በዓመታዊ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ላይ የቀረበ የማጠቃለያ አስተያየት፤
*
አመሰግናለሁ የተከበሩ ምክትል አፈ-ጉባዔ፣
የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላት፣
ምክር ቤታችን በ2014 በጀት ዓመት ያፀደቀው በጀት የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባከናወነው ኦዲት ባቀረበው ሪፖርት በርካታ የሂሣብ አያያዝ ግድፈቶች እና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች መኖራቸውን እንዲሁም አፈፃፀማቸው ከሕግ እና ከተዘረጋው አሰራር ውጪ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርቱን በመገምገም በምክር ቤቱ እና በፌዴራል ዋና ኦዲተር ትኩረት ሊያገኙ የሚገቡ አንኳር ምክረ-ሃሣቦችን እና የማጠቃለያ አስተያየቶችን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የመንግሥት እና የሕዝብ ኃብት ለታለመለት እና ለታቀደለት ተግባር በትክክል ሥራ ላይ እንዲውል ለመቆጣጠር እና ለመከታተል ይረዳው ዘንድ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ የመረጃ አያያዝ፣ ተግባራትን በዕቅድ መፈፀም እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ዋና ዋና ጥንካሬዎቹ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡
በሌላ በኩል የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለክልሎች የሚተላለፈውን የድጎማ በጀት ኦዲት ሪፖርት አስመልከቶ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የበላይ አመራሩን በቂ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን እንዲሁም የሕግ እና ፖሊሲ ድጋፍ የሚሹ አሰራሮችን ለይቶ አለማቅረቡን እንዲሁም የ2014 በጀት ዓመት የፌዴራሉ መንግሥት አጠቃላይ ገቢ እና ወጪ ኦዲት ሪፖርት በተመለከተ ባቀረበልን ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት የተብራራ ነገር አለማቅረቡን ቋሚ ኮሚቴው በድክመት አይቶታል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ግኝትን ለማሻሻል የክትትል ኦዲትን ማሳደግ፣ የአገሪቱን የ1ዐ ዓመት መሪ ዕቅድ ለማስፈፀም እንዲቻል የልማት ኘሮጀክቶችን የዕቅድ ክትትልና የአፈፃፀም ግምገማ በማድረግ ውጤት ማስገኘት፣ የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲትና የክዋኔ ኦዲት ሥራዎች በዓለምአቀፍ ደረጃ ጥራታቸውን የጠበቁ በማድረግ የሪፖርቱን ተዓማኒነት በማሳደግ ተቀባይነቱን ማረጋገጥ፣ የመስሪያ ቤቱን የውስጥ አሰራር ውጤታማነቱንና ቅልጥፍናን የሚያረጋግጡ ሪፎርሞች ለመተግበር ከኦዲት ኮሚሽን ጋር በቅርበት መስራትን ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ ሊወስድ ይገባል፡፡
የተከበረው ምክር ቤትም በስሩ ባደራጃቸው የቋሚ ኮሚቴዎች በኩል ለኦዲት ሪፖርቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶችን ዕቅድና የአፈፃፀም ሪፖርት ሊገመግምና ውጤት እንዲመጣ ጥረት ሊያደርግ ይገባዋል፡፡
የ2014 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ግምገማን መነሻ በማድረግ በቋሚ ኮሚቴው በኩል የቀረቡ ምክረ-ሐሣቦች፤
1. የገንዘብ ማስመለስ ምጣኔ 0.65% ብቻ መሆኑ አስፈፃሚው አካል ለኦዲት ግኝት ትኩረት ያለመስጠቱን እንዲሁም በመቆጣጠር ተጠያቂነትን የማስፈን ኃላፊነት የተጣለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በስሩ የተቋቋሙ ቋሚ ኮሚቴዎች የኦዲት ግኝት ሪፖርቶችን የቁጥጥር መሣሪያ አድርገው ከመጠቀም እና በአጠቃላይ አስፈፃሚውን አካል ከመቆጣጠር አኳያ ውሱንነቶች ያሉባቸው መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የመቆጣጠር እና ከፊል የመቆጣጠር የሕግ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ገንዘብ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር በአግባቡ በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ካልቻሉ የመንግሥትና የሕዝብ ኃብትና ንብረት ከመንግሥት ሕግ አሰራርና መመሪያ ውጪ ጥቅም ላይ መዋሉ የብሔራዊ ደኀንነት ስጋት ሆኖ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለሆነም በተለይም የተከበረው ምክር ቤት ተጠያቂነትን ሊያሰፍን ይገባል፡፡
