"በምሽት የምትዘምር ወፍ የሌሊቱን ፀጥታ ቅር ታሰኛለችን? የምታበራ ትልስ ብትሆን በብርሃኗ ክዋክብትን ቅር ታሰኛለችን?"
ካህሊል ጂብራን
ከዚያም ከተማውን በየአመቱ አንድ ጊዜ እየመጣ የሚጎበኝ ባህታዊ ወደ ፊት መጣ:: አለውም፡-
‹‹ስለ ደስታ ንገረን?››
እሱም መለሰለት ደስታ የነፃነት መዝሙር ነው፤ይሁንና በራሱ ነፃነት አይደለም፡፡
‹‹የጽኑ ምኞቶቻችሁ ማበብ (መፍካት) ነው፡፡ ግን ደግሞ የፈኩት (ያበቡት) ምኞቶቻችሁ ፍሬ አይደለም..
‹‹ወደ ከፍታ የሚጣራ ጥልቀትም ነው ደስታ:: ይሁንና ጥልቀቱንም ሆነ ከፍታውን አይደለም..
‹‹በፍርግርግ ብረት በተሰራ ጎጆ ውስጥ የተያዘ እና የሚዘረጋ ክንፍም ነው፡፡ ነገር ግን የታጠረ ስፍራ አይደለም...
‹‹አዎን! በእውነቱ ደስታ የነፃነት መዝሙር ነው፡፡በልበ ሙሉነት እንድትዘምሩት እመኝላችኋለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን በመዘመር ልቦቻችሁን እንድታጡ አልመኝም....
‹‹ከወጣቶቻችሁ አንዳንዶቹ ደስታን ሁሉን ነገር እንደሆነ አድርገው በመቁጠር በብርቱ ያስሱታል፡፡ በዚህም ይወቀሳሉ፤ ይኮነናሉ፡፡ እኔ ግን አልፈርድባቸውም።፡ አልገስፃቸውምም። የበለጠ እንዲፈልጉት አደርጋቸዋለሁ እንጂ...
‹‹እነሱም ደስታን ያገኙዋታል፡፡ የሚያገኙዋት ግን ብቻዋን አይደለም፡፡ ሰባት እህቶች አሉዋትና:: ከሁሉም በዕድሜ ትንሿ ከደስታ ከራሱ እንኳን በጣም ውብ ነች...
"ስሮችን ለማግኘት ብሎ መሬትን ሲቆፍር የተደበቀ ሀብት ስላገኘው ሰው አልሰማችሁምን?...
"ከአዛውንቶች ጥቂቶቹ በደስታ ያሳለፉዋቸውን ጊዜያት በመጠጥ ስካር እንደፈፀሙዋቸው ስህተቶች በማሰብ ደስታዎቻቸውን በፀፀት ያስታውሷቸዋል፡፡ ይሁንና ፀፀት የአዕምሮ ማጨለሚያ እንጂ ቅጣቱ ራሱ አይደለም...
‹‹በመሆኑም የበጋውን መኸር እንደሚሰበስቡ ሁሉ የደስታ ጊዜያቶቻቸውንም ውለታ በማመስገን ማስታወስ ይገባቸዋል...
‹‹እንደዚያም ሆኖ መፀፀት መጽናናትን የሚሰጣቸው ከሆነ ይፅናኑ ተዋቸው...
‹‹ደግሞም በመካከላችሁ ደስታን ለመፈለግ እጅግ ወጣት የሆኑና ለማስታወስም ዕድሜያቸው የገፋባቸው አሉ፡፡ መንፈሱን እንዳይንቁ ወይም እንዳይበድሉ ሲያስቡ በሚያድርባቸው ኃይለኛ ፍርሃት የተነሳ ደስታን ለመፈለግም ሆነ ለማስታወስ አይሹም፡፡ የደስታ ጊዜያትንም በሙሉ ይሸሻሉ።
‹‹ ይሁንና ከዚያ በፊት ባሳለፉት ህይወታቸው ውስጥ ደስታቸው አለ፡፡ ደግሞም እነሱም ቢሆኑ በሚንቀጠቀጡ እጆቻቸው ስሮቹን ለማግኘት መሬትን ቢቆፍሩ የተደበቀ ሀብትን ያገኛሉ፡፡
‹‹የሆነስ ሆነና ንገሩን እስኪ?! ማን ነው እሱ መንፈሱን ቅር ሊያሰኝ የሚችል?....
‹‹በምሽት የምትዘምር ወፍ የሌሊቱን ፀጥታ ቅር ታሰኛለችን? የምታበራ ትልስ ብትሆን በብርሃኗ ከዋክብቱን ቅር ታሰኛለችን?...
‹‹ደግሞስ የምታነዱት እሳት ነበልባል ወይም ጢስ ለነፋስ ሽክም ይሆንባታልን?.... መንፈሱንስ ልክ በዘንግ ልታውኩት እንደምትችሉ የረጋ የገንዳ ውኃ ይመስላችኋልን?...
‹‹አብዛኛውን ጊዜ ለራሳችሁ ደስታን በመንፈጋችሁ በስብዕናችሁ ጓዳዎች ውስጥ ታከማቻላችሁ እንጂ ሌላ ምንም ነገር አታደርጉም....
‹‹ዛሬ የተረሳ የመሰለን ነገን ይጠብቅ እንደሆነስ ማን ያውቃል?..
‹ አካላችሁም እንኳን ቢሆን ውርሱን እና ህጋዊ ፍላጎቱን ያውቃልና አይታለልም፡፡ አካላችሁ የነፍሳችሁ ክራር ነውና...
‹‹እናም ከውስጡ ጣፋጭ ጣዕመ ዜማን ወይም አዋኪ ድምፆችን ይዞ እንዲወጣ ማድረግ የእናንተ ፋንታ ነው....
‹‹አሁን እንግዲህ በልባችሁ በደስታ ውስጥ መልካም የሆነውን መልካም ካልሆነ እንዴት እንለያለን?› ብላችሁ ጠይቁ...
‹‹ወደ እርሻ መሬታችሁ እና ወደ አትክልት ስፍራችሁ ሂዱ፡፡ እዚያ ከአበቦች ማር መሰብሰብ ለንብ ደስታን እንደሚሰጣት ትማራላችሁ፡፡ አበባውም ቢሆን ለንቧ ማሩን በመስጠቱ ደስታን እንደሚያገኝ አስታውሱ...
‹ለንቧ አበባ የህይወት ምንጯ ነው፡፡ ለአበባው ደግሞ ንቧ የፍቅር መልዕክተኛው ነች...
‹‹እናም ለንቧም ሆነ ለአበባው ደስታን መስጠትና መቀበል መሰረታዊ ፍላጎትና እና ታላቅ ትፍስህት ነው..
መፅሀፍ -የጥበብ መንገድ
ደራሲ -ካህሊል ጂብራን
@zephilosophy