ትምህርት ከፖለቲካ መጠቀሚያነት ነጻ መሆን አለበት‼️
🗣ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
የትምህርት ዘርፉ ከፖለቲካ መጠቀሚያነት ነጻ ሆኖ ለትምህርት ዓላማ ብቻ መዋል እንዳለበት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት የትምህርት ዘርፍ አፈጻጸም 5 ሺህ ትምህርት ቤቶች ከሥራ ውጭ መሆናቸውን እና በዚህም ምክንያት 7.2 ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት አለመቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለመምራን እና የትምህርት አመራሩ መንገላታት እና ለትምህርት ቤቶቹ መዘጋት ምክንያት በየአካባቢዎቹ የሚፈጠሩ ግጭቶች መሆኑን አውስተው፣ ይህ ደግሞ እንደ ሕዝብ ትልቅ ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡
ትምህርት ከፖለቲካ ማራመጃነት ነጻ ቢሆን አሁን የተከሰተው ችግር ባልተከሰተ ነበር ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አካላት ሁሉ የትምህርት ዘርፉን ከጥቃት መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
እንደ ኅበረተሰብ አይነኬ የሚባሉ ነገሮች መኖር አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የፖለቲካ ግጭቶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች መምህራንን ማገት እና መግደል እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ስለ መምህራን ደመወዝ እና ማበረታቻ በምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ የተነሳላቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ የመምህራንን ደመወዝ ማሻሻል ያልተቻለው አጠቃላይ ባለው በሲቪል ሰርቪስ አሠራር ምክንያት እንደሆነ እና ይህም ሆኖ በተቻለ መጠን መምህራን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዘዴ ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
መምህርነትን የተከበረ ሙያ ማድረግ ምንም አጠያያቂ እንደማይሆን አውስተው፣ ለዚህ ደግሞ መምህራን ልጆቻቸውን ምን እንደሚያበሉ የሚጨነቁበት ደረጃ ላይ እንዳይወድቁ የተለያዩ የማትጊያ ሥርዓቶችን ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ወደ ፍጻሜው እየደረሰ ያለውን የመምህራን ባንክን ለመመሥረት የተፈለገውም መምህራን ቢያንስ መሰረታዊ የሆነውን የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ ለመደገፍ ታልሞ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
@Esat_tv1@Esat_tv1