#ኢትዮጵያ
" ' ወደ ውጪ እንልካችኋለን ' በሚል ምክንያት ' ተጭበርብረናል ፣ ተዘርፈናል ' እያሉ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ተበራክተዋል " - የአ/አ ፍትህ ቢሮአሁን አሁን በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች በተለይም ወጣቶች ወደ ውጭ ሀገራት የመሄድ ፍላጎታቸው እየተበራከተ መጥቷል።
እኚህ ወጣቶች ከሀገር ለመውጣት የተለያዩ ሙከራዎችንም ሲያደርጉ ይታያል።
የውጭ ጉዞ ለማድረግ ከሚሞክሩባቸው አንዱ መንገድ ደግሞ በደላሎች ፣ በጉዞ ወኪሎች እና በሌሎችም አማካኝነት ነው።
ወጣቶች በትምህርት ፣ በስራ እንዲሁም በጉብኝነት አማካኝነት ነው ከሀገር ለመውጣት የሚጥሩት።
የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመቀየር ፣ አፍላ የሆነ የወጣትነት እድሜያቸው ሳያልፍ አንዳች ነገር አፍርተው ቤተሰብ መስርተው ጥሩ ኑሮ ለመኖር ፤ ከድህነት ለመላቀቅ ሲሉ በሚሞክሯቸው የውጭ ሀገር እድሎች ግን ምንም ርህራሄ በሌላቸው አጨበርባሪዎች ሲታለሉም ይታያል።
የወጣቶቹን ፍላጎት እያየ ገንዘባቸውን የሚበላቸው ፣ አውሮፓና አሜሪካ ብሎ ሌላ የወንጀልና ደህንነት የሌለው ቀጠና የሚልካቸው ደላላ፣ ወኪል እየበዛ መጥቷል።
በመዲናችን አዲስ አበባ ህገወጥ ስራን የሚሰሩ የጉዞ ወኪሎች መበራከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ለአሃዱ በሰጠው ቃል ፤ በየጊዜው የውጪ ሀገር የጉዞ ወኪልና አማካሪ ድርጅቶች እንዲሁም ደላሎች " ወደ ውጪ እንልካችኋለን " በሚል ምክንያት ' ተጭበርብረናል፣ ተዘርፈናል ' እያሉ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች መበራከታቸውን አስታውቋል፡፡
እነዚህ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ተመላክቷል።
" እነዚህን ቅሬታዎች ተሰምተዉ ዝም የሚባልበት አግባብ የለም " ያለው ቢሮ በቀጥታ ለአዲስ አበባ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በመላክ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እየሰራሁ ነው ብሏል።
" በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ሰዎች ፍላጎት መበራከቱን ተከትሎ፤ ዜጎች ከሕግ ውጪ በሚሰሩ ድርጅቶችና ደላሎች አማካኝነት ረብጣ ገንዘባቸውን መጭበርበራቸው እየተባባሰ ይገኛል " ነው ያለው።
በብዙዎች ጥቆማና ቅሬታ መሰረት፤ ከዚህ ቀደም ከ40 በላይ ሕገ-ወጥ ሥራን በመስራት የተሰማሩ የውጪ ሀገር የጉዞ ወኪሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ቢሮው አመልክቷል።
ፍትህ ቢሮ ፤ " ህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ ወደ ውጪ ለመውጣት ሲፈልግ፤ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሕጋዊ የሆኑ ወኪሎችን ለይቶ ስላሰራጨ፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ ማግኘት ይችላል " ብሏል።
አልያም በአካል ቀርቦ መረጃ እንዲያገኝ ለአሃዱ በሰጠው ቃል አሳስቧል።
Via : tikvah
@Addis_Reporter @Addis_Reporter