🌿🌿🌿🍃ጥቆማ🍃🌿🌿🌿
ካለመማር የማይሻል መማርማ አለ
~
አዎ አለመማር ያሳፍራል፣ ያስቆጫል እንጂ አያኮራም። በተለይ በዚህ ዘመን ያለው አለመማር ቀደም ባለው ዘመን ከነበረው አለመማር የከፋ ጉዳት አለው። ቆም ብሎ ያስተዋለ ብዙ ሰበዞችን መምዘዝ ይችላል።
መማር የአስተሳሰብ አድማስን ያሰፋል። የማስተዋል አቅምን ያዳብራል። ሌላው ቀርቶ በሃገራችን ተጨባጭ የዲን ሰዎች እንኳ አካደሚ ትምህርት በመማራቸው ይህንን ካላገኙት የተሻለ ብስለትና አቀራረብ ሲንፀባረቅባቸው፣ ያልተማሩት ደግሞ በዚህ ረገድ የጎላ ክፍተት ሲታይባቸው ያጋጥማል። ሁሉን ማለቴ አይደለም።
ግን መማር ምንድነው? ካምፓስ ደርሶ መመለስ ነው መማር? ዲግሪ መቁጠር ነው መማር? እንግሊዝኛ መቀላቀል ነው መማር? መማር ምንድነው?
በርግጥ መማር ብዙ እርከን አለው። ቀለም መቅመስ፣ ክፍል መቁጠር፣ ዲግሪ መደርደር ብቻውን መማር አይደለም። መማር መልለወጥ ነው። መማር ለህይወት ዋጋ መስጠት ነው። መማር በህሊና መኖር ነው። መማር ለወጡበት ማህበረሰብ ቅን መሆን ነው። መማር ለራስ የማይወዱትን ነገር ሌሎች ላይ አለማድረስ ነው። ይሄ ደግሞ ጥልቅ ንባብ፣ ማሰላሰል፣ አእምሮን ማስፋት፣ የተማሩትን ሆኖ መገኘት ይጠይቃል። በሃገራችን ተጨባጭ አብዛኛው "ምሁር" በዚህ ረገድ ሲታይ ተምሯል ለማለት ይከብዳል።
የትምህርት ስርአታችን በራሱ በሳል ትውልድ የሚመረትበት ከመሆን ይልቅ ለሃገር ፀር፣ ለወገን ጠንቅ የሆኑ መርዛማ ትውልዶችን ወይም ሻል ካለ ካንገት በላይ ሳይሆን ካንገት በታች የሰፉ ሆድ አደር አድር ባይ የሃገር ሸክሞችን ነው እያመረተ ያለው። የትምህርት ስርአታችን አባት አጥቷል። የተቋቋመበትን አላማ ዘንግቷል። በርካሽ ጥቅማጥቅም ፍትህ እየሸጠ ያለው ዳኛ፣ ethicሱን የረገጠው ሃኪም፣ የህዝብ እንባ የማይገርመው civil servant፣ የሃገርን እድገት በራሱ የተንጣለለ ቪላ እና የተንደላቀቀ ህይወት የሚመዝን ሹመኛ፣ ጥላቻ እየቸርቸረ በህዝብ ስም የሚነግድ የደም ነጋዴ የሆነ ፖለቲከኛ፣ ሚዲያን ያክል ትልቅ የለውጥ መሳሪያ ይዞ ሳለ ድባቡን እንዳለ በክፋት፣ በአድር ባይነት፣ በአርቲቡርቲ የሞላው ጋዜጠኛ፣ ... የትምህርት ስርአታችን እንዲህ አይነት ጃርቶችን ነው ያፈራውና እያፈራ ያለው።
የማህበረሰብን ለዘመናት የዘለቀ በሰላም አብሮ የመኖር እሴት የሚንድ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ፣ በህዝብ መሃል መርዝ የሚዘራ መርዝ ትውልድ ቢማርም አልተማረም። ይህ ለተማሪዎቹ ዘር እየመነዘረ ውጤት የሚሰጥ "ምሁር" ተምሯል ሊባል አይችልም። ይሄ ሃይማኖት እየለየ ታዳጊ ልጆችን ከትምህርት ገበታ እየገፋ ያለው ገ ልቱ ፍጡር ለስሙ ካምፓስ ተመላልሷል እንጂ አእምሮው የሸረሪት ድር ያደራበት ኦና ቤት ነው። አልተማረም። የገዛ ወገኑ በኑሮ ስንክሳር ጎብጦ፣ በመከራው ላይ መከራ፣ በችግሩ ላይ ችግር የሚደራርብ ህሊና ቢስ ፖለቲከኛ ከተማሩት የሚቆጠር አይደለም። ወጣቱ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሲሄድ እየተመለከተ እውነቱን የማይጋፈጥና መንጋ የሚፈራ አድር ባይ ምሁር ከመሀይም አይሻልም። ከወጣበት ማህበረሰብ ይልቅ ለአላፊ ስርአት ጥብቅና እየቆመ በወገኑ መከራ ላይ አይኑን ጨፍኖ ምናባዊ የተድላ ዓለም ያለን ያህል ሰርክ የሚደሰኩር "ሊቅ" ምኑን ተማረው?! ይሄ መደ ንቆር እንጂ መማር አይደለም።
እና ምን ለማለት ነው? ሰው በሃገራችን ተጨባጭ መማርን ቢወቅስ አትፍረዱበት ለማለት ነው። ሃሳቡ ልክ ባይሆንም ጤነኛ ምሳሌ ሳስቶበታል። ከተማሩት የሚያየው ግራ የሚያጋባ ነው። የመማር ትርጉሙ ምን እንደሆነ እንዲደበዝዝበት ተደርጓል። ተምሯል፣ ተመራምሯል፣ ለሃገር ለወገን ይጠቅማል ብሎ ተስፋ የጣለበት አካል ጭራሽ ተስፋውን የሚነጥቅ ሲሆንበት እንዴት ግራ አይጋባ?!
"እዩልኝ ስሙልኝ ሰው ይፈርዳል በኔ
በግንቦት አግብቻት ወለደች በሰኔ" አለ ግራ የገባው። ግራ የገባው ሰው ብዙ ይላል። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ምሁር ነገር ላልተማረው ቀርቶ ህሊና ላለው ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው። እና ያልተማረው ምን ያድርግ? ባየው ፈረደ።
ቢሆንም! ቢሆንም! ቢሆንም አለመማር አያኮራም። አለመማር ይሻላል እያልክ በነውርህ እንዳትመፃደቅ። አለመማር ስንኩልነት እንጂ ጌጥ አይደለም።
✍IbnuMunewor
https://t.me/ibnukedir