የዕለቱ አንኳር ዜናዎች
1. የትግራይ ልሂቃን ልዩነታቸውን በመግባባትና የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈቱ ጥሪ ቀረበ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ልሂቃን በውስጣቸው ያለውን ልዩነት በመግባባት፣ በሰላም እና የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ መንገድ ሉፈቱ ይገባል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ለክልሉ ልሂቃን እና ለትግራይ ሕዝብ መግለጫ አውጥተዋል። ይሁን እንጅ በተለያዩ አጋጣሚዎችና በተለያዩ ምክንያቶች፣ በተለይ ደግሞ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ባጋጠመ አለመግባባት የትግራይ መሬት የጦርነት አውድ፤ የትግራይ ህዝብ ደግሞ የጦርነት ሰለባ መሆኑን ገልፀዋል። የትግራይ ህዝብ የትላንት ቁስሉ ሳይሻር፣ ገና አሁንም ሰላምና እፎይታ አግኝቶ ሰርቶ እንዳይገባ በፍራቻና ጭንቅ የጦርነት ወሬ እየኖረ መሆኑ አሳዛኝ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ከፌዴራል መንግስት ይሁን ሌሎች ሃይሎች ጋር ያሉትን ልዩነቶች በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመግባባት ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆኑ መክረዋል። በፌዴራል መንግስት በኩል፥ በሁሉም ጉዳዮች ለመነጋገር እና የሐሳብ ልዩነት እንደ ልዩነት በመውሰድ በሚያግባቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰላም መስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
2. በአማራ ክልል ያሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተማሪዎቻቸው የተግባር ተኮር ስልጠና ለመስጠት የጸጥታ ችግር እንቅፋት ሆኖብናል አሉ። የጤና፣ ህግ፣ ታሪክና መሰል የትምህርት መስኮች የሚማሩ ተማሪዎችን ለተግባር ተኮር ስልጠና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመውሰድ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተናግሯል። አሁን ላይ የህግ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ራቅ ወዳለ ቦታ ሳይሄዱ በከተማው ለማሰልጠን የታቀደ ቢሆንም እንደ ታሪክ እና ጤና የመሳሰሉት የትምህርት መስክ ሰልጣኞች ወደ ሌላ ክልል እና ከተማ ተንቀሳቅሰው የሚማሩት እንደመሆኑ ሰልጣኞች ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው ውድድር ተጽዕኖ ይፈጥርባቸዋል ተብሏል።
3. በትግራይ ክልል የጤና መድህን አገልግሎት ለማስጀመር በሚደረገው የቅድመ ዝግጅት ስራ በክልሉ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው። በክልሉ በነበረው ጦርነት የጤና መድህን አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጅ በክልሉ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፤ የበጀት እና የሰው ኃይል እጥረት ተግዳሮት እየፈጠረ መሆኑን በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ ተናግሯል። 206 ሰራተኞች እንዲቀጠሩ የማድረግ እንዲሁም ማህበረሰቡ አሁን ባለበት የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የአገልግሎቱን ክፍያ መፈጸም ስለማይችል 50 በመቶ የሚሆነውን በተቋሙ መሸፈን እንዲያስችል የሃብት ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል። የምዝገባ ሂደቱን በታህሳስ ወር ለማስጀመር የታቀደ ቢሆንም በታቀደው የጊዜ ቀጠሮ ማስኬድ አልተቻለም።
4. በዳውሮ ዞን በትራፊክ አደጋ የ 2 ሰዎች ህይወት አለፈ። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ ከገሣ ከተማ ወደ ሎማ ባሌ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አይሱዚ ተገልብጦ የሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በደረሰው አደጋ 10 መንገደኞች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሳባቸውም ተገልጿል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአቅራቢያ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
5. ደቡብ አፍሪካ ለዶናልድ ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጠች። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጠው ድጋፍ ይቋረጣል ሲሉ በትናንትናው ዕለት ዝተው ነበር። ሀገሪቱ መሬት እየወረሰች ነው፤ አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎችም በመጥፎ ሁኔታ እየታዩ ነው ሲሉ የተናገሩት ፕሬዝዳን ዶናልድ ትራምፕ ዝርዝር መረጃዎችን ግን ይፋ አላደረጉም። ይሁንና በሁኔታው ላይ አስፈላጊው ምርመራ እስኪካሄድ ድረስ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚላክ እርዳታ እንደሚቋረጥ አስታውቀዋል። በአውሮፓዊያኑ 2023 አሜሪካ የ440 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለደቡብ አፍሪካ ሰጥታ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ በዚህ እንዳለ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ግን አሜሪካ ለኤችኤይቪ ኤድስ መከላከል ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር የተለየ የገንዘብ ድጋፍ ከዋሸንግተን እንደማያገኝ አስታውቋል።
@zena_ethiopia24@zena_ethiopia24