ስለ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት መከፈት
═══════❁═══════
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ከጃንሜዳ በስተሰሜን በኩል በሚገኝና የወይራ ዛፍ በሞላበት በአንድ ቦታ ላይ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ለማሰራት ስላሰቡ ከሁለት ዓመት በፊት ህንፃውን አስጀምረው ነበር።
በዚህም ዓመት ህንፃው ተጠናቆ ስላለቀ በስማቸው የሰየሙትን የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም. ሰኞ በ10 ሰዓት መርቀው ከፈቱት።
ለምረቃው በዓል የየሌጋሲዮኑ ሚኒስትሮችና ቆንስሎች ተጠርተው መጥተው ነበር። እኔም ለግዕዝና ለአማርኛ አስተማሪነት ትምህርት በአስተማሪነት ተመድቤ ታዝዤ በስፍራው ላይ ነበርኩና ስለ በዓሉ ሁናቴ ያየሁትን በሚከተለው እገልጻለሁ።
የትምህርት ቤቱ ሹም ሐኪም ወርቅነህ ከ15 ቀን ጀምረው የመዘገቧቸውን አዳሪዎችና ተመላላሾች ተማሪዎች በአንድ በኩል አሰልፈው፣ አስተማሪዎቹንም በሌላው በኩል አቁመው ሲጠባበቁ ቆዩ። አርባዎቹ የአርመን ልጆችም በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ ተሰልፈው ግቢውን በሙዚቃ ዜማ አደመቁት።
ከዚህ በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ በመኳንንት ታጅበው መጡና ከትምህርት ቤቱ በር ላይ ሲደርሱ ሹሙ ሐኪም ወርቅነህና ዲሬክተሩ ሙሴ ጒዮን ከአስተማሪዎችና ከተማሪዎች ጋር ሆነው ሰላምታ ሰጥተው ተቀበሏቸው። የአርመን ልጆችም "ማርሽ ተፈሪ" የሚባለውን አዲሱን መዝሙር በሙዚቃ ዘመሩላቸው። ይህ መዝሙር በዚያ ዘመን ገና መጀመሩ ነበር።
ልዑል አልጋ ወራሽ ከትምህርት ቤቱ አዳራሽ ገብተው በተለይ በተዘጋጀው ወምበር ሲቀመጡ መኳንንቱና የተጠሩት እንግዶች በቀኝና በግራ በየማዕርጋቸው ስፍራ ስፍራቸውን ይዘው ተቀመጡ። ከኢትዮጵያ መኳንንት ራስ ስዩም፣ ፊታውራሪ ደስታ ዳምጠው፣ ቀኛዝማች ዓምዴ፣ ከንቲባ ነሲቡ ዛማኔል፣ ብላታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴና አቶ ሳህሌ ፀዳሉ ነበሩ።
ከዚህ በኋላ ሐኪም ወርቅነህ በልዑል አልጋ ወራሽ ፊት ቆመው ንግግር አደረጉ። ከዚያም ቀጥሎ ልዑል አልጋ ወራሽ ስለ ትምህርት ነገር ከፍ ያለ ኃይለ ቃል ያለበትን ታሪካዊ ንግግር አደረጉ። ...
ልዑል አልጋ ወራሽ ተናግረው ሲጨርሱ ሦስት ጊዜ ከፍ ያለ ጭብጨባ ተጨበጨበ። ከዚያም ቀጥሎ የሻይና የብስኩት የሻምፓኝም ግብዣ ተደረገ። ለተማሪዎቹም ብስኩት ታደላቸውና በየክፍላቸው እየገቡ ተቀመጡ። ከዚህ በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ መኳንንቱንና እንግዶችን አስከትለው የትምህርት ክፍሎችንና መኝታ ቤቶችን ጎብኝተው ሲመለሱ የበዓሉ ፍፃሜ ሆነ።
በማግስቱ ሚያዝያ 20 ማክሰኞ የትምህርቱ ሥራ ተጀመረ። በዚያ በመጀመሪያው ጊዜ የተመዘገቡት ተማሪዎች 32 አዳሪዎችና 40 ያህል ተመላላሾች ነበሩ። በኋላ ግን የአዳሪዎቹም ሆነ የተመላላሾቹም ቁጥር በየቀኑ እያደገ የሚሄድ ሆኗል።
>>>
━━━━━━━━━━━
✍ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ
📔 ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው
ከ1891 - 1923
📄 137 - 141
━━━━━━━━━━━
* ማስታወሻ፦
ይህ ትምህርት ቤት በደርግ ዘመነ መንግሥት "እንጦጦ የቀለም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት"፤ በኋላም "እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ" በመባል ሲጠራ ቆይቶ አሁን 100ኛ ዓመቱን ሲያከብር በቀድሞ ስሙ "ተፈሪ መኮንን" ተብሎ የሚጠራ ሆኗል!!! 📖 📖 📖 📖 📖
https://t.me/Ethiobooks