2. ነቀፌታ የሌለበት አስተያየት የተሰጣቸው ተቋማት ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መምጣቱ በመልካም ጎኑ የሚታይ ሆኖ አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸውና የጎላ ችግር ያለባቸው ሆነው በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጣቸው ተቋማት 25 የሚደርሱ መሆናቸው በተለይም እነዚህ ተቋማት ከሚያንቀሳቅሱት ፋይናንስ፣ የሰው ኃይል እንዲሁም ለአገር እና ሕዝብ ካሏቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች አንፃር ሲታይ በኦዲት ግኝቱ የተሰጣቸው አስተያየት አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም የተከበረው ምክር ቤት እና በስሩ ያቋቋማቸው የቋሚ ኮሚቴዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት በማጤን ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የማስተካከያ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡
3. እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተሰብሳቢ ገንዘብ መኖሩ እና ከዓመት ዓመት የሚስተዋለው የመሰብሰብ ምጣኔም ለዜሮ የቀረበ መሆኑ፣ ዜጎች በተቋማት እና በፋይናንስ ሕጎች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች ላይ ያላቸውን አመኔታ ከመሠረቱ ተጠየቅ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ስለሆነም የተከበረው ምክር ቤት ብርቱ አቋም ወስዶ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የፋይናንስ ሕግጋትንና መመሪያዎችን በማክበር የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ በአጽንፆት እንዲያሳስብ እንዲሁም የመንግሥትና ሕዝብ ኃብትና ንብረት እንዲመለስ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ፣ ተጠያቂነትንም እንዲያሰፍን በአንክሮ እንጠይቃለን፡፡
4. በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ተመን ሳይወጣላቸው ከሕግ ውጪ የሚሰበሰቡ ገንዘቦች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ይኸውም ለሙስና እና ብልሹ አሰራር እንዲሁም ለቁጥጥርና ኦዲት ሥራ አመቺ ባለመሆኑ፣ የተከበረው ምክር ቤት አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት ውሳኔ ሊያሳርፍ ይገባል፡፡ የሚኒስቴሮች ምክር ቤትም ከዚህ አንፃር የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በቁልፍ ተግባር ይዞ ማስተካከያ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡
5. የመንግሥት ተቋማት ከሕግና መመሪያ ውጪ ግዥዎችን እየፈፀሙ በመሆኑ፣ ይኸውም ለከፍተኛ የኃብት ብክነትና ብልሹ አሰራር አጋላጭ በመሆኑ፣ የተከበረው ምክር ቤት ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አቋም ሊወስድ ይገባል፡፡
6. የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በየተቋሞቻቸው ያሉ ንብረቶችን በሕግ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በወጉ መወጣት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው ያሳስባል፡፡
7. የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከዓመት ዓመት ያለው የበጀት አጠቃቀም የኦዲት ሪፖርት እንደሚያሳየው ጥቅም ላይ ያልዋለ በጀት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን እንዲሁም ከተደለደለው በጀት በላይ ያለፈቃድ አዛውረው በመጠቀም በኩል ያለው ችግርም ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለሆነም የተከበረው ምክር ቤት በበጀት ማጽደቅ ወቅት የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ ያደረገ የበጀት ግምገማ እንዲያደርግ እና ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ቋሚ ኮሚቴው ምክረ-ሐሳቡን ያቀርባል፡፡
8. በበርካታ የመንግሥት ተቋማት እጅግ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን ወጪ ተደርጎ ደጋፊ ሰነድ ባለመቅረቡ ኦዲት ማድረግ እንዳልተቻለ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ያሳያል፡፡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለኦዲት ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ለምርመራ ማቅረብ የሕግ ግዴታ እንዳለባቸው በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት እና በፌዴራል ዋና ኦዲተር ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚስተዋሉ የሕግ ጥሰቶችን እንዲሁም ለብልሹ አሰራር እና ለምዝበራ አጋላጭ ሁኔታዎችን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ተጠያቂነትን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