"ከሟቹ ጋር የነበራችሁን ግንኙነት ብትገልፅልኝ"
"ሟች በሕይወት በነበረበት ጊዜ የነበረን ግንኙነት ያስተናጋጅ እና የተስተናጋጅ ነበር!"
"ሟች በሞተበት ቀን የነበረውን ሁኔታ ትገልፅልኛለህ?"
"ወደ ካፊያችን መጥቶ ውሃ አዘዘ፤አቀረብኩለት።በአጠገቡ ተቀምጠው ሻይ ሲጠጡ የነበሩ ሰዎች እንደነገሩኝ ወዲያው ከኪሱ ብዙ ክኒኖች አውጥቶ ባቀረብኩለት ውሃ እያወራረደ ዋጣቸው።አይ የቀን ጎዶሎ......ምነው ውሃውንም እንደ ክኒኑ ከቤቱ ይዞት በመጣ....."
"በጊዜው በሟች ፊት ላይ ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አንብበሃል?"
"ንባብ ላይ ያን ያህል ነኝ፤ጌታዬ"
"አልገባህም፤ስትመለከው ተስፋ ቆርጧል ብለህ ገምተህ ነበር?"
"መቼስ በርገር በሚቀረጠፍበት፤ኮካኮላ እንደ ውሃ በሚፈስበት ካፌ ውስጥ አንድ ሰው የቧንቧ ውሃ ብቻ ካዘዘ ተስፋ ቢቆርጥ ነው! ግን መልሶ እጁን ቦርሳው ውስጥ ሲከት ሳይ፤የምሳ ዕቃ ሊያወጣ ነው ብዬ ተዘናጋሁ"!
"ከዚያስ?"
"ከዚያ ልቤን ሲያወልቀው ለነበረ ተስተናጋጅ ስቴክኒ አድርሼ ስመለስ፣ያ ወጣት ወንበሩ ላይ ዘፍ ብሎ ተኝቷል።አይ ምስኪን! ይሄኔ ሮንድ አድሮ ይሆናል ብዬ ቸል አልኩት"
"የመጀመሪያ ርዳታ አላደረክለትም?"
"አድርጌለታለሁ፤ተኝቷል ብዬ ስላሰብኩ ዘፈኑን ቀነስኩለት፤በተጨማሪም አንገቱን ወደ ወንበር መደገፊያው አቃናሁት።በእኔ ቤት በስነስርዓት ማስተኛቴ ነበር።ለካ አጅሬ በሥነ-ሥርዓት እየሞተ ኖሯል"
"ሟች ከመሞቱ በፊት የተናገረው ነገር አለ?"
"ሰው ሲኖር መናገሩ መች ይቀራል!"
"አባባሌ አልገባህም፤ከመሞቱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገረው ነገር አለ ወይ?"
"የለም።ባይሆን ከጎኑ የተቀመጠ ተስተናጋጅ ተናግሯል'
ፖሊሱ በረጅሙ ተንፍሶ ወደ ወንበሩ መደገፊያ ተንጋሉ ሲያስብ ከቆየ በኃላ "አቶ አባተ፤ለማንኛውም ሟች ለነገይቱ ኢትዮጵያ ብዙ ምርምሮችን ያበረክታል ተብሎ የታሰበ ወጣት ነበር።ምን ያደርጋል፤ብዙ የእንቅልፍ ክኒኖችን በመውሰድ ራሱን አጥፍቷል፤" ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ።
አባተ አንገቱን ደፍቱ ትንሽ ካሰበ በኃላ "ከእናንተ ባላውቅም......ብሎ ጀመረ.....ሟች የዋጠው የእንቅልፍ ክኒን ከሆነ ጊዜው ይርዘም እንጂ መንቃቱ አይቀርም፣ቁርጡ እስኪታወቅ ድረስ መንግስት አስክሬኑን መቅበር ትቶ በወዶገባ ዘበኛ ቢያስጠብቀው ይበጃል ባይ ነኝ"
መርማሪው ፖሊስ አባተን በንቀት ለጥቂት ደቂቃ ካተኮረበት በኃላ መሄድ እንደሚችል ገለፀለት።
📘 ርዕስ፦መግባት እና መውጣት
✍️ደራሲ፦በእውቀቱ ስዩም
✈️
@Bemnet_Library