Addis Admass


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha


የአዲስ አድማስ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ
=====
አዲስ አድማስ https://bit.ly/2V1zyZQ
ፌስቡክ↠ https://bit.ly/2V0I6jx
ትዊተር↠ https://bit.ly/33fDhaP
ቴሌግራም↠ https://bit.ly/2JgeCvG
ዩቲዩብ ↠ https://bit.ly/3q2hXiv
የእርስዎና የቤተሰብዎ

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Statistika
Postlar filtri


የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እስካሁን የ19 ሰዎችን አስከሬን ከወንዙ ማውጣታቸውን ገልፀዋል። 300 ገደማ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋ በደረሰበት ሥፍራ አሰሳ በማካሄድ ላይ ናቸው።

በአካባቢው ባለው ከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት የአደጋ ጊዜ ሥራው እጅግ አስቸጋሪ እንደሆ ተነግሯል። በአውሮፕላኑ ተሳፋሪ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ሁለት ሩሲያዊያን 'የስኬቲንግ' ስፖርተኞች እንደሚገኙበት ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ፖሊስ እና ጠላቂዎች በጀልባ ታግዘው ወንዝ ውስጥ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች መኖራቸውን ለማጣራት አሰሳ እያካሄዱ ሲሆን የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአደጋውን መንስዔ እየመረመሩ ይገኛሉ።

የፌዴራል አቪየሽን ባለሥልጣን እንዳለው አደጋው የተከሰተው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3፡00 ገደማ ሲሆን አውሮፕላኑ ሬገን ዋሺንግተን የሀገር ውስጥ አየር ማረፊያ ለማረፍ እየተቃረበ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለአደጋው ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ገልፀው "መጥፎ አደጋ" ሲሉ ገልፀውታል።

የበረራ ቁጥሩ ፒኤስኤ ኤርላይንስ 5342 የሆነው ቦምባርዲዬር አውሮፕላን የአሜሪካ ጦር ንብረት ከሆነው ብላክ ሆክ ጋር መጋጨቱን አንድ ወታደራዊ ባለሥልጣን አረጋግጠዋል።

በቅርቡ የተሾሙት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴዝ በሰጡት መግለጫ ፔንታገን ሁኔታውን "በተጠንቀቅ እየተከታተለ ነው" ብለዋል።

የአሜሪካ መገናኝ ብዙኃን እንደዘገቡት የአሜሪካን ኤርላይንስ ንብረት የሆነው አውሮፕላን በአደጋው ምክንያተ ለሁለት የተከፈለ ሲሆን ሄሊኮፕተሩ ደግሞ ተገልብጦ ወንዝ ላይ ተገኝቷል።

እስካሁን በአደጋው ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በግልፅ ባይታወቅም የ19 ሰዎች አስከሬን ከወንዝ ወጥቷል። ነገር ግን በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞችን አደጋው አየር ላይ ሲከሰት "ደማቅ ብርሀን" ማየታቸውን ኤንቢሲ ለተባለው ጣቢያ ተናግረዋል።

ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ በአደጋው ምክንያት በረራ ማስተናገድ ያቆመ ሲሆን አውሮፕላኖች በአቅራቢያ ወደሚገኘው ዳለስ አየር መንገድ እንዲያቀኑ ተደርገዋል


በዋሺንግተን ዲሲ 60 ሰዎች የጫነ አውሮፕላን አየር ላይ ከጦር ሄሊኮፕተር ጋር ተጋጨ

አሜሪካን ኤርላይንስ የተሰኘው አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ ከሄሊኮፕተር ጋር መጋጨቱን የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር አስታወቀ።

አውሮፕላኑ 60 መንገደኞች እና አራት የበረራ ሠራተኞች ጭኖ እንደነበር የታወቀ ሲሆን ሄሊኮፕተሩ ደግሞ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን ጭኖ እንደነበር ተነግሯል።

