የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11/2017 ዓ.ም
በቅርቡ አገልግሎት ለሚጀምረው የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት የሚያገለግል የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
ሥነ-ሥርዓቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በቅንጅት ማከናወናቸው ተገልጿል፡፡
ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት የሚሆነው የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ-ሥርዓት የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ስታንዳርድ ማዕከል ባደረገ መልኩ የተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ እንደገለጹት፤ የዲጂታል ሰርተፊኬት ዋና ጠቀሜታ በይነ-መረብን በመጠቀም የሚካሄደው የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት ለከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ተጋላጭ በመሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ-ሥርዓት በሀገራችን በቅርቡ የሚጀምረውን የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት አጠቃላይ ደኅንነት ያረጋግጣል ነው ያሉት፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ምስጢራዊነትን፣ የመረጃን ምሉዕነትና ትክክለኛነትን፣ የመረጃ ልውውጥ ተሳታፊዎችን ማንነት ማረጋገጥ እና የመረጃ ልውውጥ መካካድን ማስቀረት የሚያስችል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የፓስፖርት ማጨበርበርን እና የማንነት ስርቆትን ለመከላከል የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሲሆን ይህም የፓስፖርት ባለቤቱን ማንነት በተሟላ መልኩ በማረጋገጥ ሊከሰት የሚችለውን የሐሰተኛ (ፎርጂድ) አሰራርና የማንነት ስርቆት ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት በየትኛውም ዓለም ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ በጉዞ ወቅትና በድንበር ላይ የሚኖሩ አሰራሮችን በእጅጉ የሚያቀላጥፍ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
(FMC)
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
——
Telegram:
https://t.me/ICS_EthiopiaFacebook:
https://www.facebook.com/ICSEthiopiaTwitter:
https://twitter.com/ics_ethiopiaTikTok:
https://www.tiktok.com/@ics_ethiopiaLinkedIn:
https://www.linkedin.com/company/icsethiopiaYouTube:
https://www.youtube.com/@Ics_EthiopiaInstagram:
https://www.instagram.com/icsethiopia/