Postlar filtri




ካቴድራሉም ተጠናቆ ተመርቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ በጣም ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡ 

ልዑካኑ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ የግብጽ ኮፕቲክ ፓትርያርክ የተላከውን ስጦታ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያስረከቡ ሲሆን ቅዱስነታቸውም ስለ ስጦታው አመስገነዋል። ልዑካኑም ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና ይሁንታ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዕድሳቱ ተሠርቶ ማለቁ እጅግ ደስ እንዳሰኛቸው በመግለጽ የግብጽ ኮፕቲክ እንደተለመደው በካቴድራሉ መገልገል የሚችሉበት መንገድ ስለ ተመቻቸላቸው አመስገነዋል፡፡

ሜትሮፖሊታን በመጨረሻም ለኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ባስተላለፉት መልእክት “ኢትዮጵያውያን በእምነታችሁ ጠንካራ ክርስቲያኖች ናችሁ፡፡ የሰይጣን ፈተና በመላው ዓለም ለምንኖር ክርስቲያኖች ቢሆንም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ ፈተናውን ያሳልፍልናል፡፡ በቤተክርስቲያን ሁናችሁ ጸልዩ" ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ምንጭ :- የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  የግብጽ ኦርቶዶክስ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ልዑካንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸው ተገለጸ፡፡

ጥር ፳፬/፳፻፲፯ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበ ተክለ ሃይማኖት የግብጽ ኮፕቲክ ቤተርክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ታውድሮስ ሁለተኛ መልእክት ይዘው የመጡትን ሜትሮፖሊታን አምባ ቢመን የነጋዳን፣ ጉስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳም ሓላፊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም አነጋግረዋል፡፡

ሜትሮፖሊታን አምባ ቢመን ኮፕቲክ ቤተርክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ታውድሮስ ሁለተኛ ያመጡትን መልእክት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም  ቅዱስነታቸው የግብጽ ኮፕቲክ ልዑካንን ተቀብለው በማነጋገራቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ይህም የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናትን  አንድነት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፡፡

በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት የጥንት መሆኑን ያስረዱት ሜትሮፖሊታን አምባ ቢመን “በግብጽ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ፤ በዚያም ቤተክርስቲያን አላቸው ይጸልያሉ፡፡ የግብጽ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ለአማኞቿ አገልግሎት የምትሰጥበትን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  በጥሩ ሁኔታ ዕድሳት ተደርጎለት ተመርቆ ለአገልግሎት የሚጀምሩበትን ደብዳቤ ከቅዱስነታቸው መቀበላቸውን” አስረድተዋል፡፡

የሁለቱም አብያተ ክርስቲያንናት ግንኙነትም በጣም ጥሩ ነው ያሉት አቡነ ኤንገሎስ ኤልነጋዲ በኢትዮጵያ የግብጽ ቤተክርስቲያን ተወካይ እንደተናገሩት፤ በዚያም ቤተክርስቲያን አላቸው ይጸልያሉ፡፡ በኢትዮጵያም የግብጽ ቤተክርስቲያን አገልግሎቷን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳምና በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ታካሂዳለች፡፡


በሲዳማ ሀገረ ስብከት በሀዋሳ ከተማ የታነጸው የሀዋሳ አየር ማረፊያ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ተመረቀ።

ጥር ፲፱/፳፻፲፯ ዓ.ም

በኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ማኀበረሰብ፣በCAPAT ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የበረራ ሠራተኞች መንፈሳዊ ጉባኤ እና በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት የታነጸው የሀዋሳ አየር ማረፊያ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን በትናንትናው ዕለት ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ ውሏል።

በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው የደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ  አህጉረ ስብከት እና በመንበረ ፓትርያርክ የቅርሳ ቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሙዚየም መምሪያ የማኅበራት መምሪያ  የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ፣መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ክፍል ኃላፊዎች፣መ/ፀ/መ/ር/ቆ/አባ ኪዳነማርያም የሀዋሳ ደ/ም/ቅ/ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪን ጨምሮ የሌሎች ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደተናገሩት ይህ ቤተክርስቲያን የተሰራው የእግዚአብሔር ስም እንዲጠራበት እንዲሁም ምእመናን እንዲባረኩበት ነው ያሉ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜም ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በዓለ ንግሡም ተከብሯል፡፡

በተጨማሪም በቦታው በርካታ ቁጥር ያላቸው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውጭ የሆኑ ምእመናን በታደሙበት ለተግባሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀትና ስጦታዎች ተበርክቷል።

የተመረቀው ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በሚያዝያ 05 ቀን 2016 ዓ.ም መሠረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።


“መከራ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና ለእኛ  ለልጆቿ  አዲስ አይደለም!!”፡- ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

ጥር ፲፱/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የወልድያ ማእከል ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ለብፁዕ አቡነ ቄርሎስን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥር 17 ቀን 2017 ዓ.ም  የገና እና የጥምቀት በዓላትን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደርሰዎ መርሐ ግብር አከናውነዋል።

ብፁዕነታቸው እንደተናገሩት “መከራ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለእኛ ለልጆቿ  አዲስ አይደለም” ስለዚህ  ሁላችሁም በመከራው ተስፋ ሳትቆርጡ በመጽናት የምትችሉትን ሥራ ሥሩ  በማለት የተናገሩ ሲሆን እንደ ማኅበርም አንድነታችሁን አጽኑ በማለት አባታዊ መመሪያ እና ቡራኬ ሰጥተው ስለጠየቃችሁኝ አመሠግናለሁ ብለዋል።

በተጨማሪነትም በመርሐ ግብሩ ላይ በማእከሉ መዘምራን መዝሙር የቀረበ ሲሆን  አጠቃላይ የማኅበሩን የሥራ እንቅስቃሴ እና የአባላትን ሁኔታ  ጠይቀዋል፡፡



6 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.