የአውሮፕላን አደጋው የደረሰው ፖቶማክ የተባለ ወንዝ አቅራቢያ መሆኑን የዲሲ እሳት አደጋ መሥሪያ ቤት ገልጿል።


አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ 248 ሚ. ዶላር ብድር አጸደቀ

ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ ሁለተኛውን የኢትዮጵያ የተራዘመ ብድር ግምገማ በማጠናቀቅ፣ ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ፣ ትናንት ተጨማሪ 248 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁ ተነገረ፡፡

ድርጅቱ ለኢትዮጵያ 3. 4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ባለፈው ሐምሌ ያጸደቀ ሲሆን፤ ከዚያ ወዲህ እስከ ትናንት ድረስ የለቀቀው ብድር 1.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ታውቋል፡፡ መንግሥት ለማኅበራዊ ሴፍቲ ኔት መርሃ ግብሮች የሚሰጠው ድጎማ ከተጠበቀው በታች መሆኑን የገመገመው ድርጅቱ፤ ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሴፍቲ ኔት ድጋፎችን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ መክሯል።

ድርጅቱ፣ የነዳጅ ዋጋ የመንግሥትን ወጪ ሙሉ በሙሉ ሊመልስ በሚችል ደረጃ መስተካከል እንዳለበትም ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል፡፡


“ኢትዮጵያ ተራማጅ ሀገር ናት”


አዲስ አበባ በአስደናቂ የለውጥ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ መመልከታቸውን የሩዋንዳ ፓትሪዮቲክ ፍሮንት (አር ፒ ኤፍ) ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ዌላርስ ጋሳማጌራ ገለጹ።

በነገው ዕለት አርብ በሚጀመረው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመታደም በመዲናዋ የሚገኙት ዌላርስ ጋሳማጌራ፤ የአንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም አዲስ አበባ በለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን በአድናቆት የገለጹት ዋና ጸሃፊው፤ ኢትዮጵያ ተራማጅ ሀገር ናት ብለዋል።

የአንድነት ፓርክ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሀገርነት የሚገልጥ ብቻ ሳይሆን፣ ያለፈን ታሪክ ከዛሬ ጋር አስተሳስሮ በትንሽ ቦታ የሚያሳይ ድንቅ ስፍራ መሆኑንም ጋሳማጌራ ጠቁመዋል፡፡


የአዲስ አድማስ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ
=====
አዲስ አድማስ https://bit.ly/2V1zyZQ
ፌስቡክ↠ https://bit.ly/2V0I6jx
ትዊተር↠ https://bit.ly/33fDhaP
ቴሌግራም↠ https://bit.ly/2JgeCvG
ዩቲዩብ ↠ https://bit.ly/3q2hXiv


በዚህ ረገድም እስካሁን ድረስ ከ60 በላይ ለሆኑ የልብ ህሙማን ሕፃናትና አዋቂዎች ያለክፍያ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል።

የህንድ ኦርቶዶክስ የፓትያርኩ ተወካይ በጉብኝቱ ወቅት ባዩት ሁሉ መደሰታቸውን ገልፀው፤ ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር መሥራት የእነሱም ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።

በአገራቸው ህንድ አራት ሆስፒታሎች ላይ በቦርድ አባልነትና ሊቀመንበርነት እንደሚያገለግሉ የገለጹት ተወካዩ፤ ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታል ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብሮ የሚሰራበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ጠቁመዋል፡፡ እዚህ የማይሰጡ ህክምናዎችን እሳቸው ከሚያስተባብሯቸው ሆስፒታሎች ጋር አብሮ እንዲሰራ በማድረግ፣ ድጋፍ እንዲያገኝ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ነው ቃል የገቡት፡፡


