“እየፈነጠቀች ባልሆነችበት ጊዜም ቢሆን በፀሐይ መውጣት አምናለሁ፣ ሰው የለኝም በምልበት ጊዜም ቢሆን በፍቅር መኖር አምናለሁ፣ ዝም ባለበት ጊዜም ቢሆን በፈጣሪ አምናለሁ ”
ሁሌም ቢሆን ምርጫ አለ… በጎ አልባ በመሰሉኝ አማራጮች መሃል ሳይቀር ምርጫ አለ… ጸሐይ ስትጠልቅ ጨረቃ ላይ የመመሰጥ ምርጫ አለ… ጨረቃ ስትሰወር ከዋክብቱ ላይ የመታደም ምርጫ አለ… ከዋክብት ሲጠፉ ወጋገኑን ሙጥኝ የማለት ተስፋ አለ… ብርሃን ላይ ተመስጦ ጨለማን ያለማየት ዕድል አለ… “Keep your face to the sunshine and you cannot see the shadows. It’s what the sunflowers do.” ― Helen Keller
ብርሃን የከባቢዬ ውጤት አይደለም – የውስጤ ነጸብራቅ እንጂ… በውጫዊ ሁነት በጎነት ላይ የቆመ አይደለም – በራሴ ነፃ ፍቃድ የሚዳኝ እንጂ… ብርሃኔን ነጠቁኝ ብዬ የማልጮኸው ለዚህ ነው… መስኮቴ ላይ ቆሙ ብዬ የማልነጫነጨው ለዚህ ነው… ስለግል ድክመቴ ዳፋ ሌሎችን የማልሰዋው ለዚህ ነው… የብርሃኑ ማብሪያና ማጥፊያ እጄ ላይ ነው… ብርሃን ውስጤ ነው… ብርሃንነት ተፈጥሮዬ ነውና።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን ኮሎኝ ውስጥ በአንድ አይሁዳዊ እስረኛ እንደተፃፈ የሚገመት አንድ ግጥም በምድር ቤት ግድግዳ ላይ ተጭሮ ተገኘ… ግጥሙ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የሰነበተ ሰው የጫረው ግጥም አይመስልም… ዙሪያውን በሚዳሰስ ጽልመት ውስጥ የማቀቀ ሰው የከተበው አይመስልም… 6 ሚሊዮን አይሁድ እንደ ሰም ሲቀልጡ ያየ ሰው ክታብ አይመስልም… ምናልባትም ሊያይ የናፈቀውን ብርሃን ሳያይ ያሸለበ ሰው የተስፋ እንጉርጉሮም ነው… በዙሪያው ሁነት ያልሞተ ብርታቱ ግና ዛሬም ድረስ ለብዙዎች የብርሃን ጸዳል ይረጫል።