረ። ኤጲስቆጶስም ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መረጠው እነሆ የተጋድሎውና የትሩፋቱ ዜና በተሰማ ጊዜ ከዚያ ወስደው ጠራክያ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት እንደ ሐዋርያት ሥርዓት በሹመቱ በጎ አካሔድን ተጓዘ በዘመኑም በብዙዎች ላይ ሰላም ፍቅር ቸርነት ሆነ።
❤ እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ተአምራትን አደረገ በጐዳናም አልፎ ሲሔድ የሞተ ሰው አየ ሌላም ዓመፀኛ ልቡ የደነደነ በሐሰት "ከእርሱ ላይ አራት መቶ የወርቅ ዲናር አለኝ ያንን ካልሰጠኝ አላስቀብርም" ብሎ ዘመዶቹን ሲከለክል ነበር። ይህም ቅዱስ "የሞተውን ይቅበሩት ተዋቸው" ብሎ ብዙ ለመነው እርሱ ግን አልሰማውም። በዚያንም ጊዜ ይህ ቅዱስ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየ ማለደ ያን ጊዜ የሞተው ሰው ተነሥቶ ምንም ምን ዕዳ እንደሌለበት ተናገረ።
❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርትያኖስ ያንን ዓመፀኛ በሰፊት እንዲህ አለው "ለምን በሐሰት ተናገርክ የተሠወረውን የሚያውቅ እግዚአብሔርን አትፈራውምን" በዚያንም ጊዜ ያ ዓመፀኛ ሞተ ከሞት የተነሣው ግን በሰላም ወደ ቤቱ ገባ።
❤ ከዚም በኋላ ይህ ቅዱስ መርትያኖስ ብዙ ዘመናትን ኖረ መልካም አገልግሎትንም ፈጽሞ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ ኅዳር 14 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ መርትያኖስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ዳንኤል፦ ይህም አባት ለፋርስ ንጉሥ ተአምራት ያደረገና ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳመነው ነው። የእምነቱም ምክንያት እንዲህ ነው ይህ ንጉሥ ጽኑዕ የሆነ የሆድ በሽታ ታሞ ነበር ባለ መድኃኒቶችም ሊአድኑት አልቻሉም ንጉሡም ከማዕዱ የሚመግበው አብሮት የሚኖር ሥራየኛ ሰው ነበርው ንጉሡም እንዲህ አለው "ያንተ ከእኔ ጋር መኖር ጥቅሙ ምንድን ነው ከዚህ በሽታ ካልፈወስከኝ እገድልሃለሁ"። ሥራየኛውም ንጉሡን በተንኰል እንዲህ ብሎ ተናገረው "ንጉሥ ሆይ የምነግርህን ካደረግህ ከደዌህ ትድናለህ። አሁንም ለአባትና እናቱ አንድ ብቻ የሆነ ልጅ ይፈልጉልህ እናቱ አሥራ ትያዘው አባቱም ይረደው በእርሱም ደም ትድናለህ" መሠርዩ ይህን ማለቱ ግን እንዲህ ያለ ሥራ መሥራትን ንጉሥ ይፈራል ወይም ልጁን የሚሰጥ አይገኝ ብሎ አስቦ ነው።
❤ ንጉሥም በሚገዛው አገር ውስጥ ፈልገው በአንድ ሺህ የወርቅ ዲናር ሕፃን ልጅ ይገዙለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ። በዚያችም አገር አንድ ልጅ ያላቸው ድኆች የሆኑ ባልና ሚስት ነበሩ እነርሱ ይህን ነገር ሲሰሙ ልጃቸውን ወደ ንጉሥ ወሰዱ ልጁም በማልቀስ "እኔ በፈጠረኝ እግዚአብሔር ላይ ተማምኛለሁና እርሱም ያድነኛል" ይል ነበረ። እናቱም አጥብቃ አሠረችው አባቱም ሊያርደው በንጉሡ ፊት ሾተሉን መዘዘ በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ አይኖቹን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ ወደ እግዚአብሔር በልቡ ሲጸልይ ከንፈሮቹን አንቀሳቀሰ እግዚአብሔርም በንጉሡ ልብ ርኅራኄን አሳደረ ፈትታችሁ ልቀቁት ብሎ አዘዘ ወደርሱም አቅርቦ "ዐይኖችህን ወደ ሰማይ በአቀናህ ጊዜ ምን አልክ" አለው "ጌታዬ ሆይ ልጅን የሚገፋው ቢኖር አባቱና እናቱ ያድኑታል ከዚያም የጸና ሥራ ቢኖር ንጉሥ ዳኛ ያድነዋል እኔ ግን ከሁላችሁም ርዳታ በአጣሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ለመንኩ" አለው። ንጉሡም ሰምቶ ራራለት አንድ ሽህ የወርቅ ዲናርንም ሰጠው።
❤ ስለዚህም እግዚአብሔር ይቅር ልለው ወዶ መነኰስ አባ ዳንኤልን ላከለት እርሱም ወደ ንጉሡ በደረሰ ጊዜ በፊቱ ተአምራትን አደርጎ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳመነው ከበሽታውም ፈወሰው ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋርም አጠመቀው ከዚህም በኋላ ወደ በዓቱ ተመልሶ እየተጋደለ ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ኅዳር 14 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የአባ ዳንኤል በረከቱም ትድረስን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 14 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለመርትያኖስ_ምሉአ_ጸጋ_ወሀብት። ከመ ይስብክ ሃይማኖተ በመጣርያ አንተ ተውህበቶ ሢመት። እምአርሳውያን ሕዝብ ሶበ ረኮቦ ስደት። ኀበ ሖረ ወፈለሰ ውስተ ምድር ርኅቅት። በኃይለ ጸሎቱ ተንሥአ ምውት"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር_14።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ አቡየ ወእምየ ገደፉኒ። ወእግዚአብሔር ተወክፈኒ። ምርሐኒ እግዚኦ ፍኖተከ"። መዝ26፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 15፥12-24፣ 1ኛ ጴጥ 5፥6-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 23፥6-10። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 4፥46-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ዮሐንስና የአቡነ ቄርሎስ ዘሽሬ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
@sigewe https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKwL https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886