የህንድ የልዑካን ቡድን ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታልን ጎበኘ

• ሆስፒታሉ ከህንድ ሆስፒታሎች ጋር በትብብር ሊሰራ ነው

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቴዎስ ሣልሳዊ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መልዕክተኛ፣ የልዑካን ቡድን፣ ሜትሮ ፖሊታን ማር ዩልዮስና ፋዘር ጆሲ ጃኮብ በዛሬው ዕለት ጠዋት ረፋድ ላይ የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃን ተድላ በጉብኝቱ መርሐ ግብር ወቅት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ከህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር መቀራረቡ በተለይ ከፍተኛ ህክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለማድረግ ሆስፒታሉ ያለውን ራዕይ ለማሳካት የሚረዳ ነው።

የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል፤በቴክኖሎጂ በታገዙ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችና ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ስፔሻሊስትና ሰብ-ስፔሻሊስት ባለሙያዎች በመታገዝ፣ ዜጎቻችንን ለህክምና ወደ ውጭ አገር በመጓዝ የሚያወጡትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና እንግልት ለማስቀረት እንዲሁም ወደ ውጭ አገር የሚያስኬዱ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለመስጠት አልሞ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በዋናነትም ሆስፒታሉ በአዋቂና በህፃናት የልብ ቀዶ ህክምና ላይ የተሰማራ የሕክምና ተቋም ስለመኾኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል። በተጨማሪም፣ የደረትና የሳንባ ቀዶ ጥገና ሕክምና፥ የጭንቅላትና ህብለሰረሰር ህክምና፥ የነርቭ ህክምና፥ የኩላሊት እጥበትና ህክምና፥ የአጥንት ቀዶ ሕክምና እና ጠቅላላ ህክምና ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለልብ ሕሙማን ህፃናት ያለ ክፍያ የቀዶ ህክምና በመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ብርሃን ገልፀዋል።


በደቡብ ሱዳን በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ የሟቾች ቁጥር 20 መድረሱን ፕሬዚዳንቱ አስታወቁ

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በሰጡት መግለጫ "ይህ ልብ የሚነካ ክስተት የ 20 ንፁሃን ሰዎች ሕይወትን ቀጥፏል፣ አንድ ሰው ተርፏል" ብለዋል።

ረቡዕ ዕለት 21 ተሳፋሪዎችን ያሳፈረ አውሮፕላን በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ከሚገኘው የአንድነት የነዳጅ ማደያ ሲነሳ የመከስከስ አደጋ አጋጥሞታል።

ፕሬዝዳንቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ሁሉም የሚመለከታቸው ባለስልጣናት የአደጋውን መንስኤ ለመለየት ጥልቅ እና ፈጣን ምርመራ እንዲያካሂዱ መመሪያ መስጠታቸውን መግለጫው አመልክቷል።


ሆኖም ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸው ተጠቅሷል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን በሙሉ ድምጽ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠባቸው ሲሆን፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ ጥፋተኛ ተብለዋል።
የሀሳብ ልዩነት ያቀረቡት አንደኛው ዳኛ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት የባንክ ሂሳባቸው በመገለጹ ብቻ የወንጀል ተግባሩ በስምምነት ተፈጽሟል ለማለት አያስችልም የሚል የሀሳብ ልዩነት እንዳላቸው ጠቅሰው ልዩነታቸውን አሳይተዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉ የተፈጸመው በትብብር መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ ይዟል።
በዚህም1ኛ ተከሳሽ ቀሲስ በላይ መኮንን ያቀረቡትን አራት የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በዕርከን 21 መሰረት በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ እያንዳንዳቸው አራት፣ አራት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በዕርከን 17 መሰረት በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የተወሰነውን የጽኑ እስራት ውሳኔን የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እጃቸው ከተያዘ ጀምሮ ታሳቢ በማድረግ እንዲያስፈጽም ታዟል።


