✞ ጥምቀተ ክርስቶስ ✞ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ክፍል አንድ (፩)በነቢያት የተነገረው ትንቢት በወንጌል የተጻፈው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፡፡
ጥምቀት የሚለው ቃል"ተጠምቀ – ተጠመቀ" ካለው ግሥ የወጣ ነው፤ ትርጕሙም በውሃ መጠመቅ ማለት ሲኾን፣ ይኸውም በወራጅ ወንዝ፣ በሐይቅ ውስጥ ወይም በምንጭ የሚፈጸም ነው፡፡
በካህናት እጅ የሚፈጸመው ጥምቀት ከሌላው ጥምቀት ይለያል፡፡
በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ሲሆን በዘመነ ሐዲስ የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ከሁለቱም ልዩ ነው፡፡ እርሱ ሰውን ያከብራል እንጅ ከሰው ክብርን የማይፈልግ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡
ለእኛ አርአያና አብነት ለመኾን በዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱነን ከአብ እና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመስክሮ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ጾምን ጀምሯል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን ኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ፣ ያስቈጠረውን የዘመን ሱባዔ፣ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው እንጂ፡፡
የተነገረውን ትንቢት፣ የተመሰለውን ምሳሌም እንደሚከተለው መጻሕፍት ይነግሩናል፤
"ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እም ኀበ ዮሐንስ፤ ያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስመጣ፤"ማቴ.፫፥፲፫፤ ማር.፩፥፱፤ ሉቃ.፫፥፳፩፤ ዮሐ.፩፥፴፪
ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን ብሎ አይኾንም አለው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ
"የጌታየ እናቱ እኔ ወደ አንቺ እመጣለሁ እንጂ አንቺ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን?"ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናግሮታል፡፡
ጌታም መልሶ 'ይህ ለኛ ተድላ ደስታችን ነው፤ አንተ ‹መጥምቀ መለኮት› ተብለህ ክብርህ ሲነገር፤ እኔም ‹በአገልጋዩ እጅተጠመቀ› ተብዬ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራል፡፡ ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናልና አንድ ጊዜስ ተው' አለው፡፡
አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ፤ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ፤ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ አያሻውምና፡፡
ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታም በዮሐንስ እጅ እንዲጠመቅ በነቢያት ትንቢት ተነግሯልና ጌታችን "ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናል" አለ፡፡ ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፤ እንደዚሁም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ፣ ለባሕርይ ልጁ ለእኔ፣ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ደስታችን ነውና ማለቱ ነው፡፡
አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ኾኖ "ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር፤ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤" ብሎ ሲመሠክር፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ተገልጧልና፡፡
ጌታችን ዮሐንስን 'የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናል … አንድ ጊዜስ ተው' ካለው በኋላም ተወው (ለማጥመቅ ፈቃደኛ ኾነ)፡፡
ዮሐንስም "አብ በአንተ በመንፈስቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነህ፡፡ መንፈስቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተንበማን ስም ላጥምቅህ?" ቢለው ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ" ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ባሕር ወርደዋል፡፡
"ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኀው ወጣ፤"ዮሐ.፫፥፲፮፡፡
ቃለ ወንጌል "ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ሰማይ ተከፈተለት" ይላል፡፡ ይህን ሲልም በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም፡፡ የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው ዕቃ በግልጽ እንዲታይ ጌታን ሲጠመቅ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ታየ ሲል ነው፤ ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡
ከዚህ ላይ
ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሔዶ መጠመቁ ለምንድን ነው? ምነው አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? የሚል ጥያቄ ከተነሣ ጌታችን መምጣቱ ለትሕትና እንጂ ለልዕልና አይደለምና ነው፡፡ ዳግመኛም ለአብነት ነው፤ ጌታችን ዮሐንስን 'መጥተህ አጥምቀኝ' ብሎት ቢኾን ኖሮ ዛሬ ነገሥታት፣ መኳንንት ካህናትን 'ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን' ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሒዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመኾን ራሱ ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሔዶ ተጠመቀ፡፡
ጌታችን መጠመቁም ለእርሱ ክብር የሚጨመርለት ኾኖ አይደለም፤ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትኾን ለማድረግ፤ እኛ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ለማድረግ፤ እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመኾን ነው፡፡ "ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡
"… ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰኢአምነ ወኢተጠምቀ ኢይድኅን፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፤"ተብሎ ተጽፏልና።
ዮሐ. ፫፥፫፤ ማር.፲፮፥፲፮
ያውስ ቢኾን ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው? ቢሉ.... ክፍል ሁለት ይቀጥላል.... 🙏
ይቆየን 🙏
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈ @yemezmur_gexem
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