⭕️መልዕክት አለኝ!⭕️
በቲፎዞ የሰከረ ማንነት!
ዶ/ር ኢዮብ ማሞ
ቻርልስ ብሎንዲን (Charles Blondin) በቀጭን ገመድ ላይ
በመራመድ የታወቀ ፈረንሳዊ ነው፡፡ በዘመኑ እጅግ ዝነኛ
የነበረው ይህ ሰው ከአንድ ግዙፍ ህንጻ ወደሌላኛው ህንጻ
በተዘረጋ ቀጭን ገመድ ላይ በመራመድ ተመልካቹን ትንፋሽ
በማሳጠር የታወቀ ሰው ነው፡፡ በቀጭን ገመድ ላይ
ከተራመደባቸው የከፍታ ስፍራዎች አንዱ በአሜሪካና በካናዳ
ጠረፍ ላይ በሚገኘው ናያግራ ፏፏቴ (Niagara Falls) ከፍታ ላይ
ያደረገው ይደነቅለታል፡፡
ከአሜሪካ ግዛት እስከ ካናዳ ግዛት
የፏፏቴው ጥጎች የተዘረጋውን ቀጭን ገመድ በመራመድ
ከተሻገረ በኋላ እንደገና ወደ አሜሪካው ግዛት በገመዱ ላይ
ሲመለስ የሚመለከተው ህዝብ ስለእርሱ ጭንቅ ይዞት ነበር፡፡
የሕዝቡ ጩኸት ቀልጧል፡፡ “አንተን የሚያክል የለም፣ ጀግና ነህ
… ” አሉት፡፡
ሁሉም ሰው ከተረጋጋ በኋላና ሕዝቡን ካመሰገነ በኋላ አንድ
ጥያቄ ጠየቃቸው፣
“በእርግጥም ጎበዝ እንደሆንኩ
ታምናላችሁ?” አላቸው፡፡
ሕዝቡ በአንድ ድምጽ፣ “አንተ
የምታደርገውን ሊያደርግ የሚችል ፈጽሞ አይገኝም፤ ምንም
ነገር ማድረግ ትችላለህ” በማለት አረጋገጡለት፡፡
“ይህን ያህል
ካመናችሁብኝ ከእናንተ መካከል በትከሻዬ ላይ ተሸክሜው
እንደገና በዚህ ቀጭን ገመድ ላይ እንድራመድ ፈቃደኛ የሆነ
ሰው ማን ነው?” አለ፡፡
ሕዝቡ በጸጥታ ተሞላ፡፡ አንድም ሰው
ፈቃደኛ ሊሆን አልፈለገም፡፡
ብሎንዲን ወደ አንድ የቅርብ ወዳጁ ዘወር በማለት ፈቃደኝነቱን
ጠየቀው፡፡ ይህ ወዳጁ ከፍታን እጅግ የሚፈራ ሰው ነው፡፡ ትንሽ
የወላወለው ይህ ወዳጁ በመጨረሻ ተስማማና ትከሻው ላይ
ሆኖ ያንን አስፈሪ ከፍታ አብረው ተሻገሩ፡፡
ይህ የቀጭን ገመድ
ተራማጅ #አድናቂዎቹ ብዙዎች፣ #አጋሩ ግን አንድ ሰው ብቻ እንደ
ነበር የተገለጠለትና ከደጋፊ ብዛት ከተጠናወተው ስካር ሰከን
ያለው ያን ጊዜ ነው፡፡
የሰው ልጅ የሚሰክረው በአልኮል መጠጥ ብቻ አይደለም፡፡
የሰው ልጅ በስኬት፣ በገንዘብ ብዛትና በመሳሰሉት ጊዜያዊ
ነገሮች ሊሰክር ይችላል፡፡ ከዚህ የከፋው የስካር አይነት ግን
ከጀርባው የሚደግፈው ቲፎዞ የበዛ ሲመስለውና “ጀግና”
የሚለው ሰው ሲበራከት ራሱን የመግዛት ብቃት ከሌለው
የሚሰክረው ስካር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ልክ አንድ በመጠጥ
ተጽእኖ ስር ወድቆ የሰከረ ሰው የሚያደርገውን እንደማያውቅ
ሁሉ በመደነቅ ተጽእኖ ስር ወድቆ የሰከረ ሰውም ማመዛዘን
የሚሳነው፡፡
አጭር ምክር …
• ያደነቀን ሁሉ አብሮን የሚዘልቅ አጋር እንዳይመስለን፡፡ ዛሬ
“ሆ” ያለን ሰው ሁሉ ነገ ሕይወት የየራሱን የቤት ስራ
(Assignment) ሲሰጠው ከእኛ ዘወር ሊል የሚችልበት አጋጣሚ
ሊፈጠር ይችላል፡፡
• ወደዚህ ዓለም የመጣነው ብቻችንን ነው፣ የምንሰናበተውም
ብቻችንን ነው … በመካከሉ ግን በዚህ ምድር ላይ ባለን ቆይታ
ለብቻችን ስንሆን የሚሞግት ኅሊና ከፈጣሪ ተሰጥቶናል
ኅሊናችንን ብናደምጠው ይበጀናል፡፡
• ከደጋፊዎችና ከአድናቂዎች ብዛት የተጠናወተን ስካር አንድ ቀን
በረድ እንደሚል አንርሳ፡፡ ያን ጊዜ የምንነጋገረው ከእውነት ጋር
ነው፡፡ እውነት በመጀመሪያ ስትመክር ለስላሳ ነች፣ ካልሰማናት
ግን በኋላ ስትፈርድ ጨካኝ ነች፡፡
• ከአእላፋት ደጋፊዎች ኃይል ይልቅ የአንዲት እውነት ጉልበት
እንደምትበረታና እንደምታሸንፍ እናስታውስና ዛሬውኑ በሰከነ
አእምሮ ከእውነት ጋር እንስማማ፡፡
@pilasethiopia