ቀሲስ በላይ መኮንን በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጡ
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ የቀረቡ የግራ ቀኝ ማስረጃዎችን መርምሮ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰነ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ቀሲስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ፣ በኮሚሽን ስራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ እና አለምገና ሳሙኤል እንዲሁም የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ በተባሉ ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ እና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር 382 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህም ተከሳሾቹ ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ተከሳሾች በተለያየ መጠን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት ለባንኩ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
በዚህ መልኩ የቀረበውን ዝርዝር ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ብቻ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ የሚጣራ መሆኑን ገልጾ መቃወሚያቸውን አልተቀበለውም።
ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ አጠቃላይ ሶስት ምስክሮችን አቅርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር።
ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል መርምሮ በክሱ ዝርዝር የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ማረጋገጡን ጠቅሶ በአንደኛው ክስ ብቻ እንዲከላከሉ በሙሉ ድምጽ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ሁለተኛውን ክስ በሚመለከት በሐሰተኛ ሰነድ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑ በአንደኛውን ክስ ላይ መገለጹን ተከትሎ በሰበር ሰሚ ችሎት ትርጉም የተሰጠባቸው በተደራራቢነት የቀረቡና ተጠቃልለው ሊያስቀጡ የሚችሉ ድንጋጌዎች መኖራቸውን ፍርድ ቤቱ አብራርቶ ሁለተኛውን ክስ ውድቅ በማድረግ በአንደኛው ክስ ብቻ በከባድ አታላይነት ሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።




ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ነው

በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በዝግጅት ላይ ነው



ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ አጠቃላይ ሆስፒታሉን የመቶኛ ዓመት ምስረታ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ማክበር ጀምሯል። ባለፈው ረቡዕ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በተገኙበት በይፋ የተከፈተው ክብረ በዓል፤ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።
በ1942 ዓ.ም ኢትዮጵያ የጤና ሰራተኞች እንደሚያስፈልጋትና የጤና አጠባበቅ ትምህርት የሚቀስሙበት ማሰልጠኛ ተቋም እንዲከፈት የዓለም የጤና ድርጅት ማሳሰቡን ተከትሎ ነው የጎንደር ጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ የተቋቋመው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን የጤና ባለሙያዎች ስላልነበሩ ወጣቶች እየተመረጡ ውጪ ሐገር እንዲሰለጥኑና የጤና አጠባበቅ ሰራተኞች በሃገር ውስጥ የሚሰለጥኑበት ተቋም እንዲመሰረት የተወሰነ ሲሆን፤ መስከረም 24 ቀን በ1947 ዓ.ም የጎንደር ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ ከሐሳብ ወደተግባር መቀየሩን የዩኒቨርሲቲው ታሪክ ይጠቁማል፡፡
ምስረታው እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የዓለም የጤና ድርጅትና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት የተባበሩ ሲሆን፤ በወቅቱ “የጎንደር ጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ” በሚል ስያሜ መቋቋሙ ተገልጿል። በዚሁ የምስረታው ዓመት በአገር ግዛት ሚኒስቴር ስር አንድ ዘርፍ ይዞ የነበረው የህዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመባል ከፍ ባለ ደረጃ እንዲመራ በነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 91 መታወጁን የሚያትተው የዩኒቨርሲቲው ታሪክ፤ በ1948 ዓ.ም ደግሞ በሐገሪቱ የሚካሄደው ማንኛውም የጤና ትምህርት በሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር በመታዘዙ፣ ይህ የማሰልጠኛ ተቋምም በሚኒስቴሩ አመራር ስር እንዲውል መደረጉ ተመልክቷል። ማሰልጠን ከመጀመሩ በፊትም፣ የጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ የሚል ስያሜውን በ1947 ዓ.ም ስራውን ሲጀምር፣ የጎንደር ህዝብ ጤና ጥበቃ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ወደሚል ቀየረ። ከዚህ በኋላ ብዙ ሂደቶችን ያለፈው ኮሌጁ፤ ከጤና ዘርፍ ውጪ በርካታ የትምህርት ዘርፎችን አካትቶ፣ በ1996 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደሚል ስያሜ መሸጋገሩን ፕሬዚዳንቱ አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) አብራርተዋል።
ተጨማሪ ያንብቡ

https://t.ly/t7qnz


እኔ ወይስ ሌላኛው እኔ?

በአብርሀም ገነት

ይሄ ገጠመኝ መቼቱ አይታወቅም፡፡ ገጠመኙ የሆነ የተፈፀመ ነው፣ የት እና መቼ እንደተፈፀመ ግን አይታወቅም፡፡ ታሪኩ ተራ የሚመስል ገጠመኝ ነው፣ በልቦናዬ የፈጠረው ጥልቀት ግን መለኪያ የለውም፡፡ ታሪኩ አጭር ነው፣ የታሪኩን ዳና ግን ሁለንታውን በጠቅላላ ባስስ እንኳን የምደርስበት አይመስለኝም፡፡ ቀን ላይ የተፈጠረ ገጠመኝ እንደሆነ ግን አውቃለሁ፣ ምክንያቱም የልጅቷን ብሩህ ፈገግታ አይቼዋለሁ፡፡
እንዲህ ነበር….
ሱሪዬን አውርጄ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተቀምጫለሁ፡፡ የመፀዳዳት ተግባር እርካታ እንደሚሰጥ ሁላችንም እናውቃለን፤ እናም በዚህ እርካታ ታጅቤ፣ በሌላ ሀሳብ ውስጥ ሰምጬ የት እንደተቀመጥኩ እንኳን ረስቻለሁ፡፡ የት እንዳለሁ ብቻ ሳይሆን ምን እያደረግሁ እንደነበረም ረስቻለሁ፡፡ ጨርሼ ልታጠብ እጄ በልማዱ መሰረት ውሃ ፍለጋ ሲያማትር፣ ልቦናዬ ወደ ተጨባጭ ከባቢዬ ተመለሰ፡፡ ከተወሰድኩበት የሀሳብ አለም ስመለስ የት እንዳለሁ አወቅሁ፣ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ተቀምጬ ነው ያለሁት፡፡ ቀና ስል መፀዳጃ ቤቱ ክፍት ነው፡፡ በሩን ወርውሬ ለመዝጋት በተቀመጥኩበት ስንጠራራ መፀዳጃ ቤቱ በር የለውም፡፡ ደንግጬ ሰው ሳያየኝ ቶሎ ከጉልበቴ በታች ያለ የውስጥ ሱሪዬንና ሱሪዬን እየታጠቅሁ ልቆም ስል ሱሪ የለኝም፡፡ እየተጣደፍሁ ሀፍረቴን በውስጥ ሱሪዬ ልሸፍን እጄን ስሰድ የውስጥ ሱሪም የለኝም፡፡ ፊት ለፊቴ ሳይ ወደ መፀዳጃ ቤቱ ልትገባ ወረፋ ስትጠብቅ የነበረች ልጅ ቆማ እያየችኝ ነው፡፡ ደነገጥኩ፡፡ አፈርኩ፡፡ በደመነፍስ እጆቼን ጭኖቼ መሀል አደረኩ፡፡ ልጅቷ ቅንነት ከተሞላበት የሚያፅናና ፈገግታ ጋር “አይዞህ ፓንት የለኝም ብለህ አትፈር፣ እንትን የሌለው አለና” አለቺኝ፡፡ ከዚያ “ቆይ ፎጣ ላምጣልህ” ብላ ወደ ቤቷ ፈጠነች፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ
https://t.ly/7i4qf


የኢትዮጵያ ኢስላማዊ ምሁራን የአንድነት ጥሪ
ከተሾመ ብርሃኑ ከማል

ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ እና ወሳኝ ቦታ አላት። ከመካ ስደት ለሚሸሹ የጥንት ሙስሊሞች የመጀመሪያ መሸሸጊያ ቦታ በመባል የምትታወቀው ሀገሪቱ፣ ከእምነቱ አመጣጥ ጋር የተሳሰረ ነው። እ.ኤ.አ በ615፣ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሕይወት ዘመን፣ አንዳንድ የቅርብ ጓደኞቻቸውን ጨምሮ የጥንት ሙስሊሞች ቡድን በአቢሲኒያ (በዛሬይቱ ኢትዮጵያ) መሰደድን ፈለጉ። ክርስቲያኑ ንጉሠ ነገሥት (አስሐማ ኢብኑ አብጀር) አቀባበልና ጥበቃ አደረገላቸው፡፡ በእምነታቸውና በጋራ የፍትህ እና የሰላም እሴት መሰረት ጥገኝነት ሰጣቸው። ይህ ክስተት በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የሂጅራ (የስደት) ጉዞን ያስመዘገበ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ እና በሙስሊሙ ዓለም መካከል ዘላቂ ትስስር ፈጥሯል።
ዛሬ ኢትዮጵያ 50 ሚሊዮን የሚገመቱ እስልምና እምነት የሚከተሉ አማኞች ካሏቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ ናት። እስልምና ለዘመናት የሀገሪቷ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ መዋቅር ዋነኛ አካል ሲሆን፤ ለብዝሀነቷና ለቅርሶቿ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል። ይህ ታሪካዊ ፋይዳ እና የሙስሊም ህዝቦቿ መብዛት እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ምሁራዊ አስተዋፅዖ ካለው እምቅ አቅም እና በጣም ትንሽ ህዝብ ባለባቸው ሀገራት ካስመዘገቡት የእስልምና ምሁር ውጤቶች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው።

ይህም ሆኖ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የሙስሊም ምሁራን ቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዋቂ ግለሰቦች ቢኖሩ ከነሱም ውስጥ የህግ አስተያየት የሚሰጡ ሙፍቲዎች እና ከፍተኛ የእስልምና ሊቃውንት የሚባሉት ከአስር ቤት የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ከነዚህ ምሁራን መካከል ኢስላማዊ መጽሕፍትን ያሳተሙት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ሲሆኑ፤ ከአስር የማይበልጡ ደራሲያን ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ሥራዎችን እንደሠሩ ይገመታል። እስካሁን ድረስ አንድም ኢትዮጵያዊ የእስልምና ምሁር ከ100 በላይ መጻሕፍት እንደፃፈ አይታወቅም፡፡ በትርጉም ሥራም ቢሆን ብዙ ሠርተዋል የሚባሉት ምሁራን ከአንድ ቤት የሚዘሉ አይደሉም፡፡

ይህ ንፅፅር ከ10 ሚሊዮን ያነሱ ሙስሊሞች ካላቸው ሀገራት ጋር ሲወዳደር የበለጠ ጎልቶ ይታያል። በእንደዚህ ያሉ ሃገራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሁራን እና የሃይማኖት መሪዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን በመጻፍ እና የነቃ ምሁራዊ ስነ-ምህዳርን በመቅረጽ ለኢስላማዊ ስነ-ጽሁፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
ለምሳሌ፣ አገሪቱ ጥቂት መቶ ያህል እውቅና ያላቸው የሙስሊም ምሁራን ያሏት ሲሆን የሙፍቲዎች ብዛት- ማለትም የህግ አስተያየት እንዲሰጡ የሚፈቀድላቸው ከፍተኛ የእስልምና ሊቃውንት- በአንድ ቤት የሚቆጠሩ ናቸው። ችግሩን ከኢስላማዊ ስነጽሑፍ አኳያ ስንመለከተው ልዩነቱ አስደንጋጭ ነው። ካሉት ከፍተኛ ምሁራን መካከል፣ በአስር ቤት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ምሁራን ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ኢስላማዊ መጻሕፍትን ጽፈው ይሆናል። እስካሁን ድረስ፣ ከ100 በላይ የራሱ የሆኑ ሥራዎችን ያሳተመ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ምሁር ስለመኖሩ አይታወቅም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

https://t.ly/5PU9W




ማይክሮሶፍት ቲክቶክን ሊገዛ እየተደራደረ ነው ተባለ


• ሌሎች የአሜሪካ ኩባንያዎችም ፍላጎት አሳይተዋል


የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ማይክሮሶፍት ኩባንያ፣ ቲክቶክን ለመግዛት በውይይት ላይ መሆኑንና በማህበራዊ ሚዲያው ሽያጭ ላይ የሚደረጉ ፉክክሮችን ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

ግዙፉ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት፣ ለጨረታ ዝግጁ ስለመሆኑ የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፤ “አዎን” በሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በርካታ ኩባንያዎችም ቲክቶክን ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ትራምፕም ሆኑ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከብሔራዊ ደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ የቻይናው ኩባንያ ቲክቶክ እንዲሸጥ ለዓመታት ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

በአሜሪካ 170 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ መተግበሪያ እንዲታገድ ባለፈው ሳምንት የባይደን አስተዳደር ያሳለፈውን ውሳኔ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለ75 ቀናት እንዲራዘም ማዘዛቸው ይታወቃል፡፡


“ሺ ጊዜ እንዳፈቅር” የግጥም መድበል አርብ ይመረቃል

በገጣሚት መሠረት አዛገ “ሺ ጊዜ እንዳፈቅር” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የግጥም መድበል፣ ከነገ ወዲያ አርብ 4 ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት፣ አንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የሥነጽሑፍ ቤተሰቦች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡

በምረቃው ሥነስርዓት ላይ ጸሐፌ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ፣ ጸሐፌ ተውኔትና ገጣሚ ሥዩም ተፈራ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ፣ ደራሲና መምህር ኃ/መለኮት መዋዕል፣ መምህር የሻው ተሰማ (የኮተቤው) እና ወጣት ገጣሚያን ሥራቸውን ያቀርባሉ፡፡

ገጣሚ መሠረት አዛገ፣ የ”መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅት” መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ስትሆን፣ ላለፉት 14 ዓመታት በህጻናትና በእናቶች ድጋፍና እገዛ ላይ በሠራቻቸው ሥራዎች በርካታ ሽልማቶችን ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ የውጪ ሀገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ማግኘት የቻለች እንስት ናት፡፡


በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ዴንሳ ከተራራው ስር በዓለ መርቆሬዎስ እንዲህ አምሮ እና ደምቆ ይነግሳል።


የመቀለ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያን በኃይል ለመቆጣጠር
የተደረገው ሙከራ መክሸፉ ተነገረ


በትግራይ ክልል በህወሓት አመራሮች መካከል ያለውን ክፍፍልና አለመግባባት ተከትሎ፣ አንድ የፓርቲው አባል በአምስት ታጣቂዎች በመታገዝ፣ በዋና ከተማዋ መቀለ የሚገኝ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር ባደረገው ሙከራ፣ ለሰዓታት የዘለቀ ውዝግብ መከሰቱን የጣቢያው ሠራተኞችና ፖሊስ ለቢቢሲ አረጋገጡ።

በዛሬው ዕለት ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ረፋድ ላይ አንድ የፀጥታ ኃላፊና አምስት ታጣቂዎችን ይዞ ወደ መቀለ 104.4 ኤፍ ኤም ጣቢያ የደረሰው ግለሰብ፤ ጣቢያውን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት መክሸፉን የጣቢያው ሠራተኞች ተናግረዋል።

ከአምስት ታጣቂዎች ጋር ወደ ጣቢያው ያመራው ግለሰብ፣ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የሚባል የህወሓት አባል ሲሆን፤ ጣቢያውን ለማስተዳደር በመቀለ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶ/ር ረዳኢ "ተሹሚያለሁ" ሲል መናገሩ ተገልጿል። ዶ/ር ረዳኢ በዶ/ር ደብረጽዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ ለመቀለ ከንቲባነት የተሾሙ ሲሆን፤ በክልሉ ጊዜያዊው አስተዳደር ግን ሕገወጥ ከንቲባ ተደርገው ይወሰዳሉ።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሬዲዮ ጣቢያው ሠራተኛ፤ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የተባለው ግለሰብ በታጣቂዎች ታግዞ ወደ ጣቢያው ከዘለቀ በኋላ የተቋሙን ማህተም ከፀሐፊዋ በመንጠቅ ለሠራተኞች ማስታወቂያ መለጠፉን ተናግረዋል።

ስለ ክስተቱ ለቢቢሲ የተናገረ ሌላ የጣቢያው ሠራተኛ ደግሞ በዶ/ር ደብረጽዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ ደጋፊ የሆነ ግለሰብ፣ ደብዳቤ እንኳ ሳይዝ ጣቢያውን በኃይል ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጉን አረጋግጧል።

⬇️⬇️


ይህ ግለሰብ እንደሚለው፤ ይህ ክስተት በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ኃይል የትግራይ ቴሌቪዥንና ድምጸ ወያኔ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ከእጁ ስለወጣ ኤፍ ኤም መቀለን በመሣሪያ ኃይል በመንጠቅ መጠቀሚያ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ ነው።

ሌላ የድርጅቱ ሠራተኛ በበኩሉ፤ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ "በዶክተር ረዳኢ የተሾምኩት ትክክለኛው የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ እኔ ነኝ፣ ሥልጣን አስረክበኝ" በሚል ነባር የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሀለፎም ንርአን እንደጠየቀ ተናግሯል።

"ሥልጣን አስረክበኝ አለው፣ አቶ ሀለፎም ደግሞ ሹመት የሰጠህ ዶ/ር ረዳኢ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕገወጥ የተባለ ሰው ስለሆነ ሥልጣን ላስረክብህ አልችልም። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ደብዳቤ ይዘህ ከመጣህ ግን ሥልጣን አስረክብሃለው አለው፤ በዚህን ጊዜ አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ማኅተብ ከፀሐፊዋ በኃይል አስገድዶ ወስዶ፣ ለጣቢያው ሠራተኞች የስብሰባ ጥሪ ማስታወቂያ ለጠፈ" ብሏል።

ይህን ተከትሎ አቶ ሐለፎም፤ "እኔ እያለሁ ለምን ማህተም ነጥቀህ ማስታወቂያ ትለጥፋለህ?” በማለት የተለጠፈውን ማስታወቂያ እንዳነሱትና በዚህም የተነሳ ውጥረት እንደተፈጠረ ተናግሯል።

ይህ ፍጥጫ ከጠዋቱ 3፡30 እስከ ቀትር 6፡00 ሰዓት የቆየ ሲሆን፣ በመጨረሻ ከቀዳማዊ ወያነ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ተጠርቶ ሁለቱንም ግለሰቦችና ጣቢያውን ለመቆጣጠር የመጡትን ታጣቂዎች ይዘዋቸው መሄዳቸውን የጣቢያው ሠራተኞች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ሰዓት መቀለ በሁለቱም ህወሓት ክንፎች የተሰየሙ ከንቲባዎች ቢኖሯትም ላለፉት ሦስት ወራት ያለ ከንቲባ ቆይታለች። ቢቢሲ የዛሬ ጠዋቱን ከስተት በተመለከተ ለጣቢያው ነባር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃለፎም እንዲሁም ተሾሚያለሁ ለሚሉት አቶ ዘመንፈስቅዱስ ስልክ ደውሎ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልሰመረም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር አንድነት ነገሰ በበኩላቸው ጣቢያውን ለመቆጣጠር የተደረገውን ሙከራ አረጋግጠው ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

ኤፍ ኤም መቀለ 104.4 ጣቢያ፤ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሕግ መሠረት በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ፈቃድ የሚንቀሳቀስ ሆኖ ከተመሠረተ 16 ዓመታት ያስቆጠረ የሬዲዮ ጣቢያ ነው።

